በአማራ ክልል 138 የወጣት ማዕከላት ተገንብተው ቢያልቁም አገልግሎት አይሰጡም

0
650
  • 3ሺ የወጣት ማዕከላት እንዳሉ የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል

በአማራ ክልል ግንባታቸው የተጠናቀቁ 138 የወጣት ማእከላት በተለያዩ ምክኒያቶች አገልግሎት እንደማይሰጡ እና 10 የሚሆኑት ማዕከላት ደግሞ ተገንብተው ከተጠናቀቁ በኋላ መፍረሳቸው ተገለጸ።

የክልሉ የስብዕና ልማት ማዕከላት ዳይሬክተር ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ውበቴ ጥጋቤ በክልሉ 438 ወጣት ማዕከላት የሚገኙ መሆኑን ገልጸው ከእነዚህም ውስጥ ከተገነቡ በኋላ ሌላ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ማዕከላት መኖራቸውን አክለው ገልዋል። ከግንባታ በኋላ የፈረሱት ማእከላት ከግንባታ እቃዎች ጥራት ማነስ አንዲሁም ከዲዛይን እና ከይዞታ ማረጋገጫ ጋር በተያያዘ መሆኑንም ገልጸዋል።

በገጠራማ ከተሞች በዘመቻ መልክ አካባቢው ላይ ባሉ እንደ ሳጠራ አና እንጨት ባሉ ቁሳቁሶች ተሰርተው በውስጣቸው ከ4 የማይበልጡ አገልግሎቶች የሚሰጡ ወጣት ማዕከላት መኖራቸውን ሃላፊው ተናግረዋል።

በክልሉ በባህር ዳር ኮምቦልቻ እና በጎንደር ከተሞች ከ 222 ጥራታቸውን የጠበቁ እና ከ14 አይነት በላይ አግልግሎቶችን የሚሰጡ ማዕከላት መኖራቸውን አቶ ውበቴ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ወጣት ማዕከላት በወጣላቸው ደረጃ መሰረት በውስጣቸው ከ 16 በላይ አግልግሎቶችን የሚሰጡ ሞዴል ማእከላት በሚል መዋቀራቸውንም ይናገራሉ። ሁለገብ የሚባሉት ማእከላት 14 አይነት፣ መካከለኛ የሚባሉት ደግሞ ዘጠኝ አገልግሎቶች እንዲሁም አነስተኛ በሚል የተደራጁት አራት አይነት አገልግሎት እንደሚሰጡም ተናግረዋል።

በመላው አገሪቱ 3ሺ የወጣት ማዕከላት እንዳሉ የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ከእነዚህ ውስጥም አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት አንድ ሺህ አምስት መቶዎቹ ብቻ ናቸው።

የአስተዳደራዊ ችግሮች፣ የበጀት ዕጥረት፣ የመሰረተ ልማት አለመመሟላት ወደ አገልግሎት ላልገቡት ማእከላት እንደምክኒያትነት ይጠቀሳል።
ከወጣት ማእከላት ባሻገር ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ ወጣቶችን ከቴክኖሎጂ እና ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር ለማስተዋወቅ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚንስትር ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ጋረ በመተባበር በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሳይንስ ካፌዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል።

የአማራ ክልል ህዝብ ብዛት ከ21ሚሊየን በላይ ሲሆን ከትግራይ እና ከአፋር ክልል በመቀጠል አዋቂዎች እና ወጣቶች በወንጀል ተግባራት የሚሳተፉበት ክልል መሆኑን የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ለዚህም ስራ አጥነት እና ወጣቱ ግዜውን የሚያሳልፍባቸው ቦታዎች ያለመኖራቸውን እንደ አገር እየጨመረ ለመጣው ወንጀል እና የሱስ ተጠቂነት እንደምክኒያት ይጠቀሳል፡፡

በአማራ ክልል በ2011 ዓ.ም 22 አዳዲስ ወጣት ማዕከላት ተገንብተው ወደስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here