ቡና ባንክ የንግድ መለያ ምልክት እና ቀለሙን ቀየረ

0
1907

ዕረቡ መጋቢት 7 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ቡና ባንክ ላለፉት 12 ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን የንግድ መለያ ምልክት (ሎጎ) እና ቀለም መቀየሩን በዛሬው ዕለት አስታወቀ።

ባንኩ ከአንድ ዓመት በፊት ”ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ“ የሚለውን ስያሜውን ”ቡና ባንክ“ ወደሚል መቀየሩ የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ በአዲስ የንግድ ምልክት አርማ እና ቀለም ለመምጣት ለኹለት ዓመታት ያህል የጥናት እና የዝግጅት ሥራዎችን አከናውኖ በመጨረሻም አዲሱን የንግድ ምልክት አርማና ቀለም በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።

ይህ ባንኩ ተቀየረው አዲሱ አርማና ቀለም በኢትዮጵያ ዐዕምሮአዊ ንብረት ፅ/ቤት ተመዝግቦ የፀደቀ ሲሆን፤ አዲሱ አርማ እና ቀለም የባንኩን ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች እንዲወክል ሆኖ የተዘጋጀ መሆኑን የቡና ባንክ የማርኬቲንግ እና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አባይነህ ሃብቴ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ባንኩ ከዚህ ቀደም ሲጠቀምበት የነበረው የመለያ ምልክት በቀላሉ ለመታወስ አስቸጋሪና ለመረዳትም ውስብስብ መሆኑን ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት በማረጋገጡ፤ ለአጠቃቀም ቀላል፣ ለመረዳት ግልፅ የሆነና በቀላሉ መታወስ የሚችል የመለያ አርማ እና ቀለም እንዲዘጋጅ መወሰኑን አባይነህ ተናግረዋል።

አዲሱን የባንኩን የንግድ መለያ ምልክት እና ቀለም ለመቀየር በጨረታ ከተወዳደሩ የብራንዲንግ ኩባንያዎች ውስጥ አሸናፊ የሆነው “ቤሪ አድቨርታይዚንግ” የመለያ ምልክቱን እና የቀለም ለውጡን ሥራ ያከናወነ ሲሆን፤ ኩባንያው የንግድ መለያ ምልክት እና የቀለም ዝግጅቱን ከብራንድ መመሪያ ሰነዱ ጋር አጠናቆ ለባንኩ አስረክቧል።

አዲሱ የንግድ መለያ ምልክት ከሶስት ምስሎች የተዋቀረ ሲሆን፤ እነርሱም የአይን፣ የአድማስ እና ክብ ቅርፅን የያዙ ምስሎች ናቸው።

በዚህም የመንቃትን፣ የአዲስ ቀን ጅማሮን እንዲሁም ብዙ ሆነን እንደ አንድ የምንሰባሰብበት ትርጉምን እንዲወክሉ ተደርገው መቀረቸውን የቤሪ አድቨርታይዚንግ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት መላኩ ባህሩ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

በተጨማሪም ቀለማቱን በተመለከተ መላኩ ሲያስረዱ፤ የቀይ ቀለም ዘር የሆነው ”ማሩን ሬድ“ እና የሰማያዊ ቀለም ዘር የሆነው “ኮርፖሬት ብሉ” የተባሉ ቀለማትን መጠቀማቸውን ገልጸው፤ ይህም የአላማ ጥንካሬ፣ ጥልቅ የማገልገል ፍላጎት፣ የሥራ መነሳሳትን እንዲሁም የምንጊዜን ታማኝነትን፣ ለዓላማ ቁርጠኝነትን እና በዕውቀት መስራትን ይወክላል ብለዋል።

ቡና ባንክ ከተመሰረት 12 ዓመታትን ያስቆተረ ሲሆን፤ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች፣ ከ14 ሺህ በላይ ባለአክሲዎኖች እንዲሁም ከ2 ሺህ 700 በላይ ሰራተኞችን በሥሩ አካቶ በመስራት ላይ ይገኛል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS

Twitter ➲ t.ly/mxA4n

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here