በኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድና ሕጉን መሠረት አድርገው ፍቃድ አግኝተው የሚሠሩ ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አሉ። የዛኑ ያህል በአንጻሩ በሕገ ወጥ መንገድ፣ በመንግሥት በኩል እውቅና ሳያገኙ፣ ተገቢውን ዓመታዊ የሥራ ግብር ለመንግሥት አካል ሳይገብሩ በሥራው የተሠማሩ በርካታ ድርጅቶች ይገኛሉ።
ዓለም ዐቀፍ ድንጋጌዎችም ሆኑ የኢትዮጵያ አሠሪና ሠራተኛ ሕግ፣ አሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ለሚሰጡት አገልግሎት ተገቢውን ጥቅም እና ገንዘብ እንዲያገኙ እንዲሁም ወደ እነርሱ ለሚቀርቡ ተገልጋዮችም ምቹ የሥራ ሁኔታ እንዲፈጥሩ ሲሉ ይደነግጋሉ። ነገር ግን በአዲስ አባባ ከተማ ብቻ እንኳ በየጊዜው ሥራ አጥተው ወይም የተሻለ ሥራ ፍለጋ በሚኳትኑ ዜጎች ላይ በእነዚሁ ኤጀንሲዎች የሚፈጸመው ማጭበርበር እና ስርቆት የተሞላበት ድርጊት እየተበራከተ መጥቷል።
ሥራ እናስቀጥራለን በማለት የመመዝገቢያ ገንዘብ የሚሰበስቡ፣ ከሥራ ቀጣሪዎች ጋር በሚደረግ ምስጢራዊ ውል ለራሳቸው ዳጎስ ያለ የኮሚሽን ክፍያ በየወሩ የሚቀበሉ እና ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጪ የተሰማሩ ኤጀንሲዎች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል። ጉዳዩም አሳሳቢ መሆኑን ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ሲያነሱ ይደመጣሉ። አብዛኛዎቹ በኤጀንሲዎች ተጭበርብረው ለአደጋ የሚጋለጡት ደግሞ ሴቶችና ወጣቶች ናቸው።
ይህ ሥራ ሕጋዊ መንገድ ቢዘረጋለትም፣ በሕጋዊነት ‹ሽፋን› ሕገወጥ ኤጀንሲዎች ትርፍ እያጋበሱበት እና የዜጎችን ሕይወትም አደጋ ላይ እየጣሉ ይገኛሉ። ይህም ሊገታ እንደሚገባው በርካታ ሥራ ፈላጊዎች ሲወተውቱ ይደመጣሉ።
ምን አሉ?
ምንም እንኳን ሕጉን ጥሰው የሚንቀሳቀሱ ኤጀንሲዎች ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ (በቀድሞው ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ) የሥራ ፈቃድ ወስደው እንደሚሠሩ ቢናገሩም፣ እውነቱና በተግባር የሚታየው ግን ሌላ ነው።
በተግባር እንደሚስተዋለው ከሆነ፣ ሥራ ፈላጊዎችን እና ሥራ ቀጣሪ ተቋማትን እናገናኛለን የሚሉት እነዚህ ኤጀንሲዎች በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ሕንፃዎች ላይ ቢሮ ይከራያሉ። በተለያዩ በከተማዋ ዕምብርት ቦታዎችም ‹የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ› በሚል የሐሰት ማኅተም ያረፈባቸው በራሪ ወረቀቶች ይለጠፋሉ።
ይህን ተከትሎ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያውን የተመለከቱ ሥራ ፈላጊ ዜጎች ኤጀንሲዎች በተከራዩባቸው ሕንፃ ቢሮ ተገኝተው ይመዘገባሉ። በዚህም ለአገልግሎት፣ ለአስተዳደር ወጭ እና ለሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮችን ምክንያት በማድረግ ከመቶ ብር ጀምሮ እስከ ስድስት መቶ ብር፣ አንዳንዴም ከዚያ በላይ ብር እንዲከፍሉ ይገደዳሉ።
ታድያ እነዚህ በሥራ ዕጦት በአካልም በመንፈስም የሚታገሉ ዜጎች፣ ለኤጀንሲዎች የሚከፍሉት ብር እንደወጣ መና መቅረቱና መበዝበዛቸው ብቻ አይደለም የሚያስገርመው። ይልቁንም ሥራ የሚያገኙበት ሒደት አለመመቻቸቱ፣ እንዲሁም ከአንድ እና ኹለት ሳምንት በኋላ ለኤጀንሲዎቹ ጥያቄ ሲያቀርቡ ያለአጥጋቢ መልስ አመናጭቀው የሚመልሷቸው መሆኑ ነው። ይህም ቅሬታ እንዲያነሱ ገፊ ምክንያት ሆኗል።
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገችው ሀብታም ዓለሙ (ሥሟ እንዳይጠቀስ በመጠየቋ ሥሟ የተቀየረ) የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናት። በበኩሏ የገጠማትን እና ያሳለፈችውን ስታስረዳ፣ ከሐዋሳ ዩኒቨርስቲ በ2011 ከሒሳብ ትምህርት ክፍል በመምህርነት ትምህርቷን ማጠናቀቋን በማውሳት ትጀምራለች። በኋላም በአዲስ አበባ ከተማ ሥራ እያፈላለገች በነበረችበት ወቅት መገናኛ አካባቢ በአንድ የመጀመሪያ ደረጃ የግል ትምህርት ቤት በቋሚ የሒሳብ መምህርነት ቅጥር ማታወቂያ እንደወጣ ትመለከታለች።
ይህ ማስታወቂያ በሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች በኩል የተለጠፈ ነው። ለሥራው ለመወዳደር መመዝገብ የሚፈልጉ ሥራ ፈላጊዎች ኻያ ኹለት አካባቢ በሚገኝ አንድ ትልቅ ሕንፃ ውስጥ አራተኛ ፎቅ ላይ ተገኝተው እንዲመዘገቡ እንደሚያሳስብ ታስታውሳለች።
እናም ሥራ ለማግኘት ከነበራት ጉጉትና ተስፋ የተነሳ እውነት ነው አይደለም የሚለውን ለመጠየቅ ጊዜ ሳትወስድ፣ በማግስቱ ኤጀንሲው በሚገኝበት ቢሮ ተገኝታ 600 ብር ከፍላ ትመዘገባለቸ። ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ ኤጀንሲው ቢሮ አቅንታ የሥራ ቅጥሩ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ብትጠይቅም የድርጅቱን ስልክ ቁጥር ሠጥተዋት፣ በሰባት ቀን ውስጥ ደውለው እንደሚያሳውቋት አስረድተዋት ከቢሮ ትወጣለች።
በተባለችው ጊዜ ወደ ኤጀንሲው ቢሮ ያቀናችው ሀብታም፣ ያኔ ግን ተቀብሎ የሚስተናግዳት እንኳ አልነበረም። ይብሱን ኤጀንሲው ተከራይቶ ከሚሠራበት ሕንፃ እንደለቀቀ እና በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም እንዳልተነሳላት ገልፃለች።
ሥራም ሳታገኝ፣ የከፈለችው 600 ብርም ሳይመለስላት የቀረችው ሀብታም፣ ከምታስተውለው በመነሳት ስትናገር በሕገ ወጥ ኤጀንሲዎች በኩል አሁንም ቢሆን ሥራና ሠራተኛን እናገኛለን በማለት የሚለጠፉ የውሸት ማስታወቂያዎች ከጊዜ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸውን ታነሳለች።
ሌላው በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ማለዳ አስተያየት የሰጠው ዘሪሁን ጌታቸው እንደሚለው፣ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች አማላይ ማስታወቂያዎችን በየቦታው በመለጠፍ በርካታ ወጣት ሥራ ፈላጊዎችን እየበዘበዙ ነው። እርሱም በበኩሉ እንደ ሀብታም ሁሉ የዚህ ዕጣ ፈንታ ተቋዳሽ ነበርኩ ባይ ነው።
ዘሪሁን አያይዞም በእነዚህ ኤጀንሲዎች የሚወጡና የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ዳጎስ ያለ የደሞዝ መጠን ዝርዝር ስለሚያርፍባቸው እውነት እየመሰላቸው በርካታ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች ወደ ቢሮዎቻቸው እንደሚያቀኑና ለምዝበራ እንደሚዳረጉ ይናገራል።
ኤጀንሲዎች በምዝገባ ወቅት በኮሚሽን እና በሥልጠና ሥም ገንዘብ ከመቀበላቸው ጎን ለጎን፣ ሥራ አለማስቀጠራቸው እና የወሰዱትን ገንዘብ ባለመመለሳቸው ሥራ ፈላጊ ሰዎች ለከፍተኛ ምዝበራ እየተዳረጉ ነውና መንግሥት ተገቢውን ቁጥጥር እና ዕርምጃ እንዲወስድ ብላል።
ሕግ ወዴት ነው?
ጥጋቡ ደሳለኝ የሕግ ባለሙያ ናቸው። በበኩላቸው ሥራና ሠራተኛ እናገናኛለን በማለት ሥራ የሚፈልጉ ሰዎችን ገንዘብ የሚበዘብዙ ሕገ ወጥ ኤጀንሲዎች እንዳሉ መታዘባቸውንና ይህንንም ራሱን እንደቻለ የገቢ ማግኛ ወይም መተዳደሪያ እንዳደረጉት አስረድተዋል።
ይህ ተግባር ከሕግ አንፃር ወንጀል መሆኑን ኹሉም አካላት የሚያውቁት ሐቅ መሆኑን ያነሱት ጥጋቡ፣ ወንጀሉን የሚፈፅሙ ኤጀንሲዎችን ተከታትሎ ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድና ማስተማር ያለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መሆኑን ሊያውቅና ሊገነዘብ ይገባል ባይ ናቸው።
ሕጉ ላይ በተቀመጠው ዐዋጅ መሠረት ማናቸውም ሥራና ሠራተኛ የሚያገናኙ ድርጅቾች ከግለሰቦች ጥቅማ ጥቅም መቀበል ያለባቸው ቅጥሩ እንደሚፈፀም ካረጋገጡ በኋላ ነው። በአንጻሩ በሕገ ወጥ ተቋማት በኩል ሲመዘገቡ የሚታዩ ሥራ ፈላጊዎች አብዛኛውን ጊዜ ገንዘባቸውን በቅድሚያ ፈሰስ እንደሚያደረጉ ጠቅሰዋል። ከዛም ውጪ ከሥራ ቀጣሪዎች ጋር የሚገናኙበት ዕድል ጠባብ መሆኑን አስተውያለሁ ይላሉ።
ኤጀንሲዎች ‹የአድራሻ ለውጥ ስለምናደርግ በሕግ የመጠየቅ ዕድላችን ጠባብ ነው› በሚል ዕሳቤ፣ ሥራና ሠራተኛን ከማገናኘታቸው ቀድመው የአገልግሎት ወይንም የኮሚሽን ክፍያ በሚል በማግባባትና በማጭበርበር የአገልግሎት ቅድመ ክፍያ ወይም ኮሚሽን መቀበል በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑ እንደማያጠያይቅ ጥጋቡ ያረጋግጣሉ። በሌላ በኩል እነዚህ ኤጀንሲዎች ቀድመው መቀበል ያለባቸው የሥራ ፈላጊዎችን ማንነት የሚገልጽ መታወቂያ፣ ፎቶግራፍ፣ የትምህርት ማስረጃዎችን እናሌሎች ተያያዥ ማስረጃዎችን ብቻ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
ይህ እንዳለ ሆኖ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ፈቃድ የሌላቸውንም ሆነ፣ ፍቃድ ኖሯቸው በከተማዋ በሕገ ወጥ መንገድ በሥራና ሠራተኛ አገናኝ መስክ ላይ ተሠማርተው የሚገኙትን አጥንቶና ተከታትሎ ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድና በሕግ ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
ጥጋቡ አክለውም፣ ቢሮው በተጨማሪ ፈቃድ የተሠጣቸው ድርጅቶች ምን ያህል ሥራ ፈላጊዎችን መዝግበዋል፣ ምን ያህል ተመዝጋቢዎችንስ ከሥራ ቀጣሪ ተቋማት ጋር አገናኝተዋል የሚለውን መረጃ በተግባር አፈፃፀም ላይ ተደግፎ ተከታትሎ በየወቅቱ ለኅብረተሰቡ የማሳወቅ ግደታ አለበት ባይ ናቸው።
ሕጋዊ ፈቃድ እንዳላቸው የሚናገሩ ኤጀንሲዎችም 50 በመቶ እንኳን ሕጉን አክብረው እየሠሩ ነው ለማለት እንደሚቸገሩም አያይዘው ገልፀዋል። በእነዚህ ኤጀንሲዎች ላይ ቢሮው ከባለድርሻ ተቋማት ጋር ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ አገልግሎታቸውን በየወቅቱ በመፈተሽ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ በመውሰድ አደብ እንዲይዙ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ማስፋፊያ ዳይሬክተር ጥላየ አለማየሁ ለአዲስ ማለዳ እንዳረጋገጡት፣ ከገቢዎችና ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ነገር ግን ሕጉን ጥሰው በሥራና ሠራተኛ አገናኝ ላይ ተሠማርተው የሚሠሩ እና ሥራ ፈላጊዎችን የሚበዘብዙ አካላት አሉ።
‹‹በትንሹ ከሰባት መቶ ያላነሱ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ‹ኤጀንሲዎች› ያሉ ሲሆን፣ ቢሮው አጥጋቢ ለማለት ባያስደፍርም የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ከመሥራት ግን ወደኋላ አላለም›› ብለዋል። ሆኖም ይህን ሕገ ወጥ አሠራር ሙሉ ለሙሉ ማፅዳት ያልተቻለው ችግሮች ካለመጥራታቸው በተጨማሪ ጉዳዩ ጆሮ ዳባ ልበስ እየተባለ ስለመጣ መሆኑን ቢሮው እንደማይሸሽግ ገልፀዋል።
ዳይሬክተሩ በተጨማሪ ከቢሮው ባለፈ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ለመቆጣጠር ከተፈለገ በፌዴራል የሥራ ኢንተርፕራይዝና ልማት ቢሮ በኩል በሥራና ሠራተኛ አገናኝ ዘርፍ ላይ ተሠማርተው የሚገኙ ኤጀንሲዎች የሙያ ፍቃድ ማረጋገጫ የሚወስዱበትን ተገቢውን አካሄድ የሚፈትሽ የአሠራር ሒደት ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል።
በክፍለ ከተማና በወረዳ በኩል ከሥራ ፈላጊዎች በተደጋጋሚ የሚመጡ ቅሬታዎች አሁንም ያሉ ሲሆን፣ በመረጃ በተደገፈ መልኩ አቤቱታዎችን ተንተርሶ ዕርምጃ እንደሚወሰዱ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
በእርግጥ በሥመ ሥራ ማስቀጠር በደል የሚፈጽሙ ኤጀንሲዎችን ሕገወጥ ተግባር ለመቆጣጠር የተጀመሩ ክትትሎች ለነገ የሚተዉ አይደሉም። ሥራና ሠራተኛ በማገናኘት በአስቀጣሪ ኤጀንሲ ሥም በሕገወጥነት ብር የሚያጋብሱ አካላትንም በፍጥነት ማስቆም ያሻል። በመገናኛ፣ በአራት ኪሎ አካባቢ በሚገኙ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች፣ በቆርቆሮ አጥሮች፣ የብሎኬት ግንቦች ላይ በመለጠፍ እና በተለያዩ አውራ መንገዶች በመንቀሳቀስ ሥራ ታገኛላችሁ የሚሉ አማላይ የሐሰት ወሬዎችን በመንዛት እና በማሰራጨት ገንዘብ ሰብስበው እብስ የሚሉ፣ ሌብነትን የሚያስፋፉ ኤጀንሲዎች ላይ የሚታዩ የቁጥጥር ቸልተኝነት ሊታሰብበት ይገባል።
ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014



