በሶማሌ ክልል ቦምባስ ከተማ 11 ሰዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና በታጣቂዎች ተገደሉ

0
908

አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ኢሰመኮ ጠይቋል

ሶማሌ ክልል በቦምባስ ከተማ በአኪሾ ጎሳ አባላት ባሕላዊ ሥነ ሥርዓት ላይ በክልሉ መንግሥት የጸጥታ አካላት የተወሰደ መጠን ያለፈ የኃይል አጠቃቀም ለሞትና የአካል ጉዳት ምክንያት መሆኑን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶቸ ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ጉርሱም ወረዳ ቦምባስ ከተማ መጋቢት 11 እና 12/2014 በባሕላዊ ሥነ ሥርዓት የጎሳ መሪ (ሡልጣን) ለመምረጥ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ግድያ እና የአካል ጉዳት ስለመፈጸሙ በደረሰው ጥቆማ መነሻነት ከሚያዝያ 7 እስከ 17/2014 በቦታው በመገኘት ምርመራ አድረጎ ማረጋገጡን አስታውቋል።

በዚህም መሠረት በአጠቃላይ በኹለቱ ቀናት በክልሉ ጸጥታ ኃይሎች እና በታጠቁ ግለሰቦች በተፈጸሙ ጥቃቶች 11 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ይኸውም በታጠቁ ሰዎች የተፈጸመ ግድያ እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ የኃይል አጠቃቀም የደረሰ የሕይወት መጥፋት መሆኑን ነው። በተጨማሪም ቢያንስ በ33 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል።

በተጨማሪም ቦምባስ ከተማ የሚገኙ የጥቃቱ ሰለባዎች የተቀበሩበትን የመቃብር ስፍራ የጎበኘ ሲሆን፣ በዚህም በመጀመሪያ ቀን ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች የተቀበሩበት አንድ የጅምላ መቃብር እና በኹለተኛው ቀን የተገደለች ሴት የተቀበረችበት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ለብቻው ያለ አንድ ሌላ የመቃብር ቦታ መመልከቱን ኮሚሽኑ በምርመራ ሪፖርቱ አብራርቷል።

ለሰዎች ሞትና አካል መጉደል ምክንያት የሆነው ግጭት የተቀሰቀሰው በጉርሱም ወረዳ የሚገኙ የአኪሾ ጎሳ አባላት የራሳቸውን የጎሳ መሪ ለመምረጥ በሚደርጉት ሥርዓት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና በሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች መካከል በተፈጠረ ችግር ነው ተብሏል።

የአኪሾ ጎሳ አባላት ባሕላዊ ሥነ ሥርዓት ባለመግባባትና በተቃርኖ አስተያየት እልባት ሳያገኝ ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱና ለግጭት መነሻ ምክንያት መሆኑን ኮሚሽኑ ተገዝቢያለሁ ብሏል። የምርጫው ቀን ከመድረሱ 4 ቀናት ቀደም ብሎ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ቦምባስ ከተማ በመግባት ጥበቃ ሲያደርጉ እንደነበረ እና ከልዩ ኃይሉ ውጪ ሌላ የፀጥታ ኃይል በከተማው ውስጥ ያልነበረ መሆኑን ኢሰመኮ ከአይን እማኞች ሰምቻለሁ ብሏል።

የክልሉ መንግሥት ለሟች ቤተሰቦች እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ካሳ የከፈለ ቢሆንም ለተሟላ ፍትሕ የወንጀል ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል። በአኪሾ ጎሳ አባላት ላይ ድብደባ፣ የአካል ጉዳት እና የሕይወት መጥፋት ያስከተሉ ሰዎች በሙሉ የአስተዳደርና የጸጥታ አካላትን ጨምሮ ግልጽ የሆነ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ የወንጀል ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እና ለወደፊት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይከሰት ለመከላከል፣ አስፈላጊ የሆኑ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ኢሰመኮ ጠይቋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የክልሉ መንግሥት በጸጥታ ኃይሎች የተፈጸመው ግድያ ፈጽሞ ተገቢ እንዳልነበር በመገንዘብ ለተጎጂዎችና ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፈል ማድረጉ ጥሩ እርምጃ መሆኑን አስታወሰዋል። ‹‹ከዚህ በተጨማሪ የተሟላ ፍትሕ ለማረጋገጥና ለወደፊትም ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይገባል›› ብለዋል። ስለሆነም በአፋጣኝ የወንጀል ምርመራ ሊጀመር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here