በደቡብ ኦሞ ዞን የሰላማጎ ወረዳ አርሶ አደሮች የመሬት ካሳ ለዐሥር ዓመት አልተከፈለንም አሉ

0
1085

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ሰላማጎ ወረዳ፣ ከ50 በላይ የሚሆኑ የዲሜ ማኅበረሰብ አርሶ አደሮች ከአሥር ዓመት በፊት ለመንገድ ሥራ ተብሎ የተወሰደባቸው መሬት ካሳ እስካሁን እንዳልተከፈላቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

የዞኑና የወረዳው አስተዳደር ‹አኪር ኮንስትራክሽን› ከተባለ አገር በቀል የአስፓልት መንገድ ሥራ ድርጅት ጋር በመሆን፣ የድሜ ማኅበረሰብ አርሶ አደሮች ያላቸውን ተደጋጋሚ የመሠረተ ልማት ጥያቄ በማንሳት የመንገድ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ቃል ገብተውላቸው ስለነበር፣ ለበርካታ ዓመታት አምርተው ይተዳደሩበትን የነበረ መሬታቸውንና ንብረታቸውን ሙሉ ለሙሉ ለመንገድ ሥራ እንዲውል ሠጥተው ነበር፡፡ መሬቱን ለመንገድ ሥራ በሚሠጡበት ወቅት በዞኑና በወረዳው በኩል ቃል የተገባለቸውን ተገቢ የካሳ ክፍያ ቢኖርም፣ ላለፉት አስር ዓመታት ቃል የተገባላቸውን የመሬት ካሳ እንዳላገኙ የማኅበረሰቡ ተወካዮች ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ለአብነትም የእርሻ መሬት፣ በማሳ ላይ ያሉ የንብ ቀፎዎች፣ የጓሮ አትክልትና ቋሚ ሰብሎች፣ ባህላዊ የአምልኮና የመቃብር ቦታዎች ጭምር ያለ ካሳ ክፍያ በመንገድ ሥራዉ ምክንያት የፈረሱ ናቸው ተብሏል፡፡

ነዋሪዎቹ በየደረጃዉ ከወረዳ እስከ ክልል ለሚገኙ የመንግሥት አካላት ቅሬታና አቤቱታቸውን አሰምተው መልካም ምላሽ ሲጠባበቁ የነበሩ ቢሆንም፣ በተቃራኒው ጥያቄ ያቀረቡ ሠላማዊ አርሶ አደሮች በታጠቁ የክልሉ ልዩ ኃይሎች፣ የክልል እና ፌደራል ፖሊሶች ጭምር የማስፈራራት ተግባር ከመፈጸሙ አልፎ፣ አርሶ አደሮቹ ወደ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ተውሰደው በአማካኝ ለአንድ ወርና ከዚያ በላይ ለዕሥርና መንገላታት መዳረጋቸውን ተጠቁሟል።
የወረዳ አስተዳደሩ ለካሳ ክፍያ ጥያቄው ተገቢውን ምላሽ ለመስጠትና ቅሬታውን ለማስተናገድ ፍቃደኛ እንዳልሆነ አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።

በተያያዘም፣ የወረዳው ነዋሪዎች የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአቅራቢያቸው እንዲገነባ ከ2002 ጀምሮ ለ10 ተከታታይ ዓመት ጥያቄ አቅርበው፣ የወረዳው አስተዳደር ትምህርት ቤቱ በ2009 እንደሚገነባና ከ2011 ጀምሮ የመማር ማስተማር ሒደት እንደሚጀመር በሕዝብ ፊት ቃል ገብቶ እና በወረዳ ምክር ቤት ጉባኤም ጭምር አጽድቆ የነበረ ቢሆንም፣ በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት የተገባው ቃል ታጥፎ ትምህርት ቤቱ አይሠራም ተብለናል ብለዋል።

በዚህም፣ በአቅራቢያችን የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመነፈጋችን ልጆቻችንን ለማስተማር 40 እና 50 ኪሎ ሜትር ወደሚርቁ ሌሎች ወረዳዎች ለመላክ በመገደዳችን ለአላስፈላጊ ወጪ ተጋልጠናል ሲሉ አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፣ አዳዲስ ወጣት አርሶ አደሮች አምርቶ ሕይዎታቸውን የሚለውጡበት የእርሻ መሬት እያስፈለጋቸው መምጣቱን ተከትሎ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ የእርሻ መሬት እንዲሠጣቸው ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም፣ መሬት የሌላቸውን አጣሩና እንሠጣችኋለን ከማለት በስተቀር፣ እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ ከወረዳው እያገኘን አይደለም ሲሉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

“በ2012 እንዲሁ ጓሮ ብቻ ኖሯቸዉ እርሻ ማሳ የሌላቸዉን ወጣት አርሶ አደሮችን ለይታችሁ ላኩ፤ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ የመሬት ጥያቄያችሁ ምላሽ ያገኛል” የሚል ደብዳቤ ከወረዳዉ ከተጻፈ እና አመራሩም ሕዝቡን አወያይቶ ተስፋ ከሰጠ በኋላ ተፈጻሚ አላደረገውም ተብሏል፡፡ በአጠቃላይ፣ ለ13 ዓመት ነዋሪው ለወረዳዉ ጥያቄ ያቀረብ ቢሆንም በየዓመቱ ቃል ከመግባት በዘለለ ተግባራዊ ምላሽ እየተሠጣቸው አለመሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ለሰላማጎ ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ታሪኩ አፊጾ ያደረገችው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ አልተሳካም። የደቡብ ኦሞ ዞን መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መላኩ ለማ በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ላነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ እንዳልሆኑ በመግለጽ ስልክ ዘግተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here