በመዲናዋ ለሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የነዳጅ ድጎማ ሊደረግላቸው ነው

0
1440

የድጎማው ተጠቃሚ ተሸከርካሪዎች እስከ ሚያዝያ 30 ድረስ አቅጣጫ ጠቋሚ ወይም GPS የግድ ማስገጠም አለባቸው ተብሏል

ዕረቡ መጋቢት 28 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ለሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የነዳጅ ድጎማ ሊደረግላቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ፤ በከተማው የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሸከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማ ማድረግ በሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ላይ ውይይት ተካሂዷል።

የድጎማ ሥርዓቱ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ቢሮው ገልጿል።

በድጎማ ሥርዓቱ GPS እንዲገጠም መደረጉም የትራንስፖርት ሥምሪቱን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ቁጥጥሩን ለማሳለጥ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።

ድጎማው ከሀምሌ 1 ቀን 2014 ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆንም የቢሮው መግለጫው ያስረዳል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጐማ አፈፃፀም ረቂቅ መመሪያ ማዘጋጀቱን የገለጸ ሲሆን፤ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ውይይት መደረጉም ተገልጿል።

የነዳጅ ድጎማው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ህብረተሰብ አገልግሎት የሚሰጡ በታሪፍ እና በስምሪት ቁጥጥር ላይ የተመሠረተ መለስተኛ፣ መካከለኛ የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ተሸከርካሪዎችን ይመለከታልም ተብሏል።

በዚህም መሰረት በመዲናዋ የህዝብ የትራንስፓርት አገልግሎት የሚሠጡ የመንግሥትና የግል አውቶቡሶች፣ የሳሎን ታክሲዎችን ሳይጨምር በከተማ ውስጥና በከተሞች መካከል የህዝብ የትራንስፓርት አገልግሎት የሚሠጡ ኮድ 1 እና ኮድ 3 ሚኒባስ (አዲስ አበባ ውስጥ የተመዘገቡ) ተሽከርካሪዎችን እንደሚያካትት ቢሮው አስታውቋል።

ሆኖም ግን በመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ በግል እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሠራተኛ አገልግሎት እንዲሁም በግል ትምህርት ቤቶች የተማሪ አገልግሎት የሚሠጡ ድጎማው አይመለከታቸውም ተብሏል።

በትራንስፖርት ቢሮ የህዝብ ጭነት ስምሪትና ድልድል ኦፕሬተር ፈቃድ ዳይሬክተር አልዓዛር ይርዳው ረቂቅ መመሪያው በአሁኑ ጊዜ እያደገ የመጣውን የነዳጅ ዋጋ ድጎማን በሂደት በማስቀረት ወደቀደመው የዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ አስተዳደር ሥርዓት እንዲመለስ ያስችላል ብለዋል፡፡

የነዳጅ ዋጋ ድጐማው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የጐላ ተፅዕኖ በማያስከትል አግባብ ለመተግበር የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት እንደሆነም አልዓዛር አስረድተዋል፡፡

በድጎማ ሥርዓቱ የተመዘገቡ ተሸከርካሪዎች እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2014 ድረስ ባሉት ጊዜ ውስጥ GPS መግጠም አስገዳጅ ነው የተባለ ሲሆን፤ እስከ ግንቦት 30/2014 የተሸከርካሪዎች መረጃ ወደዳታ ቤዝ የማስገባት ሥራ እንደሚሰራ ተገልጿል።

በመሆኑም በመዲናዋ በህዝብ ትራንስፖርት የተሰማሩ ተሽከርካሪዎችን የሚመለከቱ አጠቃላይ መረጃዎች በአስር ቀናት ተደራጅተው ለቢሮው እንዲላኩለት ጠይቋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here