መሠረት በቃሉ (ስሟ የተቀየረ) ከአረብ አገር ከመጣች ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ አልሆናትም። አነስተኛ ቡና ቤት ከፍታ በመሥራት ላይ ትገኛለች። በአረብ አገራት እየተዘዋወረች ስምንት ዓመታትን ብትቆይም ይኖረኛል ብላ ያሰበችውን ያህል ለፍታ ማጠራቀም አልቻለችም።
ለአዲስ ማለዳ ስትናገርም፣ ‹‹አረብ አገር ያን ያህል ዓመት መቆየቴ ቤተሰብ መመስረት እንዳልችል ትልቁ ምክንያት ሆኗል። እድሜዬ የሄደውና ትዳር ለመመሥረት አዳጋች የሆነብኝ በዚህ የተነሳ ነው። ስምንት ዓመት መቆየቴ ለብዙዎች የተትረፈረፈ ገንዘብ የሚኖረኝ ቢመስልም አሁን የምኖረው እዚህ በምሠራው እንጂ ይዤው በመጣሁት አይደለም።›› ብላለች።
መሠረት ኢትዮጵያ ከገባች በኋላ መንግሥት ብር ካለሽ የመሥሪያ ቦታ ይሰጥሽ ብሏት እንደነበር ታነሳለች። በወቅቱ ከአረብ አገራት ባዷቸውን ለመጡትም ይሁን እንደኔ ትንሽ ገንዘብ ቋጥረው ለመጡት መንግሥት የሚያቀርበው ትልቁ ድጋፍ መሥሪያ ቦታ ልስጣችሁና ሥሩ የሚል ነበር ትላለች። ሆኖም ባዶ እጃቸውን ለመጡት ይህን ማለት ትርጉም የለሽ ነው የምትለው መሠረት፣ ‹‹እኔም ሊሰጠኝ የነበረው ቦታ ለሥራ ምቹ ያልሆነ ስለነበር ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበርኩም›› ስትል ታስታውሳለች።
እሷ ኢትዮጵያ ከገባች ከወር በኋላ ደግሞ ታናሽ ወንድሟ አረብ አገር ለመሄድ በሱዳን በኩል ተደብቆ ወጣ። ይሁን እንጂ ሊቢያ ላይ በወንበዴዎች መያዙን ተከትሎ 25 ሺሕ ብር ካልተከፈለን እንገድለዋለን በማለት ሰውነቱ ላይ ፕላስቲክ እያንጠፈጠፉ ቪዲዮውን ለቤተሰቦቿ እንዲደርስ አደረጉ።
25 ሺሕ ብር መክፈል ያቃታቸው የመሠረት ቤተሰቦች ለቅሶ ሲያበዙ፣ ምን ልሥራባት እያለች ካስቀመጠቻት ገንዘቧ ላይ ቀንሳ ወንድሟን ላገቱት ወንደቤዎች ላከችላቸው። ወንድሟ ከወራት በኋላ ሳዑዲ ገብቶ በአትክልት ቤት ተቀጥሮ ሲሠራ ከቆዬ በኋላ ድንገት የሳዑዲ መንግሥት ኢትዮጵያዊያንን ማሳደድ ይጀምራል። በዚህም የተነሳ የመሠረት ወንድም ወደ ኢትዮጵያ ላለመመለስ ወደ ገጠር ወጥቶ የሚችለውን ኹሉ ሲያደርግና ሲሹለከለክ ከቆየ በኋላ መያዙ አልቀረም።
አሁን ስቃይ በበዛባቸው፣ ውሃና ምግብ እንደልብ በማይገኝባቸው የሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ ታጉሮ የሚገኝ ሲሆን፣ እስር ቤቱ ውስጥ ያለው ረሃብ አስከፊ በመሆኑ፣ ለረሃብ ማስታገሻ የሚሆን ምግብ ግዛበት ብላ እስከ አሁበን 10 ሺሕ ብር እንደላከችለት ትገልጻለች።
በቅርቡም መንግሥት ወደ አገር ከሚያስመጣቸው ስደተኞች አንዱ የእኔ ወንድም ነው ያለችው መሠረት፣ ከተመለሰ በኋላም እንደማያቸው እንደብዙዎች ሱሰኛ ወይም ‹ንክ› ሆኖ እንደሚኖር ነው የሚሰማኝ የሚል ስጋት እንዳላት አልሸሸገችም።
እጅ እግራቸውን ብቻ ይዘው የተመለሱ የማውቃቸው ብዙ ሰዎች በሱስና በሌላ ሕገወጥ ተግባር ተዘፍቀዋል ነው የምትለው። እንዲሁም ገጠር ባል አግብተው የተቀመጡ ሴቶች እንዳሉ ከጠቀሰች በኋላ፣ መኖርና መለወጥ በአገር ነው ብለው ጠንክረው ሠርተው የተሻለ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከስደት ተመላሾችንም አውቃለሁ ብላለች።
ሴቶች አረብ አገር ከሄዱ በኋላ ተዘዋውረው እንዳይሠሩ እንደገቡ ፓስፖርታቸውን ይነጠቃሉ። ብዙዎች የሚደርስባቸው ስቃይም እልፍ ነው። እንዲያም ሆኖ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከተያዙ ቀጥታ ወደ አገራቸው እንደሚላኩ ስለሚያውቁ ላለመያዝ የሚችሉትን ኹሉ ጥረት ያደርጋሉ።
‹‹ይህ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ጉዳይ ነው። ሰው አገር እያለው አገሬ አትመልሱኝ እባካችሁ ሲል አንገት ያስደፋል። ዜጎች ከአገራቸው ወጥተው በመሰደድ የሚደርስባቸው ስቃይና እንግልት እንዲሁም የሚያጡት ክብር መቆም አለበት።›› ትላለች መሠረት።
‹‹ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥም በውጭም ይህን ያህል መከራ ስለምን እንደሚደርስብን አላውቅም። ብቻ ግን መንግሥት ስደተኞችን ለማስመለስ የሚሠራው ሥራ የሚመሰገን ነው። ሆኖም ከተመለሱ በኋላ እንዲቋቋሙና ሌሎችም እንዳይሰደዱ ዘወትር ለዜጎች ኑሮ መሻሻል እና ለኢትዮጵያ ብልጽግና ጠንክሮ ሊሠራና ዜጎችንም ሊያሠራ ይገባል።›› ስትል ገልጻለች።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ጥሩ ገቢ እናገኛለን፣ በጥቅሉም የተሻለ ኑሮ እንኖራለን በሚል በርሃ አቋርጠውና ባህር ተሻግረው ወደተለያዩ አገራት ሲሰደዱ ማየት የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ብዙዎች እንደርስበታለን ያሉት አገር ሳይደርሱ መንገድ ላይ የመቅረታቸው ዜና ተደጋግሞ ይሰማል። ካሰቡት ከደረሱት ሰዎች ውስጥም ብዙዎች ነገሩ እንዳሰቡት ሳይሆን ሲቀርና የተለያየ ስቃይ ሰለባ ሆኑ ሲባል መስማትም የቆየ ነው።
በተለይም በአረብ አገራት በርካታ ኢትዮጵያውያን በሕጋዊም ይሁን በሕገወጥ መንገድ ተሰደው ስለመኖራቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሆኖም ግን በእነዚህ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ይደርሳል ተብሎ የሚነገረው ስቃይም ለጆሮ የሚከብድ ነው።
ብዙዎች በአሠሪዎቻቸው ከሚደርስባቸው በደል በተጨማሪ ስቃይ በበዛባቸው እስር ቤቶች ታጉሩው እንደሚገኙ እና በእስር ቤቶች ውስጥ ሴቶች፣ ሕጻናትና አቅመ ደካሞች ጨምሮ፣ በአጠቃላይ በስቃይ የሚኖሩ በቁጥር በርከት ያሉ ዜጎች መኖራቸው ይገለጻል።
ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር አንስቶ በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአገሬው የጸጥታ አካላት እስራት እና እንግልት እየደረሰባቸው ነው። ያንን ተከትሎ፣ የእነዚህ ዜጎች ስቃይ ተደጋግሞ ከተገነገረ በኋላ ከሰኔ ወር ማገባደጃ ጀምሮ መንግሥት በሳዑዲ ዐረቢያ እስር ቤቶች እየተሰቃዩ ያሉ 40 ሺሕ ያህል ዜጎችን አስመልሳለሁ በሚል ዘመቻ መጀመሩ የሚዘነጋ አይደለም።
በዚህም በይበልጥ ከጅዳ እና ሪያድ አካባቢዎች ያሉ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ በየቀኑ የአውሮፕላን በረራዎችን በማድረግ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ስደተኞች ሲመለሱ ቆይቷል።
ሆኖም የተጀመረው 40 ሺሕ ዜጎችን የማስመለስ ተግባር ሳይጠናቀቅ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ደግሞ በአፈሳ መልኩ በድንገት እየተያዙ ታስረዋል። ስለዚህም በአፈሳ የተያዙ ዜጎች ጉዳይ ወደ አገር ለመመለስ የተዘጋጁት 40 ሺሕ ኢትዮጵያውያንን የመመለስ ዘመቻ ከተጠናቀቀ በኋላ ቀጥሎ እንደሚካሄድ ነበር እቅድ የተያዘው። በዚህም እስከ አሁን ድረስ በየሳምንቱ በአረብ አገራት በተለይም በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ስደተኛ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሱ መሆኑ ይታወቃል።
ብዙዎች በሳዑዲ ዐረቢያ ቆይታቸው ያፈሩት ሀብትና ንብረት ያላቸው በመሆኑ ሀብትና ንብረታቸውን ሳይወስዱ ባዶ እጃቸውን ወደ አገር የተመለሱ ናቸው። ሌሎች ደግሞ ባዶ እጃቸውን መመለስ የለባቸውም ተብሎ ከኢትዮጵያ በኩል ለሳዑዲ አረቢያ መንግሥት አቤቱታ ቀርቦ እንደነበር ይታወሳል።
በወቅቱ በተደረገው የማስመለስ ዘመቻም ኹለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከኹለት ሺሕ በላይ ጨቅላ ሕጻናት፣ ከ34 ሺሕ የሚልቁ ሴቶች እና ከሦስት ሺሕ ያላነሱ ወንዶችን ጨምሮ በድምሩ ከ41 ሺሕ የሚበልጡ ዜጎች ወደ አገራቸው ተመልሰዋል መባሉ ይታወሳል። ከዚህ በመቀጠልም ከ69 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ስደተኞችን ከሳዑዲ ለማስመለስ እንደታቀደ ተሰምቶ ነበር።
ከስደት ተመላሾቹ ጊዜያዊ መጠለያ እንደሚያርፉ እንዲሁም፣ መንግሥት እነዚህ ዜጎች ወደ ትውልድ ቦታቸው እንዲጓዙ የትራንስፖርት ወጪያቸውን በመሸፈን የኪስ ገንዘብ መስጠቱን በመጠቆም፣ በቀጣይነትም የሚቋቋሙበትን መንገድ የማመቻቸት ሥራ ይከናወናል ሲል ገልጾ ነበር።
በተለይ ከሳዑዲ ዜጎችን የመመለስ ተግባር የተጀመረው በቅርብ ጊዜ ሳይሆን ከአምስት ስድስት ዓመት በፊትም በየሳምንቱ ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረግ ነበር። ሆኖም ግን ብዙዎች ከመጡ በኋላ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ከመግባታቸው ባለፈ ተመልሰው ለስደት የሚዳረጉ ስለመኖራቸውም ይነገራል።
ይኸው ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ እንዳይሆን ከስር መሰረቱ ሊሠራበት ይገባል ሲሉ የመንግሥት አካላት ሳይቀር ሲገልጹ ቢሰማም፣ እውነታው የሚባለውን ያህል እንዳልሆነ የሚገልጹ አሉ።
መንግሥት ለሚመለሱ ዜጎች ራሳቸውን ለማቋቋም በቂ ዝግጅትና ቁርጠኝነት ከሌለው መመለሱ ብቻውን ፋይዳ የለውም ሲሉ የሚገልጹ ብዙዎች ናቸው። ከሚመለሱት ውስጥ በተለያዩ ወንጀሎች ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ መኖራቸው የሚነሳ ሲሆን በሽብር፣ ሌብነት፣ ሱስ እና ሌሎች ሕገወጥ ተግባራት ውስጥ መግባታቸውም በማኅበረሰቡ ላይ ከሚፈጥሩት አሉታዊ ጫና ባለፈ ራሳቸውም ዞረው እስር ቤት ውስጥ እንዲገኙ ያደርጋቸዋል ነው የሚባለው።
ስለሆነም እነዚህ ዜጎች በአገራቸው ሠርተው የሚለወጡበትን እና ማኅበረሰባቸውን የሚጠቅሙበትን መንገድ አስመልክቶ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ፣ ምቹ የሥራ ሁኔታን መፍጠር እንዲሁም እገዛና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ይገለጻል።
ብዙዎች ከደረሰባቸው ጥቃት የተነሳ የጤና እንዲሁም የሥነልቦና ቀውስ እንዳጋጠማቸው ነው የሚነገረው። አሁንም ለሚመለሱት በቋሚነት ራሳቸውን ችለው እንዲሠሩ ለማድረግ ሁኔታዎች ሊመቻችላቸው እንደሚገባ ብዙዎች አጽንዖት ይሰጣሉ። ይህም ሲሆንና ኹሉም በአገሩ ሠርቶ መኖር ሲችል የዜጎች ስደት ማብቃት እንደሚችል ይታመናል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አፍሪካ አገራት ዜጎች በአገራቸው ያለውን የእርስ በእርስ ጦርነትና ድህነት በመሸሽ ለስደት ይጋለጣሉ። በዚህም ያፈሩትን ሀብት ንብረት ከመነጠቅ ጀምሮ የጉልበት ብዝበዛ፣ ጾታዊ ጥቃት እንዲሁም የተለያዩ አስከፊ የመብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙባቸው ነው መረጃዎች የሚገልጹት።
ሆኖም መንግሥት ስደተኞችን ማስመለስ ከጀመረ አንስቶ በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ምን እየተደረገ ነው ለሚለው ምላሽ ‹ስደተኞች እንደመጡ ሥራ መፍጠር አይቻልም። መጀመሪያ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማገናኘት ይቀድማል› ሲል ይደመጣል።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ስር ከመልሶ ማቋቋም ጋር በተገናኘ በተቋቋመ ኮሚቴ ውስጥ የሚሠሩና ሥማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የሥራ ኃላፊ፣ በተለይ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በአዲስ ዘመቻ 102 ሺሕ ዜጎችን ለመመለስ እየተሠራ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። እስከ አሁንም ከ8 ሺሕ 300 ያላነሱ ዜጎች መምጣታቸውን ገልጸው፣ ቀሪዎቹን በሳምንት ኹለት ጊዜ ሆኖ በቀን ሦስት ጊዜ በሚደረግ በረራ በሰባት ወር ውስጥ ለማስገባት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ከስደት ተመላሾች አየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላም አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ ሰባት መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንዲያርፉ እንደሚደረግና የፈለጉ መቆየት የሚችሉ መሆኑን አንስተዋል። ማገገም የማያስፈልጋቸው፣ ቤተሰብ በቅርብ ያላቸው እንዲሁም የኪስ ገንዘብ ያላቸው በገቡ በኹለት ቀናት ውስጥ ወደ ትውልድ ቤተሰቦቻቸው እንደሚያቀኑም አክለዋል።
ስደተኞች ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ማቋቋም ስለሚያስፈልግም፣ ለዚሁ ዓላማ ተብሎ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ ስለመኖሩም አውስተዋል። ሆኖም ፌዴራል መንግሥቱ የሚመድበውና የልማት አጋሮች የሚለግሱት ሀብት ስላለ ይህ ተሟልቶ ሲሰጠን ወደ ሥራ እንገባለን ብለዋል።
አሁን ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ያለው ከማቋቋም ሥራ ይልቅ ስደተኞችን የመመለስ ተግባሩ መሆኑን የገለጹት የሥራ ኃላፊው፣ ክልሎችን በመጥራት ከመልሶ ማቋቋም ጋር በተገናኘ አቅጣጫ ተሰጥቷቸው እንደተመለሱ ጠቁመዋል።
ብሔራዊ ኮሚቴው ባስቀመጠው እቅድ መሰረት የሥራ ዕድል መፍጠሪያና ማቋቋሚያ ገንዘብ እንዲሰጠን ጠይቀንም ውሳኔ እየጠበቅን ነው ብለዋል። ሆኖም ኮሚቴያቸው ገንዘብ ከተለቀቀለት በኋላ ምን ዓይነት የማቋቋም ሥራዎችን ሊሠራ እንደሚችል ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
አዲስ ማለዳ እስከ አሁን ለአጠቃላይ ከስደት ተመላሾች ምን ዓይነት የማቋቋም ሥራዎች እንደተሠሩ እንዲሁም በበጀት ዓመቱ ከስደተኞች ጋር በተገናኘ የተሠሩ የእቅድ ሥራዎችን አስመልክቶ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ብትጠይቅም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንደ አዲስ በመደራጀት ላይ ስለሆንኩኝ መረጃ ለመስጠት እቸገራለሁ ሲል ገልጿል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ስደተኞችን የመመለስ ተግባሩን እያሳለጠ እንደሚገኝ የሚነገረው፣ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ስለጉዳዩ በስልክ ማብራሪያ መስጠት አልችልም በማለቱ ምላሹን ማካተት አልተቻለም።
ከደርግ ዘመነ መንግሥት ማብቂያ ጀምሮ እስከ አሁን በየዓመቱም በርካታ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የአገራቸውን ድንበር አቋርጠው በሕገወጥ መልኩ እንደሚሰደዱ እና ብዙዎችም መንገድ ላይ እንደሚቀሩ ይነገራል። በርካታ ከስደት ተመላሾች ኢትዮጵያውያን መኖራቸውም እንዲሁ የታወቀ ሲሆን፣ ከተመለሱ በኋላ በአገራቸው ሠርተው ለመለወጥ የካፒታል እንዲሁም የክህሎት እጦትን ጨምሮ እጅግ በርካታ መሰናክሎች ስለመኖራቸው ሲገልጹ ይሰማል።
ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014



