- በያዝነው ዓመት ሕዳር ወር ላይ በአጋቾች የተገደሉ አሽከርካሪ እና ረዳቶች መኖራቸው ተገልጿል
ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ፣ ግንቦት 20 ቀን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ነጋዴ ባሕር እና ግንፍ በሚባሉ ወረዳዎች መካከል ከሱዳን ነዳጅ ጭኖ ሲመጣ የታገተውን አሽከርካሪ ለማስፈታት 400 ሺሕ ብር መጠየቁን በአካባቢው የሚገኙ የአዲስ ማለዳ ምንጮች አስታወቁ። የመከላከያ የደንብ ልብስ ለብሰው ሹፌሩ እንዲያሳፍራቸው ጠይቀው የነበሩት አጋቾች ወደተባለው አካባባ ሲደርሱ ሹፌሩን አስወርደው ጫካ ውስጥ ይዘውት እንደገቡ የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
በቦታው የመከላከያ ሠራዊት በፍጥነት ቢደርስም ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ አሽከርካሪውን ማስለቀቅ አልተቻለም። ነዳጅ የጫነው ተሽከርካሪም በቦታው ቆሞ እንደሚገኝ የገለጹት የአዲስ ማለዳ ምንጭ በወቅቱ ለ1 ሰዓት ተኩል ያህል አንድ የደረቅ ጭነት መኪና አሽከርካሪ “መንግሥት ደኅንነታችን እንዴት መጠበቅ አይችልም” በሚል ምክንያት መንገዱን ዘግቶት እንደነበረም ገልጸዋል። የአንድ የወረዳ አስተዳዳሪ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ባደረጉት ማግባባት፣ ከጎንደር እና ከመተማ በመጓጓዝ ላይ የነበሩ ነዋሪዎች መጉላላታቸውን በማስረዳት መንገዱን እንዲከፈት አድርገዋል።
በሑመራ እና በመተማ መሥመሮች ላይ የመከላከያ ሠራዊት ላልተወሰነ ግዜ መሥፈሩን ተከትሎ በተለይም የፈረቃ ልውውጥ ሲደረግ ለሠራዊቱ ሊፍት መስጠት የተለመደ መሆኑን ነዋሪዎች ያረጋገጡ ሲሆን፥ የመከላከያን ልብስ በመልበስ ይህንን ሽፋን አጋቾቹ ይጠቀሙበታል ብለዋል።
ከዚህም በፊት ተመሳሳይ እገታዎች መደጋገማቸውን የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪ፥ በያዝነው ዓመት ሕዳር ወር ላይ የተገደሉ አሽከርካሪ እና ረዳቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል። አርሴማ በሚባል አካባቢ መተለምዶ ኤፍኤስአር በሚባለው መኪና በሬ ጭኖ በመጓዝ ላይ እያለ በተተኮሰ ጥይት ረዳቱ ወዲያው ሕይወቱ ሲያልፍ ሹፌሩም ክፉኛ ቆስሎ ሕይወቱ ማለፉን ተናግረዋል። ከመኪናው ኋላ የነበረ ሌላ መኪና ላይ የነበሩ ሹፌርና ረዳትም ከባድ ድብደባ የደረሰባቸው ሲሆን በሕይወት የተረፈው ሹፌር ወደ መከላከያ ካምፕ እየተንፏቀቀ በመድረስ ወደ ጎንደር ለሕክምና ተልኮ ሕይወቱ መትረፉን ለማወቅ ተችሏል።
በመጀመሪያው መኪና ላይ የሞተውን ሹፌር አስከሬን ቤተሰቦቹ አግኝተው መቅበር እንዳልቻሉ የገለጹት ምንጮቻችን ታጣቂዎቹ ፖለቲካዊ አቋም የያዙ እንደሆኑ በተያየ መንገድ እንደሚገልጹ ከተረፉ ሰዎች መሥማታቸውንም ተናግረዋል።
በአብዛኛው የአሽካሪዎች ማኅበር፣ ቤተሰብ እና የተያዘው ሰው ጓደኞች ገንዘብ በማዋጣት ለአጋቾቹ የሚሰጥ ሲሆን ከፍተኛ ገንዘብ ቢጠይቁም በአብዛኛው ከ150 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ብር እንደሚወስዱ እና ታጋቾችን እንደሚለቁ አዲስ ማለዳ ተረድታለች።
የኢትዮጵያ የአሽከርካሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ብርሃኔ ዘሩ በጉዳዩ ላይ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት እያደረጉ እንደሆነ ገልጸው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። በተጨማሪም የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ ብርሃኑ ጣምያለው በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።
የዞኑ የፀጥታ አዛዥ ኮማንደር እንየው ዘውዴም የታገተው አሽከርካሪ እንዳልተለቀቀ ያስታወቁ ሲሆን፥ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011



