በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ የሚገኘው በዋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሕወሓት ሙሉ ለሙሉ እንደወደመና ጥገና ስላልተደረገለት ትምህርት መጀመር እንዳልተቻለ አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
ተቋሙ በሕወሓት ከፍተኛ ደረጃ ጥቃት እንደደረሰበትና ጥገና ስላልተደረገለት ትምህርት መጀመር እንዳልተቻለ የበዋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሱፐርቫይዘር ሞላ ዋሴ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሞላ አክለውም ሌሎች ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዳስጀመሩ ጠቁመው፤ በዋ ግን መጀመር እንዳልተቻለና እስከ አሁን ጥገና እንዳልተጀመረለትም ነው ያብራሩት።
በሌላ በኩል በጦርነቱ ምክንያት በወደሙና ጥገና ባልተደረገላቸው ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ አስቸጋሪ በመሆኑ በትምህርት ገበታ የሚገኙ ተማሪዎች ቁጥር እያሽቆለቆለ መሆኑም ተመልክቷል።
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ስር የሚገኙ በርካታ የትምህርት ተቋማት ጥገና ስላልተደረገላቸው የተማሪዎች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑንም የቂልጡ ዲቡስቃ ሱፐር ቫይዘር ማህሌት አዲስ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ማህሌት በራያ ቆቦ ወረዳ ውድመት ከደረሰባቸው የትምህርት ተቋማት የቂልጡ ዲቡስቃ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባር ቀደም መሆኑን ገልጸው፤ በተሸነቋቆረ ተቋም ማስተማር ስለሚያስቸግር የተማሪዎች ቁጥር ቀንሷል ብለዋል።
አያይዘውም በቂልጡ ዲቡስቃ ትምህርት ቤት እስከ ዛሬ ከአንድ እስከ አራት ባሉት ክፍሎች ከ280 በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ይከታተሉ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን በትምህርት ገበታ ያሉት 68 ተማሪዎች ብቻ ናቸው ነው ያሉት።
ከዚህም በተጨማሪ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ የትምህርት ደረጃ ያሉ ተማሪዎችን የሚያስተናግደው ወርቄ ገበያ ትምህርት ቤት፣ ጦርነት ባልተከሰተበት ወቅት 773 ተማሪዎችን ይቀበል እንደነበር የገለጹት ማህሌት አሁን 552 ተማሪዎች ናቸው ያሉት ብለዋል።
በተለይም የቂልጡ ዲቡስቃ ትምህርት ቤት በከፋ ሁኔታ ወድሟል የሚሉት ማህሌት፤ ያሉትን ተማሪዎች የሚያስተምሩት ድንኳን ተክለው እንደሆነ ጠቁመዋል። ድንኳኑን በመጋረጃ ከፋፍለው ሲያስተምሩ ድምጽ ስለሚሰማ የመማር ማስተማር ሂደቱ የተረበሸ መሆኑንም አብራርተዋል።
በሌላ በኩል በቂልጡ ዲቡስቃ ትምህረት ቤት ዙሪያ ያሉ 81 የነዋሪዎች ቤት በሕወሓት ታጣቂዎች እንደተቃጠሉ የጠቆሙት ማህሌት፤ በዚሁ ሰፈር የነበሩ ነዋሪዎች መጠለያ ስለሌላቸው ተማሪዎቹም ትምህርታቸውን መከታተል አልቻሉም ሲሉ ገልጸዋል።
ጉዳዩን ለራያ ቆቦ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ቢያመለክቱም የወደሙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመጠገን ከ40 ሺሕ ሄክታር በላይ መሆን እንዳለባቸውና ቂልጢ ዲቡስቃ ትምህርት ቤት ግን ይህን መስፈርት አያሟላም የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አስታውሰዋል።
በትግራይ ክልል ድንበር አካባቢ ያሉት የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰባቸው ያነሱት ማህሌት፤ ከድንበር አካባቢዎችም በራያ ቆቦ ወረዳ ብቻ 132 ትምህርት ቤቶች እንደወደሙ ገልጸዋል።
በተያያዘም፤ የወርቄ ገበያ፤ ያያሁም፤ አማሪሳ፤ ከወለጋ፤ ጃርሶድጌ፤ ኢሉ ኪዳነ ምህረት፤ አጋምሳ፤ ቂልጡ ዲቡስቃ፤ በዋ፤ ሮቢት፤ ጎብዬ፤ ተኩለሽ፤ ሸዎች ማርያም እና ሌሎች የትምህርት ተቋማት ውድመት እንደደረሰባቸው ማህሌት አብራርተዋል።
የራያ ቆቦ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መኮንን አጽናፉ በበኩላቸው ፕሮጀክቱን የያዙት አካላት የቂልጢ ዲቡስቃ ትምህርት ቤት ለቅድመ ጥገና የተቀመጠውን መስፈርት አያሟላም ብለዋል ነው ያሉት።
በቅድመ ጥገና እንዲደረግላቸው ዕቅድ የተያዘላቸው የትምህርት ተቋማትም ከ40 ሺሕ ሄክታር በላይ ስፋት ያላቸው መሆኑ ተመላክቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014



