ከመንግሥት ተቋማት ለድጋፍ የሚወጡ ገንዘቦች ምን ያህል ለታለመላቸው ዓላማ ይውላሉ?

0
1100

በኢትዮጵያ እየጨመረ በመጣው ሠው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግር ምክንያት ድጋፍ የሚፈልጉ አካላት በጣም በርካታ ናቸው። በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ተቋማትን ለመጠገን፣ እንዲሁም በድርቅና በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ጨምሮ አስቸኳይ ዕርዳታ የሚሹ ሠዎች በየክልሎች በርካታ ናቸው።

ይህም አሁን የተከሠተ ሳይሆን፣ ድርቅ እና ጦርነት በሚፈራረቅባት ኢትዮጵያ በትንሹ ከ50 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነው። ከንጉሠ ነገሥቱ የሥልጣን ማብቂያ ገደማ ጀምሮ በደርግ ዘመነ መንግሥት ተከስቶ በነበረው ጦርነትና ድርቅ፣ የመንግሥትን ድጋፍ የሚሹ ወገኖች በርካታ እንደነበሩ መረጃዎች ይመሠክራሉ።

በኋላም ከ1983 ጀምሮ እስካሁን በየቦታው በሚከሠት ግጭት እና ድርቅ፣ እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የመንግሥትና የለጋሽ አካላትን እጅ የሚጠብቀዉ ዜጋ ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።

ለዚህ ማለቂያ ለሌለው የኢትዮጵያ ችግር እና የዜጎች ሠቆቃ የተለያዩ የውጭ አገራት፣ መንግሥታዊ የሆኑና መንግሥታዊ ያልሆኑ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች፣ አገር በቀል ረጂ ተቋማት፣ የውጭ መንግሥታት፣ በጥቅሉም የተለያዩ አካላት በየደረጃወና በየጊዜው መጠነ ሠፊ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ይስተዋላል። የኢትዮጵያ መንግሥትም ድጋፍ ለሚሹ አካላት በሚል ከመንግሥት ካዘና ገንዘብ እንደሚያወጣ ይታወቃል። ከዚያም አልፎ ክልሎች ችግር በሚያጋጥማቸው ወቅት አንዱ ለሌላው ድጋፍ ሲሠጣጡ ይታያል።

እንደማሳያም የኦሮሚያ ክልል በአማራ ክልል በጦርነት ለተጎዱት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ፣ የአማራ ክልል መንግሥትም ለሱማሊና ኦሮሚያ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ካለው በጀት ላይ ለአማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር እና ሱማሊ ክልሎችና ለሌሎችም በየጊዜው ድጋፍ ሲያደርግ ይስተዋላል። የፌደራልና የክልል ተቋማትም እንዲሁ የአቅማቸውን ሲለግሱ ይታያል።

ሆኖም ይህ ኹሉ የሚቀርብ ድጋፍ በትክክል የታለመለት ዓላማ ላይ ስለመዋሉ የሚነገር ነገር አለመኖሩ በሕዝብ ዘንድ ጥርጣሬ የሚፈጥር ስለመሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይነገራል።

ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከአንዱ ወደ አንዱ በዕርዳታና ድጋፍ ሥም የሚሰጣጡት ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ ለሕዝብ ይፋ አለመደረጉም፣ ሕዝቡ በችግር ጊዜ መረዳዳቱን ሳይሆን፣ ነገሩን ትልቅ የሙስና በር እንደሆነ አድርጎ እንዲያየው አድርጎታል ነው የሚባለው።
በዚህ ዓመት የኦሮሚያ ክልል መንግሥት 100 ሚሊዮን ብር ለአማራ ክልል ድጋፍ ካደረገ፣ በቀጣይ ደግሞ የአማራ ክልል መንግሥት ድጋፍ በሚል ለኦሮሚያ መልሶ በተመሳሳይ መንገድ ገንዘብ በመስጠት የማይፈተሽና የማይመረመር ወጪና ገቢዎች እንዲበራከቱ ይደረጋል በማለት ሐሳባቸውን የሚገልጹ አሉ።

አንዱ ክልል ለሌላው ድጋፍ ሲያደርግ የክልል ርዕሳነ-መስተዳደሮች በቴሌቪዥን ድጋፉን ሲረካከቡ ከማየት ባለፈ፣ ማን እንደሚቀበለውና በምን መልኩ ድጋፉ እንደሚሠራጭ፣ ብሎም የተገኘው ድጋፍ ኦዲት ይደረግ ወይም አይደረግ የሚለው ለበርካቶች ግልጽ አይደለም።
በየጊዜው የሚገኘው ድጋፍም ዞሮ ዞሮ የአገሪቱን በጀት ለኪስ ከማዋል የዘለለ፣ የተረጅዎችን ፍላጎት ሲቀንስም ሆነ ልማትን ሲያጧጡፍ አይስተዋልም በማለት በአገሪቱ ካለው ችግር ግዝፈት እኩል ይህንንም የሚያነሱ ሞልተዋል።

በዚህም የተነሳ ለመከላከያ እና በጦርነቱ ጉዳት ላጋጠማቸው ወገኖች ድጋፍ በሚል የወር ደሞዛቸው የተቆረጠባቸው የመንግሥት ሠራተኞች ገንዘባችን ይመለስልን የሚል ሐሳብ ሲያራምዱም ይስተዋላል። ይህም ሐሳብ የተፈጠረው ከደሞዝ ላይ የተቆረጠው ገንዘብ ለመከላከያ እና ለተጎዱት ወገኖች ውሏል የሚል ዕምነት ከማጣት የመነጨ እንደሆነ ይናገራሉ። በቅርቡ የአማራ ክልል የብልጽግና አመራሮች እስከ 100 ሚሊዮን የሚደርስ ገንዘብ በይፋ መመዝበራቸው መጋለጡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው ሌብነት ምን ያህል ሥር እንደሠደደ ማሳያ እንደሆነ በርካቶች ሲቀባበሉት ሠንብተዋል።

በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ፣ ለመከላከያ እና በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች በሚል በየራሳቸው መንገድ ከሕዝብ ገንዘብ ሲሰበስቡ የነበሩ በርካቶች መሆናቸውም የሚዘነጋ አይደለም። ይኼ በራሱ የመንግሥት አካላት ችግሮችን እንደመጠቀሚያ ማድረጋቸውን ተከትሎ ተቆጣጣሪ አካል ባለመኖሩ የተፈጠረ እንደሆነ ይታመናል።

የአማራ ክልል የሒሳብ ባለሙያዎቸና ኦዲተሮች ማኅበር ውስጥ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ሐሳብ፣ በክልሉ ለሚያስፈልጉ ድጋፎች ከተለያዩ አካላት የሚሰበሰበው ድጋፍ የሚታመኑ ሠዎች እንዲካተቱበት፣ ኦዲት የሚደረግ ግልጸኝነት ያለው አሠራር እንዲሠፍን ሕዝቡ በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡን ገልጸዋል።

ወረራ በተከሠተ በመጀመሪያው ሠሞን የሚሰበሰበውን ድጋፍም የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ይቀበል እንደነበር አንስተው፣ በኋላ ግን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለወቅታዊ ሠላምና ደኅንነት ማስከበር የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ የሚባል ተቋቁሞ፣ በአራት ባንኮች የገቢ ማሰባሰቢያ የባንክ ሒሳብ ቁጥር ተከፍቶ በዚያ ገንዘብ ሲሰበሰብ መቆየቱን አመላክተዋል።

ሆኖም፣ ገንዘቡ ከተሰበሰበ በኋላ የታለመለት ዓላማ ላይ ውሏል የሚለውን ግን ማወቅና መገመት አስቸጋሪ እንደሆነ ነው ያነሱት። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ከኮሮና ቫይረስ መከሠት ጀምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገራት በርካታ ገንዘብ ድጋፍ ሲደረግላት መቆየቱን አንስተው፣ ይህም አለመታወቁ ግልጽኝነቱ ላይ ትልቅ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ገልጸዋል።

በተለይም በክልሉ ደረሰ የተባለው ጥፋት፣ የተሰበሰበው ገንዘብና ገንዘቡ ለሚገባቸው አካላት በትክክል ውሏል ወይ የሚለው ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው ያሉት ግለሰቡ፣ ከየማኅበረሰቡ የተሰበሰበውን ድጋፍ ለመከላከያና ለተጎጂዎች ለማድረስ ግንባር በሔድንበት ጊዜም ኃላፊነት ወስዶ ደረሰኝ የሚቆርጥ አካል አላገኘንም ይላሉ።

አክለውም፣ ድጋፉ ለሚያስፈልጋቸው አካላት ድጋፉ መድረሱን በየራሳችን መንገድ ነበር የምናረጋግጠው ሲሉ ገልጸው፣ ስለተደረገው ድጋፍ መገናኛ ብዙኃን ከሚናገሩት ውጭ መረጃዎችን በሠነድ ማግኘት እንደማይቻል ያስረዳሉ።

በጦርነቱ ወቅት ከፍተኛ ገንዘብና ሎጅስቲክስ ሲያቀርብ የነበረው የንግዱ ማኅበረሰብ ነው፤ አሁንም ቢሆን ዞሮ በግብር እየተሳቀቀ ነው የሚል ሐሳባቸውን ሠንዝረው፣ በጥቅሉ በዚህ ዙሪያ ከሚሰበሰበው ሃብትና ሥርጭቱ ላይ ግልጸኝነት እንደሚጎድል አጽንዖት ሠጥተው ተናግረዋል።

የአማራ ብሔራዊ ክልል ዋና ኦዲተር ቢሮ የኦዲት አረጋጋጭ ደሳለኝ ነጋ በበኩላቸው፣ ወቅታዊ ኹኔታዎችን ተጠቅመው ጥቅማቸውን የሚያስከብሩ እና በግዥ ወቅት ጥራት የሌላቸው ግዥዎችን የሚፈጽሙ አካላት መኖራቸውን ጠቁመው፣ በተለይም እየቀረቡ ያሉ ድጋፎችን አስመልክቶ ከግልጸኝነት አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን አልደበቁም።

በዚህም፣ ከተሰበሰቡ ድጋፎች የጠፉ ንብረቶች አሉ ያሉት ኦዲተሩ፣ በድጋፍ መልክ መጥተውና ደረሰኝ ተቆርጦላቸው ወደ ተጠቃሚው ያልተላለፉ ንብረቶች መኖራቸውን እና ንብረት ክፍል ውስጥ ሲፈለጉ የማይገኙ ዕቃዎች እንዳሉም ጭምር ነው ያነሱት።
በዚህ ጊዜ የኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ድርሻ የኦዲት ግኝቱን በሪፖርት ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከእኛ ጋር የሕግ አካል ባለመኖሩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት ግን ትኩረት ሠጥተው በመሥራት ጥፋተኛውን ተጠያቂ ማድረግ ይኖርባቸዋል የሚል ሐሳብ ሠንዝረዋል።

ከዚህ አንጻር ክፍተት እንዳለ ያነሱት የኦዲት ባለሙያው፣ እንደ ሕንድና ብራዚል ያሉ አገራት የሚከተሉት የኦዲት አሠራር ሞዴል ከእኛ አገር የተለየ ነው፣ በራሳቸው ባለሙያ ኦዲት አስደርገው ጥፋት ካገኙ በራሳቸው ዐቃቤ ሕግ ክስ መሥርተው በራሳቸው ዳኞች ብይን ይሰጣሉ ይላሉ። እኛ እዚህ ደረጃ ባለመድረሳችን እና ተጠሪነታችን ለክልል ምክር ቤት በመሆኑ በተገኙ የኦዲት ግኝቶች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር የላላ አድርጎታል ባይ ናቸው።

አሁን ባለው አሠራር በተገኙ የኦዲት ግኝቶች ላይ መልስ ተሠጥቷል አልተሰጠም የሚለውን በየዓመቱ ከምክር ቤት እንጠይቃለን። ከዚህ በዘለለ ግን መልስ መሰጠት አለበት ብለን የማስገደድ አቅም የለንም ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም፣ የአምስትዮሽ ሥምምነት በሚባል አሠራር ፍትሕ ቢሮ፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት፣ ጸረ ሙስና እና ዋና ኦዲተር ቢሮ ከክልል ምክር ቤት ጋር በጋራ ሆነው፣ በተገኙ የኦዲት ሪፖርቶች ላይ ምላሽ የማይሠጡ አመራሮችን ከሥልጣን ማንሳት ብሎም በሕግ ተጠያቂ ማድረግ የሚል መግባቢያ ሠነድ ላይ መቀመጡን አንስተዋል።

ይህ አካሄድ አንድ ወረዳ ላይ ተግባራዊ የተደረገ ቢሆንም፣ ተጠናክሮ መሔድ ግን አልቻለም ሲሉ ነው የገለጹት።

በክልሉ የተከሰተውን አደጋ ተከትሎ ለድጋፍ የሚመጣን ማንኛውም ገንዘብ አደጋ መከላከል ጽሕፈት ቤት ደረሰኝ ይቆረጥና ገንዘቡ ወደ ክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ እንደሚገባ አመላክተው፣ በዓመቱ መጨረሻ ላይ በሚደረገው ኦዲት ምርመራ ኹለቱም ተቋማት ኦዲት ሲደረጉ በድጋፍ የተገኘው ገንዘብ የኦዲቱ አንድ አካል ነው ብለዋል።

ነገር ግን፣ የሃብት ምዝበራና ብልሹ አሠራር ያለ ከመሰለንና ችግሮች እንዳሉ ካወቅን፣ የተሳሳተ መረጃ እንዳይሠራ ለማድረግና ሃብትን ከምዝበራ ለመታደግ ቅድመ ኦዲት ምርመራ ማካሔድ እንችላለን ነው ያሉት።

የተጠቃለለ ፈንድ ኦዲት በሚባለው እና በዓመቱ በሚደረገው የኦዲት ሥራም፣ በዓመቱ ያልጸደቀ በጀት ምን ያህል ነው? ከዚህም በጀት ለዞንና ለወረዳ የሚመደብ በጀት በመኖሩ ሕግና ሥርዓትን የተከተለ ዝውውር መካሔዱ፣ እንዲሁም ግዥዎች በአግባቡ ተሠርቷል ወይ የሚለው በኦዲት ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል።

በአጠቃላይ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቋማት የሚሠሩቱን ሥራ በተገቢው ኹኔታ የሚቆጣጠር፣ ብሎም የሚያወጧቸውን ሪፖርቶች ተዓማኒነት እና ትክክለኛነት የሚያጣራና መዛነፍ ሲኖር ተጠያቂ የሚያደርግ ብቁ አሠራርና በቂ ባለሙያ ወይም አካል አለመኖሩ፣ ተቋማቱ እንደፈለጉ የሕዝብ ሃብት እንዲመዘብሩ በር ከፍቶላቸዋል ነው የሚባለው።

ተቋማትም ቢሆኑ በየጊዜው ሥማቸው ሲቀየር፣ ሲፈርሱና ሲሠሩ መኖራቸው፣ ከሠሩት መልካም ሥራ ይልቅ ያጠፉት ጎልቶ የሚታይ ሲሆን፣ በየጊዜው ተቋማትን የሚፈርሱት ለዝርፊያ በሚያመች መልኩ ለማቋቋም ነው የሚሉ አይጠፉም። ትችት አቅራቢዎችም እንደማሳያ ብለው የፌደራሉ ጸረ ሙስና ተቋም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መሆኑ፣ በተቋማት እና በአሠራራቸው ላይ ግልጸኝነትና ቁጥጥር ላለመኖሩ ግልጽ ማሳያ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

ለዚህ ዘገባ አዲስ ማለዳ ከአማራ ብሔራዊ ክልል ዋና ኦዲተር ቢሮ ካገኘችው መረጃ በተጨማሪ፣ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ዋና ኦዲት ቢሮ መረጃ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here