መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናጥሬ ጨው ወደ ትግራይ ክልል በሕገ ወጥ መንገድ እየተላለፈ ነው ተባለ

ጥሬ ጨው ወደ ትግራይ ክልል በሕገ ወጥ መንገድ እየተላለፈ ነው ተባለ

ጥሬ ጨው በአማራ ክልል በሚገኙ የወሰን ስፍራዎች በኩል ወደ ትግራይ ክልል በሕገ ወጥ መንገድ እየተላለፈ መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ በራያ ቆቦ የተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በትግራይና በአማራ ክልል አዋሳኝ ስፍራዎች የሚገኙ የአማራ ተወላጆች ጥሬ ጨውን ተደብቀው በማስተላለፍ ከሚሸጥበት መደበኛ ዋጋ ዕጥፍ በላይ እየሸጡ ነው ሲሉ ጌታሁን ውቡ የተሰኙ ነዋሪ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ጥሬ ጨውን የሚያስተላልፉት፤ በራያ ቆቦ የተለያዩ ቀበሌዎች እና ከቆቦ ከተማ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው ተኩለሽ ከተማ ያሉ አንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው።

አስተላላፊዎቹ ዋጃ፤ ጥሙጋ እንዲሁም ደብረ ዘመዳ ተብለው በሚጠሩ የድንበር አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆኑ፣ ከትግራይ ክልል ነዋሪዎች ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች መሆናቸው ነው የተገለጸው።

ማኅበረሰቡ ጥሬ ጨውን ወደ ትግራይ ክልል የሚያስተላልፈው በውድ ዋጋ ስለሚሸጥ ነው ሲሉ ጌታሁን ምክንያቱን አብራርተዋል። በተያያዘም የዋጋውን ልዩነት ሲያነጻጽሩ ‹‹በቆቦና በተኩለሽ ከተማ የአንድ ኪሎ ጥሬ ጨው ዋጋ 60 ብር የነበረ ሲሆን፤ በድንበር ሥፍራዎች ግን 200 ብር ነው የሚሸጠው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፤ ይህ ድርጊት ጥሬ ጨውን ከመደበኛ ዋጋው እንዲንር አድርጎታል።

ሀብታም አበበ የተባሉት የተኩለሽ ከተማ ነዋሪ፤ ‹‹ጥሬ ጨው ወደ ትግራይ ክልል መተላለፍ ከመጀመሩ በፊት አንዱ ኪሎ ሲገዛ የነበረው 60 ብር ነበር። አሁን ግን አንድ ኪሎ 100 ብር ገብቷል” በማለት ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

በተያያዘም በማዳበሪያ ጨው ጠቅልሎ የሚጓዝ አብዛኛው ሰው ጥሬ ጨውን ለምግብነት ብሎ ከገዛ በኋላ በድንበር አካባቢ ላሉ ሰዎች የሚያቀብል ነው ሲሉ ያመላከቱ ሲሆን፤ አዲስ ማለዳም በቦታው ተገኝታ የንግድ ሂደቱን ዐይታለች።

ድርጊቱ እየተፈጸመ ያለው በተለይም የዋጃ፤ የጥሙጋ እና የአላማጣ ነዋሪዎች ወደ ቆቦ ከተማ ከመጡበት ከመጋቢት 2014 ጀምሮ መሆኑን ሀብታም ጠቁመዋል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት፤ ወደ ትግራይ ክልል እንደ ጥሬ ጨው የተጋነነ ባይሆን በሕገ ወጥ መንገድ እየተላለፈ ያለው የጥይት ፍሬም ጭምር መሆኑን ነው።

ጥላሁን ዓለሙ የተባለ ወጣት ‹‹ወደ ትግራይ ክልል የሚተላለፈው ጥሬ ጨው ብቻ ሳይሆን ጥይትም ጭምር ነው። ከበርበሬው ዛላ ውስጥ በማድረግ የጥይት ፍሬ የሚያስተላልፉ ሰዎች አሉ›› ብሏል።

በአንድ ኪሎ በርበሬ ዛላ ውስጥ የሚተላለፈው ጥይት ቀላል አይደለም ያለው ጥላሁን፤ በኬላ ያሉ ሰዎች ከእስከ አሁኑ በላይ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ወጣቱ አክሎም፣ ብርም በሕገ ወጥ መንገድ እየተላለፈ ነው ብሏል። በተያያዘም ‹‹ሰሞኑን አንዲት ሴት ከቆቦ ከተማ 130 ሺሕ ብር ይዛ ወደ አላማጣ ስትሄድ ኬላ ላይ ተይዛ ብሩን ተወርሳለች።›› ነው ያለው።

ከላይ ከተጠቀሱት ቁሳቁሶች በተጨማሪ ዝንጅብል፤ ጥራጥሬ፤ በይበልጥ ግን ጥሬ ጨውና ብር ወደ ትግራይ ክልል እየተላለፈ መሆኑን ነዋሪዎቹ በተደጋጋሚ ይናገራሉ።
አዲስ ማለዳ በኬላ ቁጥጥር የሚያደርጉ ሚሊሻዎችንና ፋኖዎችን ያነጋገረች ሲሆን፤ ኃይሉ በሪሁን የተባሉት ሚሊሻም በሕገ ወጥ መንገድ የተለያዩ ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ ክልል እየተላለፉ ነው ብለዋል።

ኃይሉ አክለውም፣ ማኅበረሰቡ ሊሰማን አልቻለም። እኛም ቁጥጥራችንን እንቀጥላለን ነው ያሉት። ሞገስ ጎበዜ የተባሉት ፋኖም፣ “ከቆቦ ወደ ተኩለሽ በሚወስደው መንገድ ብቻ እንኳ ሦስት ኬላዎችን አዘጋጅተን እየተቆጣጠርን ነው። በዚህ ምክንያት አስተላላፊዎቹም አሁን አሁን በእነዚህ መስመሮች እየቀነሱ ነው ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች