“የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሃት ለዳግም ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት በግልጽ ሊያወግዝ ይገባል”:- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

0
813

ዕረቡ ግንቦት 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሃት ለዳግም ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት በግልጽ ሊያወግዝ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡
የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ህወሃት በትግራይ ክልል በአስገዳጅ ኹኔታ ከታዳጊ እስከ አዛውንት ለጦርነት እየመለመለ እንደሆነ በማጋላጥ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ መንግስትም ቡድኑ ዳግም ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ፅኑ አቋም በተግባራዊ እርምጃዎቿ እያሳየች መሆኗን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘበው የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ፣ ሰብዓዊ ዓላማ ያለው የተኩስ ማቆም መደረጉ፣ ሰብዓዊ እርዳታዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲገቡ በመንግስት በኩል የተወሰዱ እርምጃዎችን በዚህ ረገድ በአብነት አንስተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ከቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ፣ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኞችና ሌሎችም ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ጋር በሰላም ጉዳይ ላይ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

መንግስት አሁንም ለሰላም ያለውን አቋም የሚያሳዩ ግልፅ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ለተለያዩ የዓለም ማህበረሰብ አካላት የማስረዳቱ ሥራ ቀጥሏል ነው ያሉት።

ሆኖም ኢትዮጵያ ለሰላም በርካታ ርቀቶችን ብትጓዝም ህወሃት ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህንን የህወሃትን የዳግም ጦርነት ዝግጅትና የታጣቂ ምልመላ በትክክል ተገንዝቦ በቡድኑ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እንዲያሳርፍ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ህወሃት ለጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅትና የአስገዳጅ የታጣቂ ምልምላ እንዲያቆም በጠንካራ አቋም ሊያወግዘው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here