“ጋዜጠኛን የሚፈራ ወንጀልን የሠራ ነው” እንደሚባለው፣ ባለሥልጣናትም ሆኑ ማናቸውም ዜጎች ክፉ የሠራንም ሆነ በጎ የሚሠራን ለሕዝብ የሚያሳውቁ ጋዜጠኞችን መፍራት እንደማይገባቸው አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
በያዝነው ሳምንት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከበረው የጋዜጠኝነት ቀን የዛሬ ሦስት ዓመት ተሰጥቶት የነበረውን ክብር ሩብ ያህል እንኳን አላገኘም ነበር። አንድም ጋዜጠኛ እስር ቤት ውስጥ የሌለባት አገር እየተባለ ቅስቀሳ ሲደረግ የነበረበት አገር ላይ አሁን ያለን አይመስልም። ነጻ ፕሬስ እየተባለ ጆሮ እስኪሰለች አስፈላጊነቱ ቢደጋገምና የምርመራ ጋዜጠኝነትም ይበረታታል ቢባልም መሬት ያለው እውነታ ግን ከሚወራው ፍፁም የተራራቀ ነው።
በረባ ባልረባው ጋዜጠኛውን ከሥራው እያፈሱ ወስዶ ማሰር በአገራችን የተለመደ ክስተት ቢሆንም እያደር እየሆነ ያለው ግን ፈሩን የለቀቀ ነው። ክልሎች እንደፈለጉ የፌደራሏ ዋና ከተማ ወደሆነችው አዲስ አበባ እየመጡ ያሻቸውን መርጠው በመውሰድ የፈለጉበት ቦታ ያጉራሉ። ወንጀል ተሠርቷል ቢሉ እንኳን ተሠራበት የሚሉት ቦታ ከመታሰሪያና ከመከሰሻው ቦታ እየለያዩ የሕግ ፅንሰ ሐሳብን እንደፈለጉ መሸራረፍ ብቻ ሳይሆን ከነአካቴውም ሲገረስሱት ማየት ብዙዎቻችንን ማስገረም ካቆመ ቆይቷል።
ሥራህን በአግባቡ ሠራህ ተብሎ ሽልማት የሚጠብቅን ጋዜጠኛ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ለተደጋጋሚ ጊዜ ማስጠበቅ ፋሽን እየሆነ መጥቷል። ለምን እንዲህ አድርገህ አጋለጥክ እያሉ በየተቋሙ የሚያስፈራሩ በየሳምንቱ የማይጠፉ ቢሆንም፣ የዳቦ ሥም እየሰጡ ጋዜጠኛው እንዲጠላና የአገር ጠላት ተደርጎ እንዲታይ የሚያደርጉም መደበኛ ሥራቸው እንዳደረጉት የውስጥ አዋቂዎች ሲናገሩ ይደመጣል።
“ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም” እየተባለ ሲነገር አሳሪዎቹም ሆነ ጫና ፈጣሪዎቹ ያውቃሉ። እነሱ የሚያምኑት ጋዜጠኝነት ወንጀል እንደሆነ ሳይሆን የፍላጎታቸውን የማያደርጉ ጋዜጠኞች ወንጀለኞች እንደሆኑ ነው። ነፃና ገለልተኛ ሆነው መሥራት የሚጠበቅባቸውን ባለሙያዎች ቃል አቀባይና ገፅታ ገንቢ ማድረጋቸው ለሙያው ወዳጆችም ሆነ ለአገር ተቆርቋሪዎች እጅግ አሳዛኝ ተግባር ነው።
ከሁሉም ጋዜጠኞች ላይ ከሚፈፀም ያልተገባ ተግባር ዋነኛው፣ ድንገት ክብራቸውን ባልጠበቀ መንገድ እንደወንበዴ ተይዘው የደረሱበት ሳይታወቅ ለቀናት የሚሰወሩበት መንገድ ነው። በጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ላይ ተፈፅሞ ብዙዎች የሰሙት ይህ ተግባር በወቅቱ መነጋገሪያ ሲሆን፣ አድራጊዎቹን የሚቀጣ የሕግ አካል ባለመኖሩ አሁንም ተደጋግሞ እየተፈፀመ ይገኛል።
ምንም ቢደርስበት ለአገር ሲል ቆርጦ ለገባበት ባለሙያ፣ እንዲህ መደረጉ ምንም ላይመስለው ይችላል። ሆኖም ምንም ላላደረጉ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ከባድ ቅጣት በመሆኑ መንግሥት ወዳጆቹን የሚያጣበት ብቻ ሳይሆን በርካታ ጠላት የሚያፈራበት መንገድ እንደሆነም ሊያውቀው ይገባል።
ለአገሬና ለሕዝቤ እጠቅማለሁ ብሎ በግሉ የሚሠራውን ትቶ ያን ያህል ገቢ የሌለውን ሥራ የሚሠራ ባለሙያን መንግሥት መንከባከብ ሲገባው ማሳደዱ ተገቢ አለመሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
መንግሥት በእንዲህ ዓይነት የማሳደድ መንገድ ከቀጠለ፣ ባለሙያው ተጠያቂ ሆኖ የሚሠራበትን አገሩን እየተወ ወደ ውጭ በመውጣት አማራጭ ሲያጣ የጠላቶቻችን መጠቀሚያ ሊሆን እንደሚችል መረዳት ይገባል። መፈናፈኛ ያጣች አይጥ እንኳን መሸሽ አቁማ ፊቷን ወደ ምታባርራት ድመት ማዞሯ እንደማይቀር እሙን ነው።
ከዚህ አኳያ ባለፈው ሳምንት የተሰማው ደግሞ ከመንግሥት ከሚጠበቀው የተለመደው ያልተገባ ተግባር እጅግ የራቀ፣ ብዙዎችን ያስገረመ የጋዜጠኛ እስርና መሰወር ነው። እስከ ዛሬ ሲሰወሩም ሆነ ታስረው ሲንገላቱ የምንሰማው በብርቱ ብዕራቸውም ሆነ በአንደበታቸው መንግሥትን የሚተቹና የባላሥልጣናትን ቅሌቶች ማንንም ሳይፈሩ የሚያጋልጡትን ነበር።
ይህ ዓይነቱ አሠራር አዋረዱኝ ብሎ ለክብሩ እንጂ ለሚሠራው ነገር ከማይጨነቅ አካል የሚጠበቅ ቢሆንም፣ የሕዝብን ጉዳትና ጉስቁልና መንግሥትም ሆነ ሕዝብ እንዲሰማ ያደረጉ መታደን መጀመራቸው ግን ብዙዎችን እጅግ ያሳዘነ ድርጊት ነው። ጋዜጠኛ ሲሳይ ጎበዜ ዝናን ካገኘበት ኢሳት ቴሌቪዥን ጀምሮ አሁን እያገለገለበት በሚገኘው የኛ ቴሌቪዥን ውስጥ በስቃይ ውስጥ አለ የሚባለውን የኅብረተሰቡን ችግር ማንንም ሳይፈራ ይፋ በማድረግ የሚታወቅ ባለሙያ ነው። ይህ ጋዜጠኛ በሥራው ብቻ ሳይሆን የተወለደበትን የራያ ሕዝብ ችግርንና ሰቆቃን በማሳወቁም በመንግሥት ጥርስ ተነክሶበት እንደቆየ ሲነገር ነበር።
በዚህ ተግባሩ የበርካታ በጎ አድራጊ ማኅበራትን ደጅ የረገጠው ይህ ጉምቱ ጋዜጠኛ፣ በሥራው የተመረጠበት እሱ የሚመራው ለበጎ አድራጎት ተግባር የተቋቋመ ማኅበር ቢኖርም፣ መንግሥትም ይሁን እሱን አፍኖ የወሰደው አካል የሠራውን በጎ ተግባር ከግምት ውስጥ ሳያስገባ ደብዛውን ካጠፋው ቀናት ተቆጥረዋል።
ይህ ዓይነት አስነዋሪ ተግባር ሙያውን አክብሮ ለሚሠራው መሰል ባለሙያ የሚያስተላልፈው መልዕክት ግልፅ ቢሆንም፣ ጋዜጠኛው አጎብዳጅ ሆኖ የሚቀጥልበት ወይም ራሱን ችሎ የሙያው ስነምግባር የሚጠይቀውን ባህሪ ተላብሶ የሚሠራበት የለውጥ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ የሚጠቁመው ነው።
ባለሙያውን አፍነው የወሰዱት ዓላማ እሱንም ሆነ መሰሎቹን ለማስፈራራት ቢሆንም፣ ሌሎችም ጭምር ፈርተው ዝም የሚሉ ከሆነ የሚመጣው ተፅእኖና ጫና ከፍተኛ ስለሚሆን ሙያቸውን ቢቀይሩ የተሻለ ይሆናል። ጋዜጠኛ እንደማንኛውም ባለሙያ ተጠያቂ ሆኖ የሚሠራበት ፍትሓዊ የሕግ ማእቀፍ እስካለ ድረስ መፍራት አይኖርበትም።
ቁስልና ደምን የሚፈራ ሰው ሐኪም መሆን እንደማይችለው፤ ሞት የሚፈራም መገዳደል ወዳለበት ጦር ሜዳ ማምራት እንደሌለበት ሁሉ፣ ባለሥልጣንን የሚፈራም ሆነ በጥቅም ሊታሰር የሚችል ግለሰብ ጋዜጠኛ ነኝ ብሎ አገሩን አሳልፎ መስጠት ብቻ ሳይሆን ሕዝብ የሚጠብቀውንም ማሳጣት የለበትም። መንግሥት እንደሚፈልገው መሆን የጀመረ ባለሙያ የእሱን መኖር ብቻ የሚያስብ ከሆነ እውነተኞችን ማሳደጃ መሣሪያ መሆኑ አይቀርም።
‹ነግ በእኔ› ሳይሉ አንድ ሙያተኛን ለይተው የሚያጠቁ የመንግሥት አካላትም ሆኑ ግለሰቦች ነገ የእነሱ ተራ ሆኖ ያለአግባብ ሲንገላቱ የሚያሳውቅላቸውና እንባቸውን የሚያብስላቸው እንደማይኖርላቸው ሊያውቁት ይገባል።
አገራችን እንድታድግ ከልቡ የሚመኝ ማንኛውም አካል አንድ የሙያ ዘርፍ ብቻ ለውጥ አምጥቶ ኢትዮጵያን ያሳድጋታል ብሎ ማሰብ እንደሌለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች። ለአገር መኖር መሪ፣ ወታደርና ፈራጅ፣ እንዲሁም ምሁርና አራሽ የሚያስፈልገውን ያህል እነዚህ አካላት በአግባቡ ሥራቸውን እንዲሠሩ እውነተኛ መረጃ አስፈላጊያቸው መሆኑ ሊታመንበት ይገባል።
የቀደሙ ዘመናት ታሪኮች በነገሥታቱ ወዳጆችና የቅርብ ሰዎች ብቻ የተፃፉ ናቸው በሚል ታማኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ የመኖራቸውን ያህል፣ የዘመናችንስ ክንውኖች ለወደፊት ተቀባይ ይሆናሉ ወይ ብለን ማሰብ ይጠበቅብናል። ክስተቶች በተፈጠሩ ወቅት የተለያዩ ዘገባዎችን ለመቀበል የሚያዳግተን ትውልዶች ሆነን ሳለን፣ ትክክለኛ መረጃ አጣርቶ ራሱን ችሎ በገለልተኝነት ወገን ሳይዝ ትክክለኛ መረጃ የሚያወጣ አካል እንዲኖረን መሥራት ይኖርብናል።
ደርግን ለውድቀት ዳርጎታል ተብለው ከሚጠቀሱ በርካታ ምክንያቶች መካከል የመረጃ ቅብብሉ ታማኝነት በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። ለምን እንዲህ ተደረገ በሚል ለመቀጣጫ ተብሎ እርምጃ መወሰድ ሲጀምር፣ ላለመቀጣት ሲሉ እውነተኛውን የጦር ሜዳ ውሎ እየሸሸጉ መሪዎቻቸውን ሊያስደስት የሚችለውን ብቻ በሪፖርት መልክ የሚያቀርቡ ነበሩ። በጎ በጎው እየተመረጠም ይሁን እየተፈጠረ የሚነገራቸው ሹማምንቱ፣ ከሃቁ በራቁ ቁጥር የሚመጣላቸው መረጃ ላይ ተመስርተው የሚወስኑት ውሳኔ ለበለጠ ውድቀት እንደዳረጋቸው በመመልከት ከቅርቡ ታሪካችን የዛሬዎቹ ሊማሩ ይገባል።
እውነተኛ ጋዜጠኛ የማይኖር ከሆነ የበታች ሹማምንት ሕዝብ ላይ የሠሩትን በደልም ሆነ የጠነሰሱትን ሴራ መንግሥት ሊያውቅ የሚችልበት መንገድ የለም ወይም አስቸጋሪ ነው። የደኅንነት አካላትም ሆኑ የፀጥታ አካላት በሕዝቡ በግልፅ ስለማይታወቁና አቋማቸውን በተመለከተ ተለጣፊ እንደሆኑ ስለሚታመን ሕዝቡ አምኖ ብሶቱን የሚነግረው አካል እንደሚያስፈልግ የአዲስ ማለዳ እምነት ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014



