ጾታዊ ጥቃትን በመከላከል እና በሰብዓዊ ድጋፎች ዙሪያ ያተኮረ ውይይት ከአውሮፓ ህብረት ልኡካን ጋር ተካሄደ

0
1019

ዕረቡ ግንቦት 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከልና በሰብዓዊ ድጋፎች ዙሪያ ላይ ያተኮረ ውይይት ከአውሮፓ ህብረት ልኡካን ጋር መካሄዱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በውይይቱም በአፋርና በአማራ ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ለመደገፍ የተከናወኑ ሥራዎችን እንዲሁም በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፎችን ጨምሮ የጤና፣ የስነልቦና፣ የማህበራዊ ድጋፎችና አገልግሎቶችን በመንግስት በኩል ተደራሽ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ልዩ ተወካይ ኤሞን ጊልሞር በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል አገራዊ የልማት እድገትን ለማምጣት ታልሞ የታቀደውን መሪ የልማት እቅድን አድንቀው፣ በጦርነቱ ምክንያት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ለማቋቋምና ተጠያቂነትን ለማስፈን የተጀመሩ ጥረቶችን እንዲሁም ሰብዓዊ ድጋፎችንና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ህብረቱ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱም በቀጣይ በጦርነቱ ምክንያት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችን የተለያዩ የሰብዓዊ፣ የማህበራዊ፣የስነልቦናና የጤና ድጋፎችን በአንድ ማእከላት የሚያገኙበትን አሰራር እንደሚያጠናክርና በዚህ ረገድ የአውሮፓ ህብረት ከችግሩ ስፋት አንጻር ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ መቅረቡን ከሚኒስትሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here