ፍርድ ቤቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የመከላከያ ምስክርነት በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ እንዲሰማ ብይን ሰጠ
ሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የመከላከያ ምስክርት በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ እንዲሰማ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ብይን ሰጥቷል።
ችሎቱ ባሳለፍነው መጋቢት 8 ቀን 2014 በነበረው ቀጠሮ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ለነ ለሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው የእርሻ መሳሪያና የመርከብ ግዢ የሙስና ክስ ላይ በመከላከያ ምስክርነት በተደጋጋሚ አለመቅረባቸውን ተከትሎ፤ ታስረው እንዲቀቡ በፍርድ ቤቱ የታዘዘው ትዕዛዝ ላይ መጥሪያውን ፈርሜ ባልተቀበልኩበት ሁኔታ ታስሬ እንድቀርብ መታዘዙ አግባብ አደለም ሲሉ የእስር ትዛዙ ተነስቶ ባሉበት ቦታ በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ ጥያቄ ለመመለስ እንዲፈቀድላቸው በደብዳቤ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ሀይለማርያም ባሉበት ቦታ በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ ቢሰሙ እንደማይቃወሙ የሜ/ጀ ክንፈ ጠበቃውም ሆነ ከሳሽ ዓቃቢህግ አስተያየት ሰተው ነበር።
ፍርድ ቤቱም መርምሮ በቨርቹዋል ይሰማ ወይስ አይሰማ የሚለውን ብይን ለመስጠት ለዛሬ በሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት የሀይለማርያም ደሳለኝ ተወካይ በተገኙበት የመከላከያ ምስክርነታቸው በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ እንዲሰማ ብይን ሰጥቷል።
መከላከያ ምስክርነታቸው መቼ ይሰማል የሚለው ቀጠሮን በተመለከተ ግን ከየቴክኖሎጂው መሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ከፍርድ ቤቱ አስተዳደር ጋር ተነጋግሮ ቀጠሮውን እንደሚያሳውቅ ችሎቱ መግለፁን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።
በሌሎች የመከላከያ ምስክሮች አቀራረብን በተመለከተ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት በመግለጽ ለመጋቢት 14ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n





