ባለፉት ኹለት ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ሲቡ ሲሬ ወረዳ፣ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
የተገደሉት ሰዎች በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ ወንጀል የሚፈጽመውን “የኦነግ ሸኔን” ጥቃት ሸሽተው በአከባቢው በሚገኘው የመጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የነበሩ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ግድያው የተፈጸመባቸው ግለሰቦች የእርሻ ሰብላቸውን ለመሰብሰብ ከመጠለያ ጣቢያ ወጥተው ቀድመው ቀደሞ ይኖሩበት ወደነበረው አካባቢ ባቀኑበት ወቅት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች አክለውም፣ በዞኑ ያለው የጸጥታ ኹኔታ አሁንም አስተማማኝ አለመሆኑን ገልጸው፣ የታጠቁ ቡድኖች በተለያዩ ቦታዎች እንደሚንቀሳቀሱ እና የጸጥታ ችግሩም ማገርሸቱን ጠቁመዋል። በምሥራቅ ወለጋ ሲቡ ሲሬ እና አጎራባች ወረዳዎች የፌዴራል ፖሊስ እና ሌሎች የጸጥታ አካላት ያሉ ቢሆንም፣ ወንጀል ፈጻሚዎቹን እስካሁን በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዳላዋሏቸው ነዋሪዎቹ አክለው ተናግረዋል።
በሲቡ ሲሬ እና ነኖ ወረዳ በሚገኙ የመጠለያ ጣቢያ ከ 20 ሺሕ በላይ ተፈናቃይ ዜጎች ተጠልለው እንደሚገኙ የጠቆሙት ተፈናቃዮች፣ በየወሩ ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ግራም ስንዴ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን፣ ዕርዳታው በቂ ካለመሆኑ ባሻገር በወቅቱ እንደማይደርሳቸው አስረድተዋል። የክልሉ መንግሥት እና የዞኑ አስተዳደር በየወቅቱ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር መፍትሔ አግኝቶ ተፈናቃይ ዜጎች ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንደሚመልሱ ቢናገሩም፣ አዲስ ማለዳ መረጃውን እስካጠናቀረችበት ጊዜ ድረስ ምንም ዓይነት መፍትሔ አለመሰጠቱ ተገልጿል።
ከ45 ቀናት በፊት በምሥራቅ ወለጋ ዞን ሲቡ ሲሬና ጎቡ ሰዩ በሚባሉ ወረዳዎች መካከል ሰዎች መታገታቸውን የዞኑ አስተዳደር ማረጋገጡ አይዘነጋም። የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አለማየሁ ተስፋ በወቅቱ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን በሠጡት ማብራሪያ ታገቱ ስለተባሉት ሰዎች እያጣሩ እንደሚገኙ መናገራቸው ይታወሳል።
አስተዳዳሪው በማብራሪያቸው ሰዎቹ የታገቱት በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የሸኔ ቡድን ታጣቂዎች እንደሆነም መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ዋና አስተዳዳሪው በዞናቸው የተለያዩ ሥፍራዎች፣ በተለይም የጸጥታ ኃይሎች በቶሎ በማይደርሱባቸው አካባቢዎች፣ የታጠቁ ሸማቂ ኃይሎች ሰዎችን እንደሚያግቱ ተናግረዋል።
መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀው “ሸኔ ቡድን” ዜጎችን በማገት እና በማፈናቀል ንብረትም ይዘርፋል ሲሉም ተደምጠዋል። በዞኑ ካሉት 18 ወረዳዎች መካከል አምስት በሚደርሱት ወረዳዎች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በደረሱ ጥቃቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ ዕርዳታ የማድረስ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለማየው ተስፋ ማውሳታቸው ይታወቃል። በዞኑ ኪራሙ፣ ዲጋ፣ ስቡ ስረ፣ ጉቱ ግዲና ሌሎችም ወረዳዎች በርካታ ሰዎች የተፈናቀሉባቸው መሆኑንም ከዚህ ቀደም በሰጡት ማብራሪያም አመልክተዋል።
አዲስ ማለዳ ስለጉዳዩ ማብራሪያ ለመጠየቅ ለኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ እና ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ያደረገችው ተደጋጋሚ የስል ጥሪ ምላሽ ባለማግኘቱ የክልሉን መንግሥት አስተያየት ማካተት አልቻለችም።
ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014


