የቅድመ አወጭነት ጥናት፣ የቅድመ ግምገማ ሪፖርትና ሌሎች የማረጋገጥ ሥራዎች በአግባቡ ባለመሠራታቸው 44 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ እንዲወጣ መደረጉ ታወቀ። በ290 የመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ ቅድመ አዋጭነት ጥናት ወይም የቅድመ ግምገማ ሪፖርት ባለመደረጉ በተደጋጋሚ የጊዜ ክለሣ ተደርጎ ፕሮጀክቶቹ ተፈቅደው ሥራ ሲጀምሩ በነበራቸው ዋጋ ላይ 44 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ እንዲያስወጣ ሆኗል።
በተጨማሪ ወጪ ከተመዘገበው 44 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ውስጥ በቀድሞው የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ሥር የነበሩ 18 ፕሮጄክቶች ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ የተጠቆመ ሲሆን በገንዘብ ሲሰላም 32 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ታውቋል። ይህም ከጠቅላላው ተጨማሪ ወጪ 72 በመቶ እንደሚሸፍን ለማወቅ ተችሏል።
ፌደራል ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ እንደገለፁት፥ የመንግሥት ፕሮጀክቶች በተዘጋጀላቸው ጥናት ሰነድ መሠረት ሊጀምሩና በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ ቢኖርባቸውም በተለያዩ የፕሮጀክት አስተዳደርና አመራር ችግሮች ምክንያት በርካታ ፕሮጄክቶች የክዋኔ ኦዲት ክፍተቶች እንዲታይባቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ 75 ፕሮጄክቶች ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት፣ 208 ፕሮጄክቶች ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት፤ 54 ፕሮጄክቶች ከሦስት ዓመት እስከ አምስት ዓመት እንዲሁም 32 ፕሮጄክቶች ከአምስት ዓመት በላይ ዘግይተው እንደተጠናቀቁ ተገልጿል። በተያያዘም የአዋጭነት ጥናት ሳይኖራቸው በጀት የተመደበላቸው እና የተጀመሩ 16 የመንግሥት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ያወሱት ዋና ኦዲተሩ፤ ለፕሮጀክቶቹም 246 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ከተደረገላቸው በኋላ መቋረጣቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።
ገመቹ ዱቢሶ በመቀጠልም የገንዘብ ሚኒስቴር በ1998 ላይ የፕሮጀክት አዘገጃጀት መመሪያ እና በ1996 ደግሞ የፕሮጀክት ቅድመ ትግበራ መገምገሚያ መመሪያ ማዘጋጀቱን ጠቁመው፥ መመሪያዎቹን ገንዘብ ሚኒስቴር ራሱም የማይጠቀምበት ከመሆኑም በላይ ሌሎች አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶችም እንዲጠቀሙበት ክትትል እያደረገ እንዳልሆነ ተጠቁሟል። የመንግሥት የልማት ፕሮጄክቶች በታቀደው ጊዜ እየተጠናቀቁ ባለመሆኑ ሌላ ልማት ሥራ ሊከናወንበት ይችል የነበረውን እጅግ ግዙፍ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲወጣባቸው የሚደረግበት አካሔድ መኖሩን ገለፁት ገመቹ አንዳንዶቹ ጭራሽ አዋጭነታቸው አጠራጣሪ የሆነበት ደረጃም እንዳለ አልሸሸጉም።
ለሕዝብ እንደራሴዎች የቀረበውን የገንዘብ ሕጋዊነትና የክዋኔ ኦዲት ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች ከምክር ቤቱ ተሰንዝረዋል። ለዚህ ደግሞ ምክር ቤት አባሉ አበበ መሰሉ ቀዳሚ ናቸው። “የሚወጡት ሕጎች እየተተገበሩ አይደለም” ሲሉ ይጀምራሉ። ቀጥለውም የሚመለከታቸው ሚኒስትሮች የኦዲት ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት አለመገኘታቸው ራሱን የቻለ ግድየለሽነት መሆኑን ጠቅሰው ቁርጠኛ እርምጃ ካለመወሰዱ ጋር ተያይዞ በየዓመቱ ተመሳሳይነት ያለው የኦዲት ግኝት እንዲኖር ምክንያት ነው ብለዋል።
ለዚህ ምላሽ የሰጡት ዋናው ኦዲተር ገመቹ፥ መጋቢት 16 በአፈጉባኤው የተመራ እና አስፈፃሚ አካላትን ያካተተ ስብሰባ ማድረጋቸውን እና የኦዲት ክፍተት የታየባቸው መስሪያ ቤቶች በኹለት ወራት ውስጥ እንዲያስተካክሉ ጊዜ የተሰጣቸው መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ሰዓት በተሰጣቸው ጊዜ ገደብ ባልተጠቀሙ መሥሪያ ቤቶች ላይ ዝርዝራቸውን ወደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በማስተላለፍ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011



