ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ70 ሺሕ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተለያዩ ጥፋቶችን በፈፀሙ ከ70 ሺሕ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

ከሐምሌ 1/2013 እስከ መጋቢት 30/2014 ባሉት ዘጠኝ ወራት ጥፋት የፈፀሙ ከ70 ሺሕ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እንደተወሰደ እና፣ በዛም 29 ሚሊዮን 327 ሺሕ 109 ብር ገቢ መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አረጋዊ ማሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ መስመር በማቆራረጥ የሚጭኑ 2 ሺሕ 225፣ መስመር ባለመሸፈን 1 ሺሕ 618፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈል 349፣ ከመጠን በላይ በመጫን 1 ሺሕ 683፣ ታፔላ ባለመስቀል 1 ሺሕ 50፣ ታሪፍ ዝርዝር ባለመስቀል 2 ሺሕ 53፣ ከመስመር ውጭ በመጫን 44፣ ከተፈቀደው አገልግሎት ውጪ በመስጠት 171፣ ከተርሚናል ውጪ በመጫን 25፣ ተሳፋሪ በማጉላላት 23 ሺሕ 272፣ በተጨማሪ በተያያዥ ጉዳዮች 39 ሺሕ 984 አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት እርምጃዎች ውስጥ መስመር በማቆራረጥ 1 ነጥብ 52 ሚሊየን ብር፣ መስመር ባለመሸፈን 1 ነጥብ 53 ሚሊዮን ብር፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈል 339 ሺሕ ብር፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈል 1 ነጥብ 472 ሺሕ ብር፣ ከመጠን በላይ በመጫን 401 ሺሕ ብር፣ ታፔላ ባለመስቀል 199 ሺሕ ብር፣ የታሪፍ ዝርዝር ካልሰቀሉ 30 ሺሕ ብር፣ ከመስመር ውጭ የተንቀሳቀሱ 90 ሺሕ ብር፣ ከተፈቀደው አገልግሎት ውጭ የተንቀሳቀሱ 14 ሺሕ ብር፣ ከተርሚናል ውጪ የጫኑ 14 ሺሕ ብር፣ ተሳፋሪ በማጉላት ከተከሰሱ 7 ነጥብ 621 ሺሕ ብር፣ በተያያዥ ጉዳዮች 16 ነጥብ 88 ሚሊዮን ብር የቅጣት ገንዘብ ገቢ መደረጉንም ኃላፊው ጠቁመዋል።

ከዚህ ባሻገር የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በየቀኑ ስምሪት ውስጥ የገቡ ተሽከርካሪዎችን መረጃ በመሰብሰብና ያንን መሠረት በማድረግ በሁሉም አገልግሎት መስጫ መስመሮች ላይ በኹለት ፈረቃ የቁጥጥር ሥራ በመካሄድ ላይ ይገኛል ተብሏል።

በቁጥጥር ሂደቱ የገቡና ያልገቡ ተሽከርካሪዎች መረጃ ለሚመለከተው ቅርንጫፍ የማሳወቅ እና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ሥራም እየተከናወነም እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
በልዩ ሁኔታ የመልካም አስተዳደር ችግር አለባቸው የተባሉ የስምሪት መስመሮች ተለይተው ራሱን የቻለ ኮሚቴ ተዋቅሮ ለማስተካከል እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን እና በዋና ዋና ችግሮች ምክንያትም ድንገተኛ የመስክ ላይ የቁጥጥር ሥራ በመከናወን ላይ ነው ተብሏል።

የትራንስፖርት ዘርፉንና በስር ያሉ ተቋማት ውስጥ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍና የትራንስፖርት ችግሩን ለማቃለል፣ እንዲሁም የአሠራር ስርዓቶች ለማዘመን፣ ፍትኀዊና ተደራሽ ለማድረግ፣ በዘርፉ የሚታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ማለትም የሌብነት ተግባራትን በማክሰም፣ የአገልግሎት ፈላጊ ኅብረተሰብ እርካታ ለማረጋገጥ የሚያስችል የአደረጃጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ቢሮው ተናግሯል።

የዘርፉን አሠራር በጥናት በመፈተሽ የማስተካከል እንዲሁም በየጊዜው የሚያጋጥሙና በዘርፉ የሚታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የሌብነት ተግባራትን በማክሰም የትራንስፖርት ዘርፉን ችግር ለማቃለል የሚያስችል አሰራር በዘላቂነት መዘርጋት እንደሚጠይቅም ቢሮው ገልጿል።

በዚህም የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎች ውስጥ ጥራት ያለው ዕቅድ የማዘጋጀት፣ በተዘጋጀው ዕቅድ ላይ ከአመራር ጋር ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ በዝግጅት ምዕራፍ ዕቅዶችን ለመፈፀም ጥረት ተደርጓል የተባለ ሲሆን፣ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ተግባራትንና በውስንነት የታዩትን ችግሮች በመገምገምና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ በቀጣይ የማጠቃለያ ምዕራፍ ለማናከወን የታቀዱ እቅዶች በተያዘላቸው የድርጊት መርሃ ግብር መሠረት ተፈፃሚ ይሆናሉ ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here