“ወንጀል የፈጸምኩት ተገድጄ ነው” ማለት ከተጠያቂነት ያድናል?

0
1869

‹አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም› የሕግ መሪና ቀዳሚ ጽንሰ ሐሳብ ነው። ሕግ ዕያወቁ የሚያጠፉን ኹሉ የሚቀጣ ሲሆን፣ አልፎም ‹ስለማላውቅ ነው› ላለ ምህረት ሊሰጥ ይገባል የሚል አይደለም። በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በተነሳውና ዓመትና ወራትን በተሻገረው ጦርነት መካከል በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል። ይህ ትልቅ ጥፋት ሆኖ ሳለ፣ በምርኮ የተያዙ የሕወሓት ቡድን ሰዎች ‹ወንጀሉን የፈጸምነው ተገድደን ነው› ሲሉ ይሰማል። ሽመላሽ ወንዳለ እንዲህ ማለታቸው ከተጠያቂነት ያድናል ወይ ብለው የብዙዎችን ጥያቄ ጠይቀው፣ በማያያዝ ሙያዊ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

ይህን አጭር ጽሑፍ ለማዘጋጀት ምክንያት የሆነኝ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በመጋቢት 02/2014 ያቀረበው የምርመራ ዘገባ ነው። በዘገባው ውስጥ በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል መንግሥት ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር እያካሄደ ባለው ጦርነት የተፈጸሙ ወንጀሎችን አጣርቶ ደረስኩበት ያለውን ግኝት ሲያቀርብ፤ በበላይ የጦር መሪዎች ቀጥተኛ ትዕዛዝና እውቅና፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ በሕወሓት ወታደሮች በሰዎች ላይ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ተገልጿል። እንዲሁም ቀደም ሲል የተማረኩ የቡድኑ ወታደሮች በተለያየ ጊዜ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ቀርበው ‹‹በጦርነቱና በወረራ ጊዜ ወንጀል የፈጸምኩት ተገድጄ ነው›› ሲሉ በተደጋጋሚ ይታያል፤ ይሰማል። ይህም በቀጥታ ጉዳዩን እንዳነሳ ያደረገኝ ምክንያት ነው።

ወደ ፊትም እንዲህ ያሉ ሌሎች ዘገባዎች እና ቃለ-ምልልሶችን ልንሰማ እንችላለን። በመሆኑም፣ መሰል ኹኔታዎች በመገናኛ ብዙኃን ሲደጋገሙ የሚመለከታቸውና የሚሠማቸው መላው ሕዝብ፣ እንዲሁም የወንጀል ሰለባ የሆኑ ሰዎች፣ ‹‹በበላይ ትዕዛዝ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት ትዕዛዝ ተቀባዩን አያስጠይቅም ወይ? ወንጀል የፈጸምኩት ተገድጄ ነው ማለትስ ከተጠያቂነት ያድናል?›› የሚሉ ጥያቄዎች እንደሚፈጠሩባቸው እምነቴ ነው። ስለዚህም ጉዳዩን ከኢትዮጵያ እና ከዓለም ዐቀፍ የወንጀል ሕጎች አንጻር ለማቅረብ ወደድኩ።

በአገራችንም ሆነ በዓለም ዐቀፍ ሕጎች መሠረት በውጊያ ጊዜ ኹለቱም ወገኖች የጦርነቱ አካል ያልሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጽሙ ግዴታ አለባቸው። ስለሆነም ማንኛውም አካል ጥቃት ቢፈጽምባቸው በሕግ ተጠያቂ ይሆናል። በዚህ መርህ መሠረት ሲታይ “ተገደን ነው ወንጀል የፈጸምነው” የሚሉት ግለሰቦች ወታደሮች እንደመሆናቸው “ተገደን ነው” ሲሉ፤ የበላይ ወታደራዊ ሥልጣን ያለው አካል ወይም ኃላፊ አስገዳጅና እምቢ ሊሉት የማይችሉት ትዕዛዝ ሠጥቷቸው እንደሆነ መግለጻቸው ነው።

ይህ ከሆነ ደግሞ፤ አንድ ወታደር የበላይ አካል የሰጠውን ትዕዛዝ መቀበልና መፈጸም ያለበት እስከ ምን ድረስ ነው? ከተጠያቂነት ነጻ የሚሆነው ወይም የማይሆነው በምን ኹኔታ ውስጥ ሆኖ የወንጀል ድርጊቱን ሲፈጽም ነው? የሚሉትን ተጠባቂ ጥያቄዎች ለጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ከኢትዮጵያ የወንጀል ሕግና ከዓለም ዐቀፍ ሕጎች አንጻር እንመልከት።

በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 74 (1) መሠረት፡-
ትዕዛዝ ፈጻሚው ትዕዛዙ ከሕግ ውጪ መሆኑን በተለይም ድርጊቱ ወንጀል መሆኑን እያወቀ፤ የፈጸመውም ድርጊት ነፍስ መግደል ወይም የቃጠሎ ወይም በሰዎች ላይ ወይም በንብረት ወይም በአገር ደኅንነትና በኅብረተሰብ ዋና ዋና ጥቅሞች ላይ ወይም በዓለም ዐቀፍ ሕግ ላይ የደረሰ ከባድ አደጋ ሲሆን፣ በጥፋቱ ኃላፊ ሆኖ ይቀጣል።
በማለት ተደንግጓል።

ይህም ማለት በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ከላይ በተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ ሥር ያሉትን የወንጀል ድርጊቶች የፈጸመ ወታደር ወይም ሌላ በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆነ ሰው፣ ድርጊቱ/ቶቹ ወንጀል መሆናቸውን እያወቀ እንደፈጸመ የሕግ ግምት አለ ማለት ነው። በተመሳሳይም በጄኔቫ ስምምነት ፕሮቶኮል 2 (የስምምነቱ አፈጻጸም መመሪያ 2 ሊባል ይችላል) መሠረት እና በዓለም ዐቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ማቋቋሚያ ሕግ አንቀጽ 33 መሠረት፣ ከላይ የተጠቀሱትን ወንጀሎች በተመለከተ ትዕዛዝ ፈጻሚው ግለሰብ የተሰጠው ትዕዛዝ በግልጽ ሕገ-ወጥ መሆኑን እያወቀ ከፈጸመ በወንጀል እንደሚጠየቅ በግልጽ ተደንግጎ እናገኛለን።

በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ግለሰብ በተለይም በወታደራዊ ግዳጅ ውስጥ ያለ ከላይ በተጠቀሰው ኹኔታ እንደተገለጸው፣ የወንጀል ድርጊት ቢፈጽምና “ተገድጄ ነው የፈጸምኩት” ቢል፣ መገደድ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ደግሞ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 74(2) እና ከላይ በተጠቀሱት በዓለም ዐቀፍ ሕጎች ድንጋጌዎች ጋር በማነጻጸር ስናየው፡-

ትዕዛዝ ፈጻሚው ወንጀሉን የፈጸመው የወታደር ሥርዓት አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት በሚያስገድደው ተግባር ሆኖ ትዕዛዙን ለመቃወምና ለመከራከር ባለመቻሉ በቀጥታ ከመፈጸም በቀር ሌላ የተሻለ መንገድ ለማግኘት ካልቻለ እንደሆነ በግልጽ ደንግጓል።
ወደ ተነሳንበት ነጥብ ስንመለስ፤ የሕወሓት ወታደሮች በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 74 (1)፣ በጄኔቫ ስምምነት እና በዓለም ዐቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ሕግ ሥር የተዘረዘሩትን የወንጀል ድርጊቶች ከፈጸሙ በኋላ “ወንጀሉን የፈጸምነው ተገደን ነው” ማለት ይችላሉ ወይ? የሚለውን እንይ፤

በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግም ሆነ በተጠቀሱት የዓለም ዐቀፍ ሕጎች ውስጥ፤ ሰው መግደል፣ ማሰቃየት፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎችም በሰዎች ላይ እንዲፈጸሙ የታዘዙ ትዕዛዞች፣ በግልጽ ሕገ-ወጥ የሆኑ ትዕዛዞች ተብለው ተቀምጠዋል። ይህም ማለት፣ ማንም ሰው እነዚህ ድርጊቶች ወንጀል መሆናቸውን እንደሚያውቅ የሕግ ግምት ይወስዳል። በመሆኑም አንድ የበታች ወታደር እነዚህን ድርጊቶች እንዲፈጽም ሲታዘዝ፣ ትዕዛዙን ተቀብሎ ከፈጸመ በኋላ ወንጀል መሆናቸውን አላወቅሁም የሚል መከላከያ እንዲያቀርብ አይፈቀድለትም። ቢያቀርብም ተቀባይነት አይኖረውም ማለት ነው።

በሌላ አንጻር ደግሞ አንድ ሰው በኢትዮጵያም ሆነ በተጠቀሱት የዓለም ዐቀፍ ሕጎች መሠረት ከላይ የተጠቀሱትና ማንም ሰው እንደሚያውቃቸው የሕግ ግምት የሚወሰድባቸው የወንጀል ድርጊቶችን ከፈጸመ በኋላ “ተገድጄ ነው” የሚል መከላከያ ለማቅረብ የሚችለው ድርጊቱን ከመፈጸም በቀር ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌለው ለፍርድ ቤት ማስረዳትና ማሳመን ከቻለ ብቻ ነው።

ዋና መነሻችን “ተገደን ነው ወንጀል የፈጸምነው” የሚሉት ግለሰቦች አባባል ስለሆነ፣ ምላሻቸውን ከላይ ከተጠቀሱት ሕጎች ትንታኔ እና ከግለሰቦቹ የወንጀል አፈጻጸም ጋር በማነጻጸር እንመልከት፤ የተፈጸሙት ወንጀሎች፡-
ብዙ ሰዎችን በአሰቃቂ ኹኔታ በሕይወት እያሉ በእሳት ማቃጠል፤
አንዲትን ሴት ብዙ ወንዶች ሆነው አስገድደው መድፈር፤ ያውም ሴት ልጅን ወላጆቿ ፊት እና እናትን ልጆቿ ፊት፤
መነኮሳትን አስገድዶ መድፈር፤
የግለሰቦችን ቤት መዝረፍና ቤቱን ማውደም፤
የሕዝብ መገልገያ ተቋማትንና መሠረተ-ልማቶችን መዝረፍና የቀረውን ማውደም፤
ሰዎችን ማሰቃየትና ከባድ የአካል ጉዳት ማድረስ፣ ወዘተ. ናቸው።

የተፈጸሙትን ድርጊቶች ስንመለከት ግለሰቦቹ ድርጊቶቹን ሲፈጽሙ መፈጸም ብቻ ሳይሆን የሚፈጽሙትን ድርጊት በምን መልኩ ቢፈጽሙት በተጎጂዎቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ አካላዊና ሥነልቦናዊ ጉዳት እንደሚያስከትል አስበው ነው የፈጸሙት። በሌላ አገላለጽ፣ የወንጀሎቹ አፈጻጸም የሚያረጋግጠው የወንጀል ድርጊቶቹ አስቀድሞ በደንብ የታቀዱና የታሰበባቸው እንደሆኑ ነው። በተጨማሪም ከዘገባዎችና ከተጎጂዎች ቃለ-መጠይቅ መረዳት እንደሚቻለው የሕወሓት ወታደሮች ድርጊቱን ሲፈጽሙ ተበዳዮቹን በማንነታቸው እየሰደቡና እያንቋሸሹ፣ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ አካላዊ ድብደባና ስቃይ በማድረስ ጭምር ነው።

ለምሳሌ አንዲትን ሴት በቡድን አስገድደው ሲደፍሩ ጥላቻቸውን ለመግለጽ ከስድብና ማንቋሸሽ በተጨማሪ በጥርስ እስከመንከስ የደረሰ ፍጹም ነውረኝነትና ኢሰብዓዊነትን የሚያሳይ የአካል ጉዳት በማድረስ ነው። ስለሆነም፣ ወንጀል አፈጻጸሙ የሚያመለክተው ፈጻሚዎቹ ድርጊቱ ወንጀል መሆኑን ከማወቃቸውም ያለፈ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ሆን ብለውና በዓላማ የፈጸሙት እንጂ ድርጊቱን ተገደው ያልፈጸሙት መሆኑን ነው።

የአሸባሪው ሕወሓት ወታደሮች “ተገደን ነው” ሲሉ ትዕዛዙን ለመቃወምና ወንጀሉን ላለመፈጸም ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም? የሚለውን ጥያቄ ከተጠቀሱት የኢትዮጵያና የዓለም ዐቀፍ ሕጎች ትንታኔ አንጻር ስንመለከት ደግሞ፣ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት የሕወሓት ወታደሮች ከመፈጸም ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም ወይም ኹኔታው አስገድዷቸዋል ለማለት፣ ትዕዛዙ ወዲያው እንዲፈጸም ግድ የሚል እንዲሁም ወዲያው አለመፈጸም ከፍተኛ ቅጣትን ወይም ሞትን ወይም ከባድ የአካል ጉዳትን ወይም ሌላ ተጨባጭ ችግርን ወይም ጉዳትን ሊያስከትል የሚችል መሆን አለበት።

በሕወሓት ወታደሮች የተፈጸሙትን ድርጊቶች ከላይ ከተሰጠው ማብራሪያ ጋር በማነጻጸር ስንመዝናቸው፣ ወንጀሎቹ የተፈጸሙት በወራት ለሚቆጠር ጊዜና በተደጋጋሚ እንደመሆኑ በዚህ ጊዜ ውስጥ ወንጀል ፈጻሚዎቹ ግለሰቦች ታዝዘው ቢሆን እንኳ ለወራት ወንጀል ከመፈጸም ይልቅ ቢያንስ ለመንግሥት አካል እጃቸውን የመስጠት ዕድል ነበራቸው። እነሱ የተያዙት ግን በወንጀል ድርጊታቸው ቀጥለው ባለበት በውጊያ ጊዜ ቆስለውና ተማርከው ነው። በሌላ አገላለጽ፣ ግለሰቦቹ በጊዜው ሕሊናቸው ወንጀል ለመፈጸም ወይም ላለመፈጸም ምርጫ ነበረው፤ እነርሱም ወንጀል መፈጸምን ምርጫቸው አድርገዋል።

ምርጫቸው ባይሆን ኖሮ ወንጀሉን በቡድን በመሆን ከመፈጸም ይልቅ የቡድን ቅንጅታቸውን ንጹኃን ላይ ወንጀል ለመፈጸም ሳይሆን ከወንጀል ድርጊቱ እራሳቸውን ለማራቅ በተጠቀሙበት ነበር። እነዚህና ሌሎች ወንጀሉን ያለመፈጸም ዕድል እያላቸው ነገር ግን የተለያዩ አሰቃቂ ወንጀሎችን ደጋግመው ለወራት በቡድን መፈጸማቸው የሚያረጋግጠው፣ መገደድን ሳይሆን ሙሉ ፍቃደኝነትንና የድርጊቱ ዓላማ ተጋሪነታቸውን ነው።

ስለሆነም የተያዙና ወደ ፊትም በቁጥጥር ሥር የሚውሉ የሕወሓት ወታደሮች ዓላማቸው አድርገው ብዙ ወንጀሎችን ከፈጸሙና የልባቸውን ካደረሱ በኋላ “ወንጀል የፈጸምነው ተገደን ነው” በማለት ከተጠያቂነት ሊድኑ አይችሉም። ይልቁንም በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ዐቀፍ የወንጀል ሕግ ስለሚያስጠይቃቸው መንግሥት በፍርድ አደባባይ አቁሟቸው ተበዳዮች (እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ሕዝብ) ፍትሕን ማግኘት አለባቸው፤ መብታቸውም ነው። መንግሥትም ይህን የማረጋገጥ ግዴታ አለበት።

ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ለወደፊቱ የመንግሥትም ሆኑ የግል መገናኛ ብዙኃን የወንጀል ተጠርጣሪዎቹን የሕወሓት ወታደሮች ቃለ-መጠይቅ በማድረግ “ወንጀል የፈጸምነው ተገደን ነው” ሲሉ በማሳየትና በማሰማት በሕዝብ ቁስል እንጨት መስደዳቸው ሊቆም ይገባል። ምክንያቱም ሕዝብ የሚፈልገው ፍትሕ እንጂ ምሬቱን የሚቀሰቅሱ ዘገባዎችን አይደለም።

ሽመላሽ ወንዳለ (በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ እና በዓለም ዐቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ኹለተኛ ዲግሪ) አላቸው። በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ላይ ይገኛሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here