የቀሩት 18 ሺሕ ስደተኞች “እገታ በሚመስል ሁኔታ ላይ” ናቸው ተብሏል
በሕወሓት ቁጥጥር ሥር በሚገኙት የማይ-ዓይኒ እና አዲ-ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ይኖሩ ከነበሩ 23 ሺሕ ገደማ የኤርትራ ስደተኞች መካከል አምስት ሺሕ ገደማ የሚሆኑት የሚደርስባቸውን ጥቃት በመሸሽ አቆራርጠው ወደ አማራ ክልል ዳባት ወረዳ መግባታቸው ተገለጸ።
የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት የኮምዩኒኬሽንና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር በአካል ንጉሤ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ዓዲ-ሓሩሽ እና ማይ-ዓይኒ በሚባሉ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኙ ከነበሩ 23 ሺሕ በላይ ስደተኞች አምስት ሺሕ ገደማ የሚሆኑት ወደ አማራ ክልል ዳባት ወረዳ ገብተዋል።
ወደ ዳባት ወረዳ እየገቡ የሚገኙትም የሚፈጸሙባቸውን ጥቃቶች በመሸሽ እና ብዙ ፈተናዎችን እና አደጋዎችን አልፈው እንደሆነ ዳይሬክተሩ አመላክተዋል። መምጣት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እስከ ባለፈው ሳምንት አምስት ሺሕ የሚደርሱ ስደተኞች ወደ አማራ ክልል ዳባት ወረዳ የገቡ ሲሆን፣ በቀጣይም ቁጥራቸው እንዲሚጨምር ነው ያስገነዘቡት።
የሰሜን ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንም፣ ከቀናት በፊት ምዕራብ ጠለምት ወረዳ (ማይጠምሪ) ልዩ ሥሙ አዴ ወሰኔ፣ አዴ ግርማይ፣ ሰረቴያና አዴ ጉባይ ከሚባሉ ቦታዎች በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች የነበሩ የኤርትራውያን ስደተኞች በሕወሓት የሚደርስባቸው ተደጋጋሚ ጥቃት መኖሩን ገልጿል።
ሕወሓት ስደተኞችን ታገሉ በማለት እንደሚያሰቃያቸው፣ አንታገልም ያሉትን ደግሞ በጨለማ ከመጠለያ ጣቢያ ወደማይታወቅ ቦታ እንደሚወስዳቸው ነው የተመላከተው።
እንዲሁም፣ ከስደተኞች መካከል ወደ አማራ ክልል ለመግባት በሚሞክሩበት ጊዜም ንብረታቸውንና ልብሳቸውን ተዘርፈዋል። የአካባቢው የሕወሓት ደጋፊዎችም ወደ አማራ ክልል እናስገባችሁ በማለት ከእያንዳንዳቸው አምስት ሺሕ ብር በመቀበል ከ11 ሰዎች 55 ሺሕ ብር እንደወሰዱባቸውም ነው በዞኑ ኮምዩኒኬሽን በኩል የተገለጸው።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በትግራይ ክልል ይገኝ በነበርው ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ስር ይተዳደሩ በነበሩ አራት መጠለያ ጣቢያዎች 40 ሺሕ ገደማ ኤርትራውያን ስደተኞች ይኖሩ ነበር።
ሆኖም ከጦርነቱ በፊት ሕፃፅ እና ሽመልባ የሚባሉ ኹለት መጠለያ ጣቢያዎች ያላቸው አመቺነት እና ደረጃ ታይቶ ሥደተኞችን ወደቀሩት መጠለያ ጣቢያዎች ለማሸጋሸግ የተደረገ ሙከራ በሕወሃት አስተጓጓይነት ሳይሳካ እንደቀረ እና በጦርነቱ ወቅት ስደተኞች ወደተለያዩ አካባቢዎች ተሰራጭተዋል። ያንን ተከትሎም ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ ዓዲ ሓሩሽ እና ማይ ዓይኒ በሚባሉ መጠለያ ጣቢያዎች 23 ሺሕ አካባቢ ስደተኞች ይገኙ ነበር ብለዋል።
ለእነዚህ ስደተኞችም የምግብ፣ የመድኃኒትና አስፈላጊ ቁሳቁሶች እና አገልግሎቶች አቅርቦት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ያከናውኑ እንደነበር እና ሕወሃት ድጋሚ በአካባቢው ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ አገልግሎት ለመስጠት እንዳልቻሉ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትግራይ ክልልን ለቆ ከወጣ በኋላ፣ የሕወሓት ታጣቂዎች ወደ መጠለያ ጣቢያዎች ገብተው ጥቃት እንደፈጸሙባቸው እና ለሰብዓዊ አገልግሎት ይውሉ የነበሩ ግብዓቶችን እንደዘረፉ አንስተዋል።
በዚህም ታግተው ወዳልታወቀ ቦታ የተወሰዱ ስደተኞች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ስደተኞችን ከችግር ለማውጣት በማለም ከዓለም ዐቀፍ የስደተኞች ተቋም ጋር በመተባበር አማራ ክልል ውስጥ መጠለያ ጣቢያ እንዲገነባ በተደረገ ጥረት ዳባት ውስጥ ዓለምዋጭ የተሰኘ የመጠለያ ማዕከል ተቋቁሞ ስደተኞችን ለማዛወር ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ቢሆንም ሕወሓት የስደተኞችን ጉዳይ እንደ ሰብዓዊ ጉዳይ ለመመልከት ባለመፍቀዱ እና ሂደቱ እንዳይሳካ በማድረጉ ስደተኞች ለተራዘመ ስቃይ መዳረጋቸውን ነው የገለጹት።
ስለሆነም፣ አሁን ላይ በማይ-ዓይኒ እና አዲ-ሐሩሽ የሚገኙ ከ18 ሺሕ በላይ ስደተኞች ‹እገታ› በሚመስል ሁኔታ ውስጥ እንዳሉና አንዳንዶች እየሾለኩ አዲስ ወደተዘጋጀው የዓለምዋጭ የስደተኛ ማዕከል እየመጡ እንደሆነ ተናግረዋል። እዚያ ስላሉትም ሾልከው ከሚመጡትና በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች የተወሰነ መረጃ እንደሚያገኙ የገለፁት ዳይሬክተሩ፣ ያሉበት ሁኔታም ያሳስበናል ሲሉ ተደምጠዋል።
ወደ ተሻለ ቦታ እንዳይዛወሩ ነፃነታቸውን ተነፍገዋል፣ ከታገዱበት ሊለቀቁና ተገቢ የሆነ ማኅበራዊና መሠረታዊ አገልግሎት ወደሚያገኙበት አካባቢ ሊለቀቁ ይገባል። ይህ እንዲሆንም ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ አድርገናል፣ እያደረግንም ነው ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት ዳባት በሚገኙ ስደተኞች ግጭት መፈጠሩን እና አምስት ስደተኞች ላይ ጉዳት መድረሱን አንስተው፣ የተፈጠረው ግጭት በተደራጁ ታጣቂዎች ሳይሆን ውስጥ የተፈጠረ ሳይሆን እንዳልቀረ ተናግረዋል። ስለተፈጠረው ችግር በጸጥታና ሕግ አካላት ምርመራ እየተካሄደበት ስለሆነም ወደ ፊት ይፋ ይደረጋል ነው ያሉት።
በዳባት ዓለም ዋጭ መጠለያ ማዕከል ለሚኖሩ ስደተኞች በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በኩል በዓለም ዐቀፉ የስደተኞች ኤጀንሲ (UNCHR)፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) እና ሌሎች አጋር አካላት ማኅበራዊና መሠረታዊ አገልግሎት እያገኙ መሆኑንና፣ ወደፊት የሚመጡትም በማዕከሉ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚያገኙ ይሆናል ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ 160 ሺሕ የሚሆኑ ኤርትራውያን ስደተኞች እንደሚኖሩ ተመላክቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014


