ከሳዑዲ አረቢያ ተመላሾች ውስጥ አጥፊዎችን የሚለይ መርማሪ ቡድን ተቋቋመ

0
690

ከሳዑዲ አረቢያ ተመላሽ ዜጎች መካከል ያሉ አጥፊዎችን በምርመራ ለመለየት የሚያስችል የምርመራ ቡድን ወደ ሥራ እንዲገባ አቅጣጫ መሰጠቱን ፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የምርመራ ቡድኑ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ አቅጣጫውን የሰጠው በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ነው ተብሏል። በሰው መነገድና ሰዎችን ድንበር ማሻገር ወንጀሎች ከሳውዲ አረቢያ ተመላሾች መካከል የሚኖሩ አጥፊዎችን ለህግ ማቅረብና የወንጀል ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦች ከመለየት አንፃር ልዩ የምርመራ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ አንዲገባ አቅጣጫ ተሰጥቷል።
መንግሥት በሰዎች የመነገድ ወንጀልና ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና የዚህ ወንጀል ሰለባ የሆኑ ዜጎችን መብት ለማስከበር፣ ተጋላጮችን ለማስተማር የሚያስችሉ የተለያዩ እርምጃዎችን ከመውሰድ ባሻገር ወንጀሉን ለመግታት የሚያስችል የሕግ ሥርዓት የተዘረጋ ቢሆንምና መሻሻሎች ቢታዩም እስከ አሁን ግን የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ማምጣት አለመቻሉ ተገልጿል።
ሕገ-ወጥ ድርጊቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ስር እየሰደደ እና መልኩን በመቀያየር እየተባባሰ በመምጣቱ ዜጎችን ለአስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና እንግልት እየተዳረጉ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም የበኩሉን መወጣትና ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ እንዲሁም የወንጀሉ ተጠቂ ቤተሰቦች ወይም ማኅበረሰቡ አዘዋዋሪዎችን ለሕግ አስከባሪ አካላት መጠቆም ተገቢ እንደሆነ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
የምርመራ ዕቅዱ በፍትሕ ሚኒስቴር ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ከፌደራል ፖሊስ እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለተውጣጡ ባለሙያዎች የቀረበ ሲሆን በዕቅዱ ላይ ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች በአዘጋጆች ተገቢው ምላሽ ተሰጥቷል።
የምርመራ ቡድኑ በንዑስና በቴክኒክ ቡድን ተከፋፍሎ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ አንዲገባ አቅጣጫ በመስጠት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here