ባለፉት አምስት ዓመታት የፕሬስ ነጻነት በዓለማቀፍ ደረጃ ቀንሷል ተባለ

0
590

ከ2008 ጀምሮ እስከ 2013 ድረስ የፕሬስ ነጻነት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ቀንሷል ሲል ዩኔስኮ አስታወቀ።
85 በመቶ የዓለም ሕዝብ በየአገሩ የፕሬስ ነጻነት መቀነሱን ተመልክቷል ያለው ዩኔስኮ፣ በተጠቀሱት ዓመታት 455 ጋዜጠኞች መገደላቸውን ገልጿል።
እንደ ዩኔስኮ ገለጻ፣ ከ2008 (በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ2016) ጀምሮ በ44 አገራት 57 የሚጠጉ ከጋዜጠኝነትና የመገናኛ ብዙኀን ጋር የተያያዘ ሕግና መመሪያዎች ወጥተዋል። እነዚህ ሕግና መመሪያዎች የተሳሳተ እና የተዛባ መረጃ፣ የሳይበር ወንጀል፣ የጥላቻ ንግግርና መሰል ነጥቦች ጋር በተያያዘ በቋንቋ ረገድ በግልጽ ያልተቀመጡ ናቸውም ተብሏል። በዚህም ሳቢያ ለፕሬስ ነጻነት ስጋት ሆነው መቀመጣቸውን ነው ያስታወቀው።
‹ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ› የተሰኘው መረጃን በነጻነት የማግኘት መብት ተሟጋች የሆነ ዓለማቀፍ ድርጅትም በበኩሉ፣ የዓለም የፕሬስ ነጻነት የደረጃ ሰንጠረዥ ያወጣ ሲሆን፣ በዚህም የ180 አገራትና የአምስት ክልሎችን የፕሬስ ነጻነት ከመገናኛ ብዙኀን ራስን መቻል፣ ከብዝኀነት፣ ከሕግ ማዕቀፍ ጥንካሬ እንዲሁም ከጋዜጠኞች ደኅንነት አንጻር ቃኝቷል።
በዚሁ የ2022 የዓለም የፕሬስ ነጻነት የደረጃ ሰንጠረዥ መሠረት፣ ኤርትራ የፕሬስ ነጻነት የላቸውም ወይም መጥፎ ደረጃ ላይ ናቸው ከሚባሉ አገራት ተርታ በቀዳሚነት ተቀምጣለች። በመቀጠል ሰሜን ኮሪያ፣ ቱርክሜኒስታን፣ ቻይና እና ጅቡቲ በተከታታይ ተቀምጠዋል። በዓመቱ በአውሮፓ ከፍተኛ የሚባል የፕሬስ ነጻነት ታይቷል ያለው ‹ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ›፣ ያም ቢሆን ግን አሁንም በጋዜጠኞች ላይ የሚደርስ ጥቃት እንደጨመረ አስታውቋል።
ኖርዌይ በፕሬስ ነጻነት አንደኛ ሆና ስትቀመጥ፤ ጎረቤቷ ፊንላንድ ኹለተኛ፤ እንዲሁም ስዊድን፣ ዴንማርክ እና ኮስታሪካ በተከታይነት ቅደም ተከተሉን ይዘዋል።
በተያያዘ ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (ሲ.ፒ.ጄ.) ባወጣው ዘገባ፣ በ2022 እስከ አሁን ድረስ 27 ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኀን ባለሞያዎች ተገድለዋል ብሏል። ከነዛ መካከልም 11 የሚሆኑት በቅርቡ በሩስያ እና በዩክሬን መካከል ከተነሳው ጦርነት ጋር ተያይዞ ዩክሬን ውስጥ የተገደሉ መሆናቸውን ጠቅሷል።
ኮሚቴው ባለፈው ዓመት 293 ጋዜጠኞች በዓለማቀፍ ደረጃ ታስረዋል ያለ ሲሆን፣ ቻይና 50 ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚ መሆኗንም አያይዞ አስቀምጧል። ማይናማር፣ ግብጽ፣ ቬትና እና ቤላሩስ ጋዜጠኞችን በማሰር ቻይናን ይከተሏታል። ከዚህ በተጓዳኝ በዚህ ዓመት ብቻም ቢያንስ 65 ጋዜጠኞች የደረሱበት እንዳልታወቀና እንደጠፉ ነው ሲፒጄ ያስታወቀው ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።
የ2014 የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ‹ጋዜጠኝነት በዲጂታል ከበባ› በሚል መሪ ቃል በመላው ዓለም የሚከበር ሲሆን፣ በዚህም የዲጂታል ዘመን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የጋዜጠኞች ደኅንነት እንዲሁም የመረጃ ተደራሽት ላይ ያለው ተጽእኖ ትኩረት ያገኛል ተብሏል። ኢትዮጵያም የፕሬስ ነጻነት ቀንን ዘንድሮ ለ31ኛ ጊዜ ታከብራለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here