አርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ህወሃት የትግራይ ህዝብ በመሬት ላይ ካለው ፍላጎት ጋር የሚመጣጠን የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያገኝበት ምቹ ሁኔታዎች ከተፈጠረለት፤ በተመጣጣኝ የጊዜ ገደብ ውስጥ የትግራይ መንግስት የትጥቅ ማቆም አድማውን በአስቸኳይ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀ።
ይህ የጦርነት ማቆም የተሳካ እንዲሆን የትግራይ መንግስት የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል ሲልም ገልጿል።
መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ትናንት ማስታወቁን ተከትሎ፤ ህወሃት የትግራይ የውጪ ጉዳይ ፅ/ቤት ባለው ተቋም በኩል መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም፤ የትግራይ ህዝብና መንግስት እያጋጠመን ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁሌም ፍላጎቱን እና ዝግጁነቱን እንዳላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል ብሏል።
ባለፉት አራት ዓመታትም ይህንን መልዕክት ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሙሉ ደጋግሞ ማስተላለፋን የገለፀው ህወሃት፤ “ከ17 ወራት በፊት የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት ሰላማዊ መንገዶች ሁሉ ስለተዘጉ እና የትግራይን ህዝብ ለማጥፋት አስከፊ ወታደራዊ ዘመቻ በመጀመሩ ህልውናችንን ለማረጋገጥ ጦርነት ውስጥ እንድንገባ ተገደናል።” ሲል ገልጿል።
“የትግራይ ህዝብና መንግስት አሁን የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ምንጊዜም ግልፅ አቋም አላቸው።” ሲልም በመግለጫው አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም የትግራይ ህዝብ ያለአንዳች እንቅፋት በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ሊደረግ የሚገባውን ሰብዓዊ እርዳታ በመከለከሉ ምክንያት ምንም አይነት እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲገባ አልተፈቀደም ማለት ይቻላል ሲልም ገልጿል።
የስልክ እና የባንክ አገልግሎቶችን መልሶ በማቋቋም መንግስት በጣም ቀላል እርምጃዎች ቢወስድ ኖሮ ቁጥር ሥፍር የሌላቸውን ህይወት ይታደግ እንደነበረም ህወሃት ገልጿል።
አክሎም “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ወደ ትግራይ ያልተገደበ ሰብዓዊ አገልግሎት እንዲደርሱ ከከንቱ ቃል ኪዳን በመውጣት ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን።” ብሏል።
የትግራይ መንግስት ለዚህ ሥራ ስኬት ቁርጠኛ ቢሆንም፣ ፖለቲካዊ እና ሰብዓዊ ጉዳዮችን ማስተሳሰር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ልናስተውል እንወዳለን ያለው ህወሃት “የትግራይ ህዝብና መንግስት ለሰላም እድል ለመስጠት የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ” ሲልም ገልጿል።
____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




