የአፍሪካ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች የፈጠራ ነጻነት ኔትዎርክ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

0
1155

በሰላም ኢትዮጵያ አስተባባሪነት የሚመራ የአፍሪካ የኪነጥበብ ሙያተኞች የፈጠራ ነጻነት ዙሪያ ያተኮረ ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል።
የመላው አፍሪካ የኪነጥበብ ሙያተኞች የፈጠራ ነጻነት ቅንጅት (PANAF) ተብሎ የሚጠራው ይህ ፕሮጀክት፣ በአፍሪካ የሚገኙ የፈጠራ ሙያተኞችን የፈጠራ ነጻነት ጉዳዮች በጋራ በማስተጋባት ለሙዚቃና ለፊልም ጥበብ ኢንዱስትሪዎች ከፍ ያለ ድርሻ ያበረክታል ተብሎ ይታመናል።
በዚህ ፕሮጀክት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ዋናዎቹ የአቅም ግንባታ፣ ባለሞያዎችን ማሰባሰብና ማስተባበር፣ ጥናትና ምርምር፣ የባህል ፖሊሲ ቀረጻ፣ አውደ-ርዕዮችና ጉባኤዎችን ማካሄድና ማስተባበር ናቸውም ተብሏል።
የሰላም የሪጅናል ፕሮግራም ዳይሬክተር ላሉሲ ኢላዶ፤ በአፍሪካ የነፃ አስተሳሰብ ጉዳይ እያደር እየቀጨጨና እየጠበበ በመሄድ ላይ ይገኛል ያሉ ሲሆን፣ እንዲህ ዓይነት ችግር ባለበት ሁኔታ የአፍሪካውያንን ኪናዊ አቅም በአግባቡ መዝኖ ማድነቅና ተገቢውን እውቅናና ክብር መስጠት እንደማይቻል ጠቁመዋል። በመሆኑም በየአገሩ ካሉ ሕግ አውጪዎች ጋር በጋራ በመሆን የፈጠራ ሙያተኞችን መብቶች እውቅና የመስጠት እና ያለምንም ስጋትና ፍርሀት ማሰራጨት እንዲችሉ ማድረግ ትኩረት ሰጥተን ልናከናውነው የምንፈልገው ሥራ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ የኪነጥበብ ሙያተኞች የፈጠራ ነጻነት ቅንጅት በአሁኑ ጊዜ በናይጄሪያ፣ በጋምቢያ፣ በሞዛምቢክ፣ በኬንያ፣ በዛምቢያ፣ በሩዋንዳ፣ በኡጋንዳና በኢትዮጵያ የሚገኙ አጋር ድርጅቶች ባደረጉለት ድጋፍ እየታገዘ ሥራውን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ሰላም ኢትዮጵያ ለአዲስ ማለዳ የላከው መግለጫ ያስረዳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here