ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የቦንድ ሽያጭ ሊጀመር መሆኑ ተገለፀ

ከቦንድ ሳምንት ሽያጭ ከ 70 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል

ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የቦንድ ሳምንት ሽያጭ እንደሚጀመር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በአገር ዐቀፍ ደረጃ በከፍተኛ የሕብረተሰብ ተነሳሽነት ላለፉት ስምንት አመታት ሲካሄድ የቆየውን የቦንድ ሽያጭ፣ ሀብት በማሰባሰብ ለማጎልበት እንደታሰበ እና ይህም መርሃ ግብር ከመጋቢት 20/2014 ጀምሮ እንደሚካሄድ ተነግሯል። ለተከታታይ ኹለት ሳምንታት ማለትም እስከ ሚያዚያ 5/2014 የሚቆይ የቦንድ ሽያጭ እንደሚጀመር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሀ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በ 2012 በኮቪድ መመሪያዎች ምክንያት የቦንድ ሽያጩ ያልተካሔደ ቢሆንም፣ ከ 2007 ጀምሮ እስከ 2013 በየዓመቱ የቦንድ ሳምንት ተካሒዶ በስድስት ዙር 427 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል።

በየዓመቱ በተካሄደው የቦንድ ሳምንት እንቅስቃሴ በአማካይ ከ 85 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ እንደተቻለ እና በተያዘው አመት ከ 70 እስከ 100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በተያዘው በጀት ዓመት በየካቲት ወር 2014 ብቻ ከ91 ሚሊዮን ብር በላይ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን በመጠቀም መሰብሰብ እንደተቻለ እና ይህም ከጥር ወር 2014 ጋር ሲነጻጸር ከ 50 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ማሳየቱ ተጠቁሟል።
በተያዘው በጀት ዓመት በጥር ወር ለግድቡ 41 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፣ በየካቲት ወር 91 ሚሊዮን 802 ሺሕ 903 ብር መሰብሰብ መቻሉ ተገልጿል።

በበጀት ዓመቱ በየካቲት ወር የተሰበሰበው ገቢ፣ በኢትዮጵያ ከሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ከቦንድ ግዥ 65 ሚሊዮን 788 ሺሕ፣ ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ 72 ሚሊዮን 790 ሺሕ፣ ከ 8100 ኤ የስልክ ዕርዳታ መቀበያ እንዲሁ 12 ሚሊዮን 213ሺሕ ብር፣ በአጠቃላይ 91 ሚሊዮን 802 ሺሕ 903 ብር መሰብሰብ መቻሉን ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው የሕዳሴ ግድብ የብሔር ብሔረሰቦች ዋንጫ ጥሩ በሚባል ደረጃ ገቢ መሰብሰብ በመቻሉ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ፣ በሕብረተሰቡ በኩል ያለው ተነሳሽነት መጨመሩ፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎች የማነቃቂያ ሥራዎች እንዲሁም እንቅስቃሴዎች መጨመራቸው ለገቢው መጨመር በቀዳሚነት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

በተያዘው በጀት አመት በአጠቃላይ በስምንት ወራት 672 ሚሊዮን 757 ሺሕ 856 ብር እንደተሰበሰበ እና ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ 700 ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ ማሳየቱ ተገልጿል።
ባለፈው በጀት ዓመት በስምንት ወራት ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ እንደተቻለ እና በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ኹለት ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ኃላፊው ተናግረዋል።

ያለፈው ዓመት የግድቡን የውኃ ሙሌት ተከትሎ ከፍተኛ ገቢ የተሰበሰበበት በጀት ዓመት ሲሆን፣ በተያዘው ዓመት ግን በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በየወቅቱ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ለገቢው ማሽቆልቆል መሆናቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here