ግብርና ሚኒስቴር ኃላፊነት የተሞላበት የመሬት አስተዳደር የጀርመን ተራድኦ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ኃላፊነት የተሞላበት የግብርና ኢንቨስትመንት አገር ዐቀፍ ረቂቅ መመሪያ አዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ አማካሪ ስለሺ ጌታሁን በምክክር መድረኩ ላይ እንደተናገሩት፣ አገር ዐቀፍ ኃላፊነት የተሞላበት የግብርና ኢንቨስትመንት የሥራ መመሪያ ዝግጅት ዘርፉ በተሻለ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣትና የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልፀዋል። በመሆኑም መመሪያውን ማበልፀግና ወደሥራ ማስገባት ልዩ ትኩረት እንደሚሻ አክለው ገልጸዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ ኃላፊነት የተሞላበት የግብርና ኢንቨስትመንት መመሪያ ረቂቅና በዘርፉ የነበሩ ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች ዙሪያ ጥናትዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። ከመድረኩ ተሳታፊዎችም ረቂቅ ሰነዱን ለማበልፀግ የሚያስችሉ ነጥቦች በስፋት ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ባለፉት ዓመታት በግብርና ኢንቨስትመንት አፈጻጸም ረገድ የነበሩ ተግዳሮቶችን በመቅረፍና የመፍትሄ ምክር ሐሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ሳይንሳዊ አሰራሮችን ተከትለው እንዲሠሩ በማድረግ ኢትዮጵያ እንደ አገር ካላት የግብርና ኢንቨስትመንት አቅም ውስጥ 2.4 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት ስድስት ሺሕ ለሚሆኑ የአገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶች በሊዝ ውል ማስተላለፍ ተችሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014


