ሐሙስ ግንቦት 11 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮ ኤርስ ንግድና ኢንቨስትመንት ሥር ከሚገኙ ተቋማት ውስጥ አንዱ የሆነውና በአለም አቀፍ ደረጃ ወደ ባህር ማዶ በሥራ፣ በጉብኝት፣ በቢዝነስና በኢንቨስትመንት ቪዛ ለመሄድ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንን የቪዛ ማማከር አገልግሎት የሚሰጠው “ሩቢ” ኮንሰልቲንግ ታዋቂ እና ተፅእኖ ፈጣሪ ያላቸውን ሦስት አርቲስቶች በብራንድ አምባሳደርነት ሰይሟል።
በኩባንያው በብራንድ አምባሳደርነት የተሰየሙት አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፣ አርቲስት ሩታ መንግሥተአብ፣ አርቲስት ሊዲያና ሰለሞን ሲሆኑ፤ በዛሬው ዕለት በሸራተን አዲስ ሆቴል ከኩባንያው ጋር የፊርማ ሥምምነት ፈፅመዋል።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት የኢትዮ ኤርስ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ታረቀኝ ቶሎሳ እንደገለፁት፤ ሦስቱ አርቲስቶች የኩባንያው አምባሳደሮች በመሆን እንዲወክሉት በአጠቃላይ አምስት ሚልየን ብር የሚደርስ ክፍያ ተፈፅሟል።
አርቲስቶቹ በሥነምግባራቸው፣ በሥራቸው እንዲሁም በማህበረሰቡ ዘንድ ባላቸው ተቀባይነትና መሰረት የኩባንያው አምባሳደር ሆነው እንዲሾሙ መመረጣቸውንም ታረቀኝ ጨምረው ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
የ”ሩቢ” ቪዛ ኮንሰልቲንግ የብራንድ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አርቲስቶችም ኩባንያው በእነርሱ ላይ እምነት ጥሎ ኩባንያውን እንዲያስተዋውቁ ሀላፊነት ስለተሰጣቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ በቀጣይም ኩባንያው በሚፈልጋቸው ሥራዎች ኹሉ በታማኝነት እና በትጋት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።






