ሐሙስ መጋቢት 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በኤሌክትሪክ አስተላለፊ መስመር ላይ በተፈፀመ ሥርቆት ምክንያት ዳንግላ፣ዱርቤቴ፣መራዊ ፣ኮሶበር፣ግምጃ ቤት፣ቻግኒና በአካባያቸው ባሉ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰታወቀ።
በተፈፀመው ሥርቆት ምክንያት 4 የብረት ታወሮች መውደቃቸውንም ነው አገልግሎቱ ያስታወቀው።
ከባህር ዳር – ዳንግላ በሚሄድ 66KV የኤሌክትሪክ አስተላለፊ መስመር የብረት ታወር ላይ በተለምዶ ቆጥቆጥማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተፈፀመ ሥርቆትና ምሰሶዎች በመውደቃቸው ከዳንግላና ፓዌ ማከፋፈያ ጣቢያ ኤሌክትሪክ የሚያገኙ ከተሞች ኃይል ተቋርጦባቸዋል፡፡
የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞች የእንጨት ምሰሶዎችን በመቀየር አገልግሎቱን ወደነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ በመሆናቸው ደንበኞቻችን በትዕግስት እንዲጠብቁ ጠይቋል።
በብረት ታወሮችና በአጠቃላይ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ሥርቆት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባበሰ በመምጣቱ በአገልግሎት አሰጣጣ ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት መፈጠሩም ተገልጿል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኝ የፀጥታ አካል በአካባቢው የተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በንቃት እንዲጠብቅና ከዚሁ ጋር በተያያዘ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለሚመለከተው የፀጥታ አካልና ለተቋሙ እንዲጠቁም የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳስቧል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4na




