አርብ መጋቢት 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ መንግሥት የኦንላይን አገልግሎት ክፍያዎችን በዲጂታል አማራጭ እንዲፈጸሙ ሊያደርግ መሆኑ ተገለፀ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ማስተርካርድ የመንግሥት አገልግሎት የክፍያ ሥርዐትን ለማዘመን የሚያስችላቸውን ሥምምነት አድርገዋል፡፡
ሥምምነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የማስተርካርድ የክፍያ አማራጭን ከኤሌክትሮኒክ ሰርቪስ አገልግሎት ፖርታል ጋር በማቀናጀት ዜጎች ክፍያዎችን ኦንላይን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ጥረታችን ኢትዮጵያን ከጥሬ ገንዘብ ሕትመትና ሥርጭት ወጪ ማላቀቅና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂያችን ተግባራዊ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ከማስተር ካርድ ጋር የሚደረገው ትብብር ኹለገብ ዲጂታል የክፍያ መፍትሔዎችን በማቅረብ ዜጎች በማንኛውም የባንክ ካርድ ክፍያ እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል ያሉት ሚኒስትሩ፥ የገቢ አሰባሰብን ለማሻሻል እና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
የማስተር ካርድ የምሥራቅ አፍሪካ ሥራ አስኪያጅ ሸርያር አሊ ቀልጣፋ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ፈጠራ የታከለበት የዲጂታል የክፍያ አማራጮችን በመዘርጋት የኢትዮጰያ መንግሥትን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እንደሚደግፉ መናገራቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አገልግሎቱ በሚቀጥለው ሳምንት የሚጀመር ሲሆን፤ ዜጎች ከውጭ አገራት ጭምር ባሉበት ቦታ ሆነው ለተጠቀሙት የመንግሥት አገልግሎት በማሰተር ካርድ የክፍያ አማራጭ ክፍያዎችን ኦንላይን መክፈል ይችላሉ ተብሏል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የትግበራ ምዕራፍ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅት አባላት ይህንን የክፍያ መተግበሪያ አማራጭ በመጠቀም ፍቃድ ለማውጣትና ለማደስ በማንኛውም የክፍያ ካርድ ዓይነት ክፍያ መፈፀም ይጀምራሉ፡፡
ይህንን አሠራር ለመተግበር ማስተር ካርድ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሥምምነት ላይ የደረሱት በ2020 ሲሆን፤ ይህም “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቲጂን” መሠረት በማድረግ መሆኑም ተገልጿል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n






