ሰሞኑን በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች ቤንዚን በቀላሉ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል ሲሉ ተጠቃሚዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በዚህም አሽከርካሪዎች በተለይም ደግሞ ቤንዚን በስፋት የሚጠቀሙ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ቤንዚን በቀላሉ በማደያ ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸው፣ አሁን ላይ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱንና በዚህም ምክንያት መቸገራቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ከተማ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ቤንዚን ለማግኘት ለረዥም ሰዓት ተሰልፈው እንደሚውሉ ነው ለማወቅ የተቻለው። በዚህ ሁኔታ ከቀጠሉ ከአንድ ሳምንት በላይ እንደሆናቸው እና አሁኑ ደግሞ ለነገ ሥራ በሌሊት ተነስተው ወረፋ ማስያዝ መጀመራቸውን የባጃጅ አሽከርካሪዎች ገልጸዋል።
ሥማቸውን ለመናገር ፈቃደኛ ያልሆኑ የባጃጅ አሽከርካሪ፣ በእኔ ዕይታ ይህ የሆነው እጥረት ተፈጥሮ አይደለም። ነገር ግን የሚሠራው አሻጥር ነው፣ ከምንሠራበት ይልቅ ወረፋ የምንጠብቅበት ሰዓት እንዲበልጥ ያደረገው ብለዋል።
በክልሉ በምትገኘዋ ሌላዋ ከተማ ደብረ ማርቆስም ሥማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የባጃጅ አሽከርካሪ፣ እንዲሁ አንድ ሊትር ቤንዚን ማደያ ላይ 32 ብር የሚሸጥ መሆኑን ገልጸው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማደያዎች ላይ እንደልብ ማግኘት ባለመቻሉ በጥቁር ገበያ (black market) በእጥፍ ጨምሮ 60 ብር እየተሸጠ ነው ብለዋል።
አዲስ ማለዳ በኢትዮጵያ ባሉ ብዙ ከተሞች ያለውን የቤንዚን አቅርቦት ለማጣራት የሞከረች ሲሆን፣ በየከተሞች ቤንዚን ያላቸው ቸርቻሪዎች እና ማደያዎች ለሚያውቁት ሰው ካልሆነ በስተቀር፣ ለተጠቃሚዎች በፍትሀዊነት መስጠትን እየተዉ መምጣታቸው እና ካለው ቤንዚን አብዛኛው በጥቁር ገበያ እንደሚሸጥ ነው ለማወቅ የተቻለው።
በተለይ ከጥቁር ገበያ አንገዛም በማለት ከማደያ የሚገዙ አሽከርካሪዎች ረዥም ሰዓት ተሰልፎ መጠበቅ ግዴታቸው ሲሆን፣ በአዲስ አበባም እንዲሁ በተለይ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት በሚፈቀድባቸው ቦታዎች ለረዥም ሰዓት ተሰልፈው ቤንዚን ሲጠብቁ ይታያል።
በተለያዩ ከተሞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድ ሊትር ቤንዚን ከ20 እስከ 40 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ በዚህ ዋጋ በማደያዎች በቀላሉ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ ከጥቁር ገበያ ከእጥፍ በላይ በሆነ ዋጋ ለመግዛት እንደሚገደዱ ቅሬታ አቅራቢዎች ተናግረዋል።
ይህ እየሆነ ያለው የነዳጅ እጥረቱ ኖሮ ሳይሆን መንግሥት ጠንካራ ቁጥጥር ሊያደርግ ባለመቻሉ በነጋዴዎችና ደላሎች የሚሠራ የንግድ አሻጥር ስለመሆኑም ተገልጿል።
ይህም አሽከርካሪዎችን እና የትራንስፖርት ተጠቃዎችን ላልተፈለገ ወጪ እየዳረጋቸው መሆኑን ነው ቅሬታ አቅራቢዎች የሚገልጹት።
በቆቦ ከተማም እንዲሁ የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ ከ40 ብር ወደ 100 ብር ከፍ ማለቱንና በተጠቃሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን አዲስ ማለዳ በቅርቡ መዘገቧ ይታወሳል።
በመዲናዋ በጫማ ማጽዳት ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ሳይቀር ቤንዚን በቀላሉ ማግኘት ስላልቻሉ እንዲሁም ቢጠቀሙ የሚገዙበት ዋጋ ከሚያገኙት ትርፍ የላቀ በመሆኑ ብዙዎች ለጊዜው መጠቀም ማቆማቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በዋጋ እየጨመረ የመጣው ነዳጅን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ማስወጣትና በጥቁር ገበያ መገበያየት እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ ዓለማየሁ ፀጋዬ፣ የነዳጅ እጥረት አለ ተብሎ እንደማይታሰብ ገልጸው፣ በእኛ በኩል ጅቡቲ ድረስ በቂ ነዳጅ እናስመጣለን። ከዚያ በኋላ የኩባንያውና የተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ ኃላፊነት ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ሥርጭት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የኮምዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ቁምነገር እውነቱ በበኩላቸው፣ በቂ ነዳጅ መኖሩንና ዋጋውም ባለበት መሆኑን ገልጸዋል። ሆኖም ቤንዚን የለም በማለት እየዘጉ ያሉ ማደያዎች መኖራቸውንም ነው የጠቆሙት።
ይህም የሆነው በዋናነት መገናኛ ብዙኃን ወደፊት ተግባራዊ ይደረጋል ስለተባለው የነዳጅ ውጤቶች መሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አፈጻጸም መመሪያ እና የአሠራር ሥርዓትን በተመለከተ ለሕዝብ የሚያደርሱት የተዛባ መረጃ ነው ብለዋል። በቅርቡ መገናኛ ብዙኀን ተጠርተው ግንዛቤ የተሰጣቸው ቢሆንም፣ ከሄዱ በኋላ ብዙዎች የዘገቡበት መንገድ የተሳሳተ በመሆኑ ማደያዎች እንዲዘጉ ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት።
ኃላፊዋ የዘጉ ማደያዎችን በምንጠይቅበት መንገድ ተጠያቂ እንዲሆኑ እናደርጋለን ብለው፣ መገናኛ ብዙኀንም እንዲህ አይነት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በተገቢው ሁኔታ ተገንዝበው መዘገብ ይገባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014



