የሕገ መንግሥቱ የመሻሻል ዕድል

የአንድ አገር መተዳደሪያ ዋልታ የሆነው ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ ኹሉንም ዜጋ በተዋረድ ማሳተፍ ይገባዋል። ነገር ግን በተቃራኒው የጥቂት ቡድንን ፍላጎት እና ዓላማ መሠረት አድርጎ አንድ ሕገ መንግሥት ከተረቀቀ የግጭት መነሻ ከመሆን ባለፈ ለአገር መፍረስ ምክንያት ይሆናል የሚሉት በዋናነት የሕግ ባለሙያዎች ናቸው።

አንዳንድ ባለሙያዎች ስለሕገ መንግሥት ጉዳይ ሲያነሱ፣ አገራት በየጊዜው ሕገ መንግሥትታቸውን የሚያሻሽሉበት ዕድል ሰፊ መሆኑን በመጥቀስ አሜሪካን እንደ አብነት ሲያነሱ ይደመጣሉ።

አሜሪካ ሕገ መንግሥቷን እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ለመጀመሪያ ጊዜ በ 1787 ሥራ ላይ ካዋለች በኋላ ለ 27 ጊዜ ያሻሻለች አገር ናት። አገሪቱ ሕገ መንግሥቷ ካወጣች ኹለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ማለትም በ 1788 ለማሻሻል እንደበቃች መረጃዎችን በማጣቀስ ምሁራን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያም ‹ዘመናዊ› ሕገ መንግሥት የሚባለው በ1923 አጼ ኃይለሥላሴ በሥራ ላይ እንዲውል ያደረጉት የመጀመሪያው ሠነድ ነው።
ኹለተኛው ሕገ መንግሥት የሚባለው እንዲሁ ኤርትራ ከጣሊያን ወረራ ነፃ ከወጣች በኋላ የ1923ቱን ሕገ መንግሥት ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1955 ተሻሽሎ የቀረበው ነበር።
ሦስተኛው እና አጭር ዕድሜ ያለው ሕገ መንግሥት ሊባል የሚችለው ደግሞ በ1979 የፀደቀው እና በ1983 የደርግ አገዛዝ ከሥልጣን ሲወገድ የተሻረው ነው።

አራተኛው እና አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በ1987 የጸደቀ ሲሆን፣ የሕገ መንግሥቱ ረቂቅ ላይ ሕዝብ ተወያየበት ከተባለ በኋላ ከብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወከሉ በተባሉ የምክር ቤት አባላት አማካይነት ኅዳር 29 ቀን 1987 ጸድቆ ነሐሴ 15 ቀን 1987 በነጋሪት ጋዜጣ ታውጆ በሥራ ላይ የዋለ ነው።

የአገሪቱ የሕጎች ኹሉ የበላይ ሕግ የሆነው ይህ ሕገ መንግሥት፣ በአጠቃላይ 11 ምዕራፎች እና 106 አንቀፆችን ይዟል። ሕገ መንግሥቱ ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩት ሰብዓዊ መብቶች እና ነፃነቶች የማይጣሱና የማይገፈፉ መሆናቸውን ይደነግጋል። ከዚህ ባሻገር የዜጎች እና ሕዝቦች ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው ያስገድዳል።

በሕገ መንግሥቱ መሠረት መንግሥትና ኃይማኖት የተለያዩ ሲሆኑ፣ መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ፣ ኃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አንደማይገቡ አመላክቷል።

አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት መጽደቁን ተከትሎም፣ የፀረ-ሙሥና ኮሚሽን፣ የኢትዮጽያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፣ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን ጨምሮ ሌሎች መሰል ልዩ ልዩ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲፈጠሩ ከማገዝ ባለፈ፣ ነፃ ፍርድ ቤቶች እና ነፃ መገናኛ ብዙኃን አገራችን ውስጥ እንዲቋቋሙና እንዲያብቡ አስችሏል ይባላል። በተያያዘም አገሪቱ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የመድብለ ፓርቲዎች ምርጫ እንዲካሄድ ያስቻለው ይኸው አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት ስለመሆኑ ሲነገር ይሠማል።
ታዲያ ይህ ሕገ መንግሥት በርካታ ጠቃሚ ፅንሰ-ሐሳቦች ወይም የሕግ አንቀፆች ቢኖሩትም፣ መካተት ያልነበረባቸው የሕግ አንቀፆች ይዟል በሚል ሠፊ ትችት ይቀርብበታል።

በርካቶች ሕገ-መንግሥቱ ኢትዮጵያን ለመፍረስ አደጋ አሳልፎ ይሰጣታል ብለው ያምናሉ። ለዚህም በተለይ ስለ ሉዓላዊነት የሚያነሳውን አንቀፅ ስምንት እና ስለ ብሔራዊነት የሚያትተው አንቀፅ 39 አገርን ለአደጋ የሚያጋልጡ ሰለመሆናቸውን በሕገ መንግሥት ባለሙያዎች ሲነሳ ይደመጣል።

በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አገርን ለብተና የሚዳርጉ አንቀፆች አሉ መባሉን ተከትሎ ሕገ-መንግሥቱን ሊቀየር ይገባል የሚሉ አካላት እንዳሉ ኹሉ፣ ሕገ መንግሥቱ መቀየር የለበትም ብለው የሚከራከሩ እና ሠነዱ የሚቀየርበት ዕድል ካለ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚለውን ዕሳቤ በማጉላት ሐሳባቸውን የሚያንጸባርቁ አካላትም አሉ።

ይህ ዓይነቱ የሐሳብ ተቃርኖ አሁን ላይ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለውን መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጥርት ያለ አቋም እንዳይኖረው ያደረገ መሆኑ እሙን ነው።
የተለያዩ ሐሳቦች የሚነሳበት ይህ ሕገ መንግሥት አሁን የመቀየር ዕድል አለው ወይስ የለውም የሚለውን ጥያቄ ብዙዎች ሲያነሱ ይደመጣል።

የሕግ ባለሙያው ካፒታል ክብሬ በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ብዙኀንን በአግባቡ ከማስተናገድና ሠላምን ከማረጋገጥ አንፃር ችግር ያለበት፣ ዕኩልነትን የላረጋገጠ ነው ይላሉ።
የሕግ ባለሙያው ሕገ መንግስቱ አገራዊ አንድነትን ከመፍጠር እና ሕዝባዊ ትስስሮችን ከማደርጀት አንፃር የተወጣው ሚና አናሳ መሆኑን አጽንዖት ሠጥተውበታል።

በዚህም፣ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ ለሙሉ መቀየር የማይታሰብ ቢሆንም፣ የሚሻሻልበት ዕድል ግን ቅርብ መሆኑን አልጠራጠርም ባይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ያለፉት ኹለትና ከዚያ በላይ ዓመታት ልዩነቶች የሠፉበት፣ ዜጎችን ለግጭት የሚዳርጉ ትርክቶች እና ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በሠፊው የተስተዋሉባቸው ነበሩ። ክልሎች እና የፀጥታ አካላት የሕዝቦችን መብት ከማስጠበቅ ይልቅ ፖለቲካው መጠቀሚያ ሲያደርጉ የተስተዋለበት ሒደት ታዝበናል ይላሉ የሕግ ባለሙያው።
ለነዚህ ተደራራቢ ችግሮች መነሻ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ መሆኑን ያምናሉ።

መንግሥትም የነዚህ ተደራራቢ ችግሮች መነሻ በዋናነት ሕገ መንግሥቱ መሆኑን በመረዳት እና የፀጥታ አደረጃጀቶችን በመገምገም መፈተሽ እንዳለበት የሕግ ባለሙያው ካፒታል ክብሬ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እያስተዳደረ የሚገኘው ብልጽግና ፓርቲ የሥልጣን ጊዜውን ሳይጠናቅቅ፣ የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽ እና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ፣ሕዝብን ያሳተፈ ሠፊ ዝግጅት በማድረግ ሕገ መንግሥቱን ቅርብ በሚባል ጊዜ መቀየር እንዳለበት ነው የገለፁት።
ሌላው የሕግ ባለሙያው አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ ሕገ መንግሥቱ በኹለት ዓይነት መልኩ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ እየተነሳበት ነው ብለዋል።

በሕወሓት እና በኦሮሚያ ክልል በኩል ሕገ መንግሥቱ መሻሻል የለበትም ብለው የሚያምኑ አሉ። የአማራ ክልል ሕዝብና በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ በተቃራኒው ሕገ መንግሥቱ እንዲቀየር በተደጋጋሚ የሚወተውቱ እንዳሉ ታዝቢያለሁ ባይ ናቸው።

አበበ አስከትለውም፣ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ብዙ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ የጠቀሱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው የብልጽግና መንግሥት ከተፎካካሪ የፖለተካ ፓርቲዎች ባሻገር፣ ከክልል እስከ ወረዳ በመውረድ ከኹሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ሠፊ ዝግጅት አድርጎና ጊዜ ወስዶ በሕገ መንግሥቱ ላይ ሊወያይበት ይገባል ብለዋል።

ሌላኛው የሕግ ባለሙያ ጥጋቡ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ ሕገ መንግሥቱን አሁን ባለው ትውልድ ዘመን መቀየር አይታሰብም ያሉ ሲሆን፣ የሚሻሻሉ አንቀፆች እንዳሉ ግን አልጠራጠርም ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ኹለት ምክንያቶችን አስቀምጠዋል። አንደኛው ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር ማለትም፣ ለዜጎች መፈናቀል ወይም መሰደድ እና ለሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ጭምር ምክንያት ስለሆነ ባይ ናቸው።

ከዚህ ባሻገር፣ ይህ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በቋንቋና በጎሳ የተመሠረተ፣ ለአንዱ ዜጋ የአካባቢና የክልል ባለቤትነት የሚሠጥ፣ ሌላውን ዜጋ መጤ ብሎ የሚፈርጅ በመሆኑ አብዛኛው ማኅበረሰብ አይቀበለውም ብለዋል።
ከዚህ አንፃር አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚስማማበት ሥርዓት እንዲኖር ስለሚያስፈልግ የሕገ መንግሥቱ መሻሻል አያጠያይቅም ብለዋል።

ማኅበረሰቡ በሠላማዊ መንገድ ሕይወቱን መምራት እንዲችል፣ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱ እንዲጠበቅለት፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወቱ እንዲዳብር ከተፈለገ ሕገ መንግሥቱን መቀየር የግድ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል።
ጥጋቡ አክለውም፣ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ አገረ መንግሥት ለመገንባት ሲታሰብ በዋናነት አሁን ያለው የፌደራል አወቃቀር በቋንቋና በጎሳ ተዋቅሮ መገንባት የለበትም ባይ ናቸው።

የሕገ መንግሥት እና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታዮ (ዶ/ር) የፌደራል ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች የሚያወጡት ሕገ መንግሥት በቀላሉ የሚሻሻል አይደለም ይላሉ።
ከዚህ አኳያ በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም የሚሻሻልበት ዕድል እሩቅ ነው ባይ ናቸው። ሕገ መንግሥቱን በቀላሉ ለማሻሻል እንደሚከብድም ማኅበረሰቡ ሊረዳ ይገባዋል ብለዋል።

ኃይለየሱስ አክለውም፣ በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መቀየር እንዳለበት ጥያቄውን የሚያነሱ በርካቶች ሲሆኑ፣ ጥያቄያቸው እንደተጠበቀ ሁኖ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ አገራዊ ኮሚሽን እንዳቋቋመ ጠቅሰዋል።
በዚህም ይህ ውይይት ውጤታማ የሚሆንበት ዕድል ካለ የሕገ መንግሥቱ ጉዳይ እንደሚቀርብ እና ከምክክሩ በኋላ ኮሚሽኑ መግባባት ላይ የሚደርስበት አጋጣሚዎች ካሉ ሕገ መንግሥቱ ጊዜ ቢወስድም ሊሻሻል የሚችልበት ዕድል እንዳለ ገልፀዋል።

የሕገ መንግሥት እና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተሩ በተጨማሪ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የማኅበረሰቡ ስምምነት እንደመሆኑ መጠን በስሜታዊነት ተነሳስቶ መቀየርም ሆነ ማሻሻል እንደማይቻል በመረዳት፣ ሠፊ ውይይት እና አገራዊ መግባባት ላይ ተደርሶ የሚሻሻልበት ኹኔታ ቢፈጠር ጥሩ መሆኑን ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here