ሐሙስ መጋቢት 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን የመመሪያ ጥሰት ፈጽመው በተገኙ ተጨማሪ ኹለት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የማስተካከያ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ የደረሱትን የኅብረተሰብ ጥቆማዎች መነሻ በማድረግ ባካሄደው ድንገተኛ ጉብኝት ተጨማሪ ኹለት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት /ካምፓሶች/ ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱን ገልጿል፡፡
በዚሁ መሰረት የእርምት እርምጃ የተወሰደባቸው የትምህርት ተቋማት ‘ሰቭን ስታር’ ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ /ደብረ ብርሃን ካምፓስ/ እና ‘ራዳ ኮሌጅ’ /ደብረሲና ካምፓስ/ መሆናቸውን የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን አስታውቋል።
ራዳ ኮሌጅ ቀደም ሲል እውቅና ሳይኖረው እራሱን ራዳ ዩንቨርሲቲ ኮሌጅ የሚል የደረጃ ስያሜ ተጠቅሞ በመገኘቱ የማስተካከያ እርምት እርምጃ ተወስዶበት እንደነበረ የገለጸው ባለስልጣኑ፤ በተጨማሪ በተደረገ ምርመራ ከመመሪያ ውጭ በደብረሲና ከተማ ከባለስልጣኑ የእውቅና ፈቃድ ሳይኖረው በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ ደረጃ ተማሪዎችን እየመዘገበ በመገኘቱ የእርምት እርምጃ ተወስዶበታል፡፡
በዚህም ራዳ ኮሌጅ በደብረሲና ከተማ በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ እስከ መጋቢት 7 ቀን 2017 እውቅና ፈቃድ እንዳይሰጠው ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡
በተመሳሳይ ሰቭን ስታር ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በደብረብርሃን ከተማ ከባለስልጣኑ የእውቅና ፈቃድ ሳይኖረው በቅድመ ምረቃ ደረጃ ተማሪዎችን እየመዘገበ በመሆኑ÷ ኮሌጁ በደብረብርሃን ከተማ የከፈተውን ካምፓስ በመዝጋትና የመዘገባቸውን ተማሪዎች በማሰናበት ለባለስልጣኑ በ10 ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርግ መወሰኑን ከትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም በደብረብርሃን ከተማ በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ እስከ መጋቢት 7 ቀን 2017 እውቅና ፈቃድ እንዳይሰጠው ባለስልጣኑ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን በቅርቡ ሰባት የትምህርት ተቋማትን በተለያዩ የአሰራር ግድፈቶች ምክንያት ማገዱ ይታወሳል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4na



