ድርቅ የተከሰተባቸው ክልሎች ሰቆቃና ተስፋ

0
1169

ከአራት ዐሥርት ዓመታት በኋላ ለከፋ ድርቅ የተጋለጡት ደቡብ፣ ኦሮሚያና ሱማሌ ክልልን ጨምሮ፣ በደቡባዊ ምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍል ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶች ላይ እየደረሰ ያለው የርሀብ አደጋ አድማሱን አስፋፍቶ ቀጥሏል።
በኦሮሚያ፣ አፋር እና ሱማሌ ክልል ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ባጋጠመው የዝናብ ዕጥረት ሳቢያ በተከሰተው ድርቅ በርካታ እንስሳት ሞተዋል፤ ሰብሎች ወድመዋል፤ የውኃና የምግብ ዕጥረት ተከስቷል፤ በርካታ ዜጎችም ተፈናቅለዋል፤ እየተፈናቀሉም ይገኛሉ።
በነዚህ አከባቢዎች በተከሰተው ድርቅ፣ ሚሊዮኖች መተዳደሪያቸውን እና ከብቶቻቸውን በማጣታቸው ሕፃናት እና ቤተሰቦቻቸው በሕይወት ለመትረፍ እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ።
7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ በርካቶችም ቀያቸውን ትተው እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴም በደቡበ ምሥራቅ ኢትዮጵያና በሱማሊያ ያሉ ሰዎች በአርባ ዓመት ውስጥ ከታዩት የከፋ ድርቅ እንዳጋጠማቸው እና ድርቁም በእነዚህ አካካቢዎች ለሰብዓዊ ቀውስ መባባስ ምክንያት መሆኑንም በቅርብ ጊዜ ባደረገው ግምገማ መመልከቱን በሪፖርቱ አስታውቋል።

በተጨማሪ፣ ከአንድ ወር በፊት ባወጣው መረጃ መሠረት በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ የተከሰተው ድርቅ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የቁም እንስሳትን እንደገደለ እና በርካቶችንም ለምግብ ዕጥረት እንዳጋለጠ ያስታወቀው ደግሞ ፋኦ ነው።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም እንዲሁ በቀጠናው የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ከላይ የተጠቀሰውን ቁጥር የሚያክሉ የቁም እንስሳት መሞታቸውን እንዳረጋገጠ በመጥቀስ፣ የተጋረጠውን የድርቅ አደጋ ለመቀልበስ ያለው ተስፋ ደግሞ የተመናመነ ነው ብሏል።
ድርቁን ተከትሎ፣ በሱማሌ ክልል ከዚህ በፊት ከነበሩት ዓመታት የአልሚ ምግብ አቅርቦት ወደ 58 በመቶ፣ እንዲሁም በኬንያ ወደ 70 በመቶ ዝቅ ማለቱ ተጠቅሷል።

በተያዘው ወር ደግሞ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ለሚገኙ ለቀጠናው አገራት የምግብ ድጋፍ ለማቅረብ 130 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ድርቁ ተባብሶ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ መጪው ጊዜ ለቀጠናው አስከፊ እንደሚሆን ፋኦ አውስቷል።

የግብርና ሥራዎችን መሥራት አለመቻል ለምግብ ዕጥረቱ መባባስና በርካቶችም ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል ያለው ድርጅቱ፣ በቀጠናው ሊደርስ የሚችለውን የሰብዓዊ ቀውስ ለመግታት አስቸኳይ ድጋፎች እንደሚያስፈልጉ ነው የተናገረው።
በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡ ሳቢያ ድርቁ መቀጠሉንም ነው ድርጅቱ ያስታወቀው። በዚህም ሳቢያ የእርሻ ሥራ ቆሟል፤ የቀንድ ከብቶችም እየሞቱ ነው ያለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በኢትዮጵያ ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ የሚገኙ 13 ሚሊየን ሰዎች ለረሃብ ሊጋለጡ ተቃርበዋልም ብሏል።

በእነዚህ አገራት በአስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፎች ካልተደረጉ የሚደርሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ማስቆም አዳጋች እንደሚሆንም አሳስቧል።

በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ የሚሆን 327 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልገውም ነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያስታወቀው። ገንዘቡም በአጭር ጊዜ ምግብ እና ጥሬ ገንዘብ ለተጎጂዎች ለማቅረብ፣ እንዲሁም በረጅም ጊዜ ደግሞ ከአየር ፀባይ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ለድርቅ የተጋለጡ አካባቢዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚውል ነው ብሏል።

የዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ በድርቅ በተጠቁ የኦሮሚያ እና የሱማሌ ክልሎች ውስጥ በተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት የተጎዱ ከ 225 ሺሕ በላይ ሕፃናት እና ከ100 ሺሕ የሚልቁ ነፍሰ-ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች አስቸኳይ የተመጣጠነ ምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁሟል። ድርቅ በተከሰተባቸው በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች 4.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለከፋ የውኃ ዕጥረት ተጋልጠዋልም ብሏል።

በተለይም የንጹህ መጠጥ ውኃ አለመኖር የሕፃናት እና የሴቶችን ሁኔታ ይበልጥ እያባባሰው እንደሚገኝ ተነግሯል። ሕፃናት የተበከለ ውኃ እንዲጠጡ ከተገደዱ፣ ከአምስት ዓመት በታች ባሉ ሕፃናት ዘንድ ዋነኛ የሞት ምክንያት ለሚሆነው ለተቅማጥና ሌሎች ውኃ ወለድ በሽታዎች የሚጋለጡበት ዕድል ሰፊ መሆኑ ተጠቁሟል።

በኦሮሚያ፣ አፋር እና ሱማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ አሁን ላይ አዙሪቱን ወደ አማራ ክልል ማስፋቱ ተነግራል። በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን በሚገኙ አራት ወረዳዎች፣ በክረምት ወቅት በቂ ዝናብ ባለመዝነቡ እና በአከባቢው በነበረው ጦርነት ምክንያት በወረዳው የሚገኙ አርሶ አደሮች ሰብላቸውን መሰብሰብ ባለመቻላቸውም ርሃብ መከሠቱ ተገልጿል።

በዞኑ የሚገኙ አራት ወረዳዎች በድርቅ መጎዳታቸውንና ማኅበረሰቡ ርሃብ ላይ መሆኑን የዋግ ኽምራ ዞን ብሔረሰብ አስተዳደር የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ከፍያለው ደባሽ አስረድተዋል።

ዝቋላ፣ ሳህላ፣ ፃግብጅ እና አበርገሌ የተሠኙ በዞኑ የሚገኙ ወረዳዎች ድርቅ የነበረባቸው መሆኑን ያነሱት ከፍያለው፣ በወረዳዎቹ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለተፈናቃይ ዜጎች መርዳት ይቅርና ለራሳቸውም የመሠረታዊ ፍላጎት ችግር ተጋርጦባቸዋል ብለዋል።
አራቱ ወረዳዎች በክረምት ወቅት በቂ ዝናብ አለማግኘታቸውና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በሠነዘረው ጥቃት የአካባቢው አርሶ አደሮች ሰብላቸውን መሰብስብ አለመቻላቸው ለርሃቡ መከሠት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ኃላፊው ጨምረው አብራርተዋል።

በአካባቢው የዝናብ ዕጥረት ነበር ያሉት ከፍያለው፣ ከዚህም በተጨማሪ ሕወሓት በሚሠነዝረው ጥቃት አርሶ አደሩ ምሽግ ውስጥ ስለነበር አንድም ጣሳ እህል ቤታቸው አልገባም ሲሉ ነው ያስረዱት።
ከፍያለው አክለውም፣ የድርቁ መከሠት እንደ አንድ ችግር ሆኖ ሳለ በአካባቢው ሠፍኖ የነበረው ሠላም በመደፍረሱ አርሶ አደሩ ከድርቅ ያመለጠውን ሰብል እንኳን መሰብሰብ አለመቻሉ እና አሁንም ድረስ ጦርነቱ አለመቋጨቱን ተከትሎ
የተፈናቃዮች መበራከት ለርሃቡ መከሠት ድርብርብ ምክንያት መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

አያይዘውም፣ በአካባቢው የተከሠተው ርሃብ ከዞኑ ተሻግሮ ከክልሉ አቅም በላይ ስለሆነ፣ የፌደራል መንግሥትን ርብርብ ይሻል ብለዋል። መንግሥት ጣልቃ መግባት ብቻ ሳይሆን ወደ አከባቢው በማቅናት መጎብኘትና አስፈላጊ ተግባራትን ማከናወን አለበት ባይ ናቸው።
በሌላ በኩል፣ በአካባቢው ያለው የፀጥታ ችግር መጥራት ባለመቻሉ የአካባቢው ነዋሪ በሥጋት እና በርሃብ እየተጎዳ ነው ያሉት ኃላፊው፣ የሕወሓት ታጣቂዎች አሁንም ድረስ የሥጋት ምንጭ በመሆናቸው ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት አዳጋች አድርጎታል።

ኃላፊው በመጨረሻ፣ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ሰብዓዊ ድርጅቶች በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን እንዲታደጉ ጠይቀዋል። ድርቅ በተከሰተባቸው ዝቋላ እና አበርገሌ ወረዳዎች ጤፍ፣ ማሽላ፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ እንዲሁም ፃግብጅ ወረዳ ጤፍ፣ ገብስ፣ ስንዴ እና ሌሎች ጥራጥሬዎችን በማምረት እንደሚታወቁ ጠቁመዋል።

በሱማሌ ክልል በተከሰተው ድርቅ እስካሁን በአካባቢው ዝናብ ባለመኖሩ ከፍተኛ የሆነ የቤት እንስሳት ሞት መኖሩን የተናገሩት የሱማሌ ብሔራዊ ክልል አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን ኃላፊ በሽር አረብ ናቸው።
በክልሉ ከአንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺሕ በላይ የቤት እንስሳት ማለቃቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ የድርቁ ሁኔታ ምንም ዓይነት መሻሻል እያሳየ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

እስከ መጋቢት 8 ቀን 2014 ባለው ወቅት ብቻ 57 ሺሕ ከብቶች፣ 731 ግመሎች፣ 328 ሺሕ 447 በጎች፣ 655 ሺሕ 951 ፍየሎች፣ እንዲሁም ከ37 ሺሕ በላይ አህዮች፣ በጥቅሉ ከአንድ ሚሊዮን 121 ሺሕ 762 በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን ኃላፊው አብራርተዋል። በበረሃማ አካባቢዎች መረጃ ያልሰጡ አርብቶ አደሮች በመኖራቸው የሞቱት የቤት እንስሳት ቁጥር ከላይ ከተጠቀሰው ሊበልጥ ይችላል ብለዋል።

በተጨማሪም፣ በአካባቢው ያሉ ትናንሽ የውኃ ምንጮችና የውኃ ጉድጓዶች ሳይቀር በመድረቃቸው፣ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለመጠጥ ውኃ ችግር መጋለጡን ገልጸዋል። ሆኖም ችግሩን ለማቃለል ውኃ በቦቴ እየቀረበ መሆኑን ነው ያነሱት።
ከ41 ሺሕ በላይ አባወራዎች ወይም ከ244 ሺሕ 242 ያላነሱ ዜጎችም፣ ዝናብ ቢዘንብና ድርቁ ቢጠፋ ወደ ነበሩበት እንዳይመለሱ ሆነው ተፈናቅለው በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ይህም የሆነው አርብቶ አደር በመሆናቸው እና አሁን ላይ ኹሉም የቤት እንስሳዎቻቸው በማለቃቸው ለመመለስ የሚያስችል ምንም ነገር ስለሌላቸው እንደሆነ አብራርተዋል።

የድርቁ ሁኔታ ሲሻሻል ወደ ቀያቸው መመለስ የሚችሉት ደግሞ ለከብቶቻቸው መኖ መግዛት የሚችሉና የቤት እንስሶቻቸውን ከቦታ ቦታ በመኪና ማንቀሳቀስ የሚችሉ ወደ ተለያዩ ቦታዎች መሔዳቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም ወደ ምሥራቅ ሐረርጌ ወረዳዎች ሳይቀር አቋርጠው የገቡ ዜጎች መኖራቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ3.6 ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ላይ የምግብ ዕጥረት እንደተከሰተ እና ማዳረስ የተቻለው ግን በ87 ወረዳዎች ለሚገኙ አንድ ሚሊዮን 47 ሺሕ 537 ሰዎች መሆኑን አንስተዋል።

ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚቀርብ ያን ያህል ድጋፍ የለም ያሉት ኃላፊው፣ የእስካሁኑ ድጋፍ የተደረገው በመንግሥት አቅም መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ የተከሰተው ድርቅ አሁን ላይ በዐሥር ዞኖች እና ከ87 ወረዳዎች በላይ፣ እንዲሁም በአንድ ሺሕ 975 ቀበሌዎች በላይ የተከሰተ መሆኑና፣ በተለይም በዘጠኙ ዞኖች ከፍተኛ የውኃ ዕጥረት መኖሩንም አመላክተዋል።
85 በመቶ የክልሉ ማኅበረሰብ የዕለት ምግቡንና ሌላ ወጪውን የሚሸፍነው ከቤት እንስሳት በሚያገኘው ገቢ በመሆኑም፣ ድርቁ በርካታ እንስሳትን በመግደሉና ዋጋ እንዳያወጡ በማድረጉ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የኑሮ ቀውስ መፍጠሩ ተጠቅሷል።
በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅም እስካሁን ምንም መሻሻል አለማሳየቱ እና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም በድርቁ የተነሳ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ከ300 ሺሕ በላይ ከብቶች ማለቃቸው ተጠቁሟል።
በቦረና ዞን ለሦስት ተከታትይ ወቅቶች ዝናብ አለመዝነቡን ተከትሎ፣ በደቡብ እና በምሥራቅ ኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጫና ማሳደሩን ቀጥሏል።

በቦረና ዞን ያሉ አርብቶ አደሮች የኑሯቸው ምሰሶ የሆኑት ከብቶች በድርቁ ምክንያት እየሞቱ በመሆናቸው፣ ድርቁ ከብቶቻቸውን ጨርሶ ባዶ እጃቸውን እያስቀራቸው መሆኑን የቦረና ዞን አርብቶ አደሮች ሲናገሩ ይደመጣሉ።
የዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር በበኩሉ፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ከብቶች መሞታቸውን ገልጿል። የቦረና ዞን የእንስሳት ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት በበኩሉ የድርቁ ጫና ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን የሚል ሥጋት እንዳለው ጠቁሟል።

የኦሮሚያ ክልል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ገረመው ኦሊቃ በበኩላቸው፣ በክልሉ ቦረና ዞን እና ባሌ ዞን በተከሰተው ድርቅ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ከብቶች መሞታቸውን እና አሁንም ቢሆን በአካባቢው ያለውን ችግር ለመቋቋም በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ዕርዳታ የሚሹ መሆናቸውን ተናግረዋለወ።

በኹለቱ ዞኖች ከዘጠኝ ሺሕ በላይ ዜጎች የሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚሹ እና በቦረና ዞን አምስት ሺሕ ሰዎች ፣በባሌ ዞን እንዲሁ 427 ሺሕ ሰዎች በምግብ ራሳቸው የማይችሉ እና በአስከፊ ችግር ላይ የሚገኙን በመለየት በቂ በሚባል ደረጃ ለማለት ባያስደፍርም እንኳን በየወሩ ለአንድ ሰው አስራ አምስት ኪሎ ስንዴ ዕርዳታ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት በጥምረት የከብት መኖ ከማቅረብ ባሻገር፣ በቦረና ዞን የሚገኙ እንስሳትን ወደ ጌድዮ፣ ኮንሶ፣ ጉጂ እና ሌሎች ዕርጥበታማ፣ ውኃ እና መኖ ወዳለባቸው አካባቢዎች የማሠማራት ሥራ እየሠሩ ነው ብለዋል።
አያይዘውም፣ በክልሉ መንግሥት፣ በፌዴራል መንግሥት፣ በአጋር ድርጅቶች፣ በዞን፣ በወረዳ እና ሕዝብ ለሕዝብ በመተባበር፣ በ126 ቦቲዎች ውኃ የማሰራጨት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ድርቁ ባለባቸው አካባቢዎች ቀን በተጨመረ ቁጥር የችግሩ አድማስ እየሰፋ በመሆኑ ሕብረተሰቡ እና አጋር ድርጅቶች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ይሄን አስከፊ ወቅት አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ጊዜ ማለፍ እንዲቻል ተረዳድቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ኃላፊው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የልማት ምጣኔ ሀብት እና ሥራ አመራር ትምህርት ክፍል ኃላፊ ካሳ ተሻገር (ዶ/ር) በ በኦሮሚያ ክልል ባሌ እና ቦረና ዞን፣ በአፋር እና በሱማሌ ክልል ያለው ድርቅ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች ለሚስተዋለው ድርቅ መባባስ በተለያዩ ቦታዎች በአካባቢ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጥምረት ትኩረት ሠጥተው መሥራት ባለመቻላቸው ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከላይ በተጠቀሱት አከባቢዎች ላይ ያለው ድርቅ በሰሜን ኢትዮጵያ ከነበረው ጦርነት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ኢኮኖሞ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ እና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ከብቶችን እንዳሳጣ፣ እንዲሁም በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለመጠበቅ ከመገደዳቸው በተጨማሪ በከፍተኛ ችግር ላይ እንዲወድቁ አድርጓል ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት እና ሌሎች ተደራራቢ የፖለቲካ ትኩሳቶች መኖራቸውን ተከትሎ፣ መንግሥት ድርቁ በተከሰተባቸው አከባቢዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በማተኮር እየሠራ ነው ለማለት እንደማያስደፍር አመልክተዋል።
አክለውም፣ በቀጣይ መንግሥት ድርቁን ወይም ርሀቡን ለመታደግ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር የኢኮኖሚ ሽግግር ላይ በትኩረት መሥራት ይኖርበታል ብለዋል።

መንግሥት በየጊዜው በዕቅድ የሚይዘውን የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ከሐሳብ ዕቅድ በማውጣት ሊተገብረው ይገባል። በተለያዩ ቦታዎች አካባቢ ምኅዳሩ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ተግባሮችን በመቀነስ፣ ሌሎች ተጨማሪ የማኅበረሰቦችን የአኗኗር ሁኔታ የማዘመን እና አከባቢን የመጠበቅ ሥራ ቢሠራ ይመከራል ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር በየአከባቢው መልካም የሚባሉ አጋጣሚዎች መኖራቸውን ተከትሎ መስኖ እና የውኃ ሀብትን በመጠቀም፣ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ መከላከል እንደሚያስፈልግ ባለሙያው ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here