ሐሙስ ግንቦት 11 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክፍል ከተማ አያት መንድር የዞን 8 ነዋሪዎች ሕጋዊ ካርታ አውጥተው ያለሙት የሕዝብ መናፈሻ ያለ ምንም ማስጠንቀቂና ሕጋዊ ማስረጃ በትራክተር እየታረሰ መሆኑን ፓርኩን ያለሙት የመንደሩ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፤ ከ15 ዓመት በላይ ያለሙት የሕዝብ መናፈሻ ወይም ፓርክ ከነዋሪዎች በተዋጣ ገንዘብ በአረንጓዴ ልማት የተሸፈነና የሸክላ ሴራሚክስ የተነጠፈለት ነው፡፡
ይሁን እንጅ ዛሬ ማለዳ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይዘን ነው የመጣነው ያሉ ፖሊሶች ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ ሰራተኞችና አንድ ትራክተር አሰማርተው ፓርኩን እያፈረሱ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ሕጋዊ ካርታ አውጥተው ከ15 በላይ በመናፈሻነት የተጠቀሙት ፓርክ እንደሚፈርስ ምን አይነት ማስጠንቀቂያም ይሁን መረጃ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይዘን ነው የምናፈርሰው ያሉት የመንግሥት አካላት ማዘዣውን ለፓርኩ ባለቤት ለሆኑት ነዋሪዎች እንዲሳዩ ቢጠየቁም የፍርድ ቤት ማዘዣ ማሳየት አልቻሉም ተብሏል፡፡
ፓርኩን የሚጠቀሙ ከ400 በላይ አባዋራዎች ሲሆኑ፣ ፓርኩን ያለሙት ሕጋዊ ካርታ በማውጣትና ብር በማዋጣት እስከዛሬ ድረስ በጋራ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡






