ገቢው ከባለፈው ዓመት በ20 ሚሊዮን ብር አድጓል
በ2014 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ዘጠኝ የሎተሪ ዓይነቶችን ለገበያ በማቅረብና ከዕድል ጨዋታ ኮሚሽን ከ687 ሚሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ ገቢ መሰብሰቡን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ከሐምሌ 1/2013 እስከ የካቲት 30/2014 ባሉት ስምንት ወራት፣ ኹለት የሚፋቁ ማለትም፣ ቢንጎ እና ዕድል ሎተሪ፣ እንዲሁም እንቁጣጣሽ፣ ገና፣ ትንሳኤ፣ ልዩ ዕድል፣ ዝሆን እና ቶምቦላን ጨምሮ ስድስት ዓይነት የቁጥር ሎተሪዎችን ለገበያ በማቅረብ እና ከዕድል ጨዋታ ኮሚሽን በጥቅሉ ስድስት መቶ ሰማንያ ሰባት ሚሊዮን 878 ሺሕ የሚጠጋ ብር ገቢ መሰብሰቡን የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቴዎድሮስ ንዋይ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ኃላፊው አክለውም፣ ተቋሙ ከላይ ከተጠቀሰው ገቢ ከ1 መቶ ሚሊዮን 803 ሺሕ ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን ገልጸዋል። ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 20 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ማሳየቱ ተጠቁማል። በ2013 በጀት ዓመት በስምንት ወራት 600 ሚሊዮን 687 ሺሕ ብር ተሰብስቦ የነበረ ሲሆን፣ በተያዘው ዓመት ከ 687 ሚሊዮን 878 ሺሕ ብር ያላነሰ ገቢ ተሰብስቧል።
በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ወራት ለማግኘት ታቅዶ የነበረው፣ 500 ሚሊዮን 300 ሺሕ ሲሆን፣ ይህም አስተዳደሩ የዕቅዱን 128 በመቶ ማሳካት መቻሉን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገልጸዋል።
ባለፉት ሦስት እና አራት ወራት የከፍተኛ ወይም ትላልቅ ሎተሪዎች ማለትም የገና፣ የዝሆን እና ቶምቦላ የመሳሰሉትን ሎተሪዎችን በስፋት ማሰራጨቱ ከላይ የተጠቀሰውን ዕቅድ ለማሳካት ጉልህ ሚና መጫወቱ ተነግሯል።
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት ምንም እንኳን ከያዘው ዕቅድ በላይ ቢያስመዘግብም፣ በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት እና ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ ባለው ጦርነት ምክንያት በተለያዩ አከባቢዎች የሚገኙ ዘጠኝ ቅርንቻፎቹ ከአራት ወራት በላይ ተዘግተው እንደነበረ እና በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ሲፈጠሩ የነበሩ የጸጥታ ችግሮች ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደሩበት ተናግሯል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት 500 ሚሊዮን 500 ሺሕ ብር ገቢ፣ 100 ሚሊዮን 500 ሺሕ ብር ትርፍ የተገኘ ሲሆን፣ ባለፉት ኹለት ወራት እንዲሁ ከ35 ሺሕ ብር ያላነሰ ብር አስገብታል ተብሏል።
በተመሳሳይ ባለፈው ጥር ወር 2014 አስተዳደሩ ሰብስቦት ከነበረው አንጻር በየካቲት ወር ብቻ ከ 98 ሺሕ ብር በላይ ብልጫ ያለው ብር እንደተሰበሰበ ተመላክቷል።
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በተያዘው በጀት ዓመት በሚቀጥሉት አራት ወራት ከፍተኛ ወይም ትላልቅ ሎተሪዎችን ማለትም፣ የትንሳኤ፣ ቶምቦላ፣ ዝሆን እና ሌሎች ሎተሪዎችን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚገኙ ደንበኞቹ በማሰራጨት የተሻለ ገቢ ለማስገባት እንደሚሠራ ኃላፊው ጠቁመዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014



