ከ80 በላይ ሸገር አውቶብሶች በመለዋወጫ እጥረት ከስምሪት ውጭ መሆናቸው ተገለጸ

ከ80 በላይ አውቶብሶች በመለዋወጫ እጥረት ምክንያት ከስምሪት ውጭ መሆናቸውን የሸገር ብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የሸገር ብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሳሙኤል ፍስኃ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ ድርጅቱ 226 መደበኛ አውቶብሶች እና 235 የድጋፍ ሰጪ አውቶብሶችን በአጠቃላይ 461 አውቶብሶችን ስምሪት በማሰማራት ለደንበኞች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ነው። 80 የሚሆኑ መደበኛ አውቶብሶችም በተለያየ የመለዋወጫ እጥረት ምክንያት ከስምሪት ውጪ ናቸው።

ኃላፊው አክለውም ድርጅቱ ከስምሪት ውጪ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት ያደረገ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ብዛት ያላቸው የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን የሚያቀርቡ ድርጅቶች ባለመኖራቸው እና ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ ችግሮች ሳይፈቱ ከ10 ወር በላይ አስቆጥሯል ብለዋል።

ድርጅቱ ከላይ ቁጥራቸው የተጠቀሱ አውቶብሶች ወደ ስምሪት የሚገቡበትን ሂደት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ እየተነጋገረ የሚገኝ ሲሆን ለተሽከርካሪዎች የሚያስፈልጉ መለዋወጫዎችን የመለየት ሥራም ተሠርቷል ተብሏል። ኃላፊው አያይዘውም የመለዋወጫ ግዥ መቼ ተፈጽሞ አውቶብሶች ወደ ስምሪት ተሰማርተው፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣሉ የሚለው ጉዳይ ግን አይታወቅም ሲሉ ገልጸዋል።

የሸገር ብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ ባለፈው ዘጠኝ ወር ከመደበኛ አውቶብስ ትኬት ሽያጭ አገልግሎት 168 ነጥብ 42 ሚሊዮን ብር፣ ከድጋፍ ሰጪ አውቶብስ ትኬት ሽያጭ አገልግሎት ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ያቀደ ሲሆን፣ 107 ሚሊዮን 348 ሺሕ 498 ብር መሰብሰብ ችሏል ተብሏል።

አጠቃላይ በዘጠኝ ወር ውስጥ ድርጅቱ ከድጋፍ ሰጪ ባስ እና ከመደበኛ አዉቶቡሶች ከ285 ሚሊዮን 324 ሺሕ ብር በላይ ከትኬት ሽያጭ መሰብሰቡን አስታውቋል። በተጨማሪ ለተለያዩ ተቋማት የኮንትራት ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት 6.5 ሚሊዮን ብር፣ ከተማሪ የትራንስፖርት አገልግሎት 8.1 ሚሊዮን ብር፣ ከልዩ ልዩ አገልግሎቶች ገቢ 3.8 ሚሊዮን ብር፤ በአጠቃላይ 186.6 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተነግሯል።

የሸገር ብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአውቶቡስ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ብዛት ወደ 42 ሚሊዮን 442 ሺሕ ለማሳደግ እቅድ ይዞ፣ ከ44 ሚሊዮን 193 ሺሕ ላላነሱ ተሳፋሪዎች አገልግሎት መስጠት መቻሉን ጠቁሟል።

ድርጅቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ሽፋን ርቀትን አስመልክቶ 7.8 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር መሸፈን እንደቻለ እና በአጠቃላይ የነጠላ የአውቶብስ ምልልስን 602 ሺሕ 991 ለማድረስ ታቅዶ፣ 694 ሺሕ 265 ምልልስ ማድረግ ተችሏል ተብሏል።

በአጠቃላይ አፈጻጸሙ 115 በመቶ ማሳካት የተቻለ ሲሆን፣ በሁሉም የስምሪት መስመሮች እስከ ሦስት ሰዓት አምሽቶ መሥራት፣ ኅብረተሰቡ ወደ ብዙኀን ትራንስፖርት እንዲያዘነብል ማድረግ በመቻሉ፣ የማበረታቻ ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ ምልልስ እንዲጨምር ማድረግ በመቻል፣ የተቀናጀ አመራር፣ ሠራተኛ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ መቻሉ ለተመዘገበው ውጤት ተጠቃሽ ነው።

ድርጅቱ በመዲናዋ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጥባቸው በ24 መስመሮች ላይ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ባለፈው ዓመት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ የደንበኞች የቆይታ ጊዜ ወደ 13 ደቂቃ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰዋል።

ጥናቱ ከፍተኛ የሕዝብ ትራንስፖርት ፍላጎት ባለባቸው፣ ረዣዥም የጉዞ መስመሮች መነሻ እና መድረሻ ቦታዎች ላይ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፣ በአንዳንድ መስመሮች የቆይታ ጊዜውን ስድስት ደቂቃ በማድረስ ጥሩ ስኬት ማስመዝገብ መቻሉን አንስተዋል። በተቃራኒው ትራንስፖርት ለማግኘት እስከ 33 ደቂቃ የሚጠብቁ ሌሎች መስመሮች መኖራቸውንም ገልፀዋል።

ድርጅቱ ይህን ሰፊ ልዩነት ለማጥበብ በተያዘው ዓመት የአውቶቡስ ቁጥር በመጨመር፣ መስመሮችን በመለየት፣ ድጋፍና ክትትል በማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ እና ደንበኞች በየተርሚናሉ አውቶብስ ከ10 ደቂቃ በላይ እንዳይጠብቁ ለማድረግ ከመሥራት ባሻገር በተያዘው ዓመት የሚደረገው የዳሰሳ ጥናት መረጃ ድርጅቱ ለኅብረተሰቡ እንደሚያሳውቅ ጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here