ሐሙስ መጋቢት 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ተቋሙን ሰውን ማዕከል ባደረገ መልኩ ለማሻሻል እያከናወነ ያለው ሥራ የሚደነቅ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት”የተቋም ግንባታ የለውጡ ሂደት ወሳኝ አካል ነው“ ብለዋል።
“ኤሌክትሮኒክ አገልግሎት የሚሰጥበትን ሥርዓት በመዘርጋት፣ ምቹ የሥራ ቦታን በመፍጠር፣ ሠራተኞች በተመጣጣኝ ዋጋ የምግብ አቅርቦት እንዲያገኙ በማስቻል፣ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የሕፃናት ማቆያ ማዕከላትን በማደራጀት እና ለጽዳት ሠራተኞች ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ መንገዶችን በማመቻቸት እና አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር ቅልጥፍናን የሚጨምሩ ሥራዎችን ከውነዋል።” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልፀዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር በተፈሪ ፍቅሬ የተመራ የልኡካን ቡድን በዛሬው ዕለት በጉምሩክ ኮሚሽን የተከናወኑ ሁለንተናዊ የለውጥ ሥራዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡
በጉብኝቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የአገልግሎቶች እና መልካም አስተዳደር ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አለምጸሐይ ጳውሎስ እና ሌሎች የጽ/ቤቱ አመራሮች ተገኝተውበታል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4na
















