ሚዲያ ከመንግሥት እና ከተለያዩ አካላት ነፃ መሆን እንዳለበት የሚታመን ሲሆን፣ ያለ ፕሬስ ነፃነት እንዲሁ ዴሞክራሲን ማምጣት ወይም ማረጋገጥ የማይታሰብ ጉዳይ ነው። ለረዥም ዓመታት የፕሬስ ነፃነት ካልተረጋገጠባቸው አገራት ተርታ ደግሞ ኢትዮጵያ ትጠቀሳለች።
ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት ለፕሬስ ነፃነት ከማይሰጡ አገሮች ተርታ ትሰለፍ የነበረች ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ፣ ለአንድ ዓመት ያህል ለውጥ ያሳየው የኘሬስ ነፃነት ወደ ቀድሞ ስጋቱ ተመልሷል።
በየዓመቱ የአገራትን የፕሬስ ነፃነት ደረጃ እየመዘነ የሚሰፍረው ዓለም ዐቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን፣ ኢትዮጵያ ቀድሞ ከነበሩ ዓመታት አንፃር ሲታይ በቀደመው ዓመት ደረጃዋን አሻሽላ እንደነበር ጠቅሷል።
ቡድኑ ባለፈው ዓመት ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት ሰንጠረዥ ላይ ኹለት ደረጃ ቀንሳ 101 መሆኗን ጠቁሟል። ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ታይቶ የነበረው የፕሬስ ነፃነት መልሶ አደጋ እንደተጋረጠበት አልሸሸገም።
ቡድኑ የጋዜጠኞች እና የተለያዩ አካላትን ከእስር መፈታት እንደ መልካም እርምጃ ቢቆጥረውም፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን ተከትሎ ሚዲያው ላይ ፅንፍ እንዲይዝ እያደረገ ነው ማለቱ ይታወሳል።
አር ኤስ ኤፍ በተሰኘ ቅፅል ሥሙ የሚታወቀው ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን፣ ባለፈው ዓመት 180 የዓለማችን አገራትን አካትቶ በሠራው ጥናት መሠረት ጋዜጠኝነት 70 በመቶ እክል እንደገጠመውና የመረጃ ጋዜጠኝነት በ73 አገራት እንዲሁ ከበድ ያለ እክል መግጠሙን ይገልፃል።
ድርጅቱ አክሎም አገራት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተገን አድርገው ጋዜጠኞች ተዘዋውረው እንዳይዘግቡ ከልክለዋል ሲል ወቀሳውን ሰንዝሯል።
ጥናቱ እንደሚጠቁመው በተለይ በእስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅና አውሮፓ ጋዜጠኞች ተዘዋውረው ለመዘገብ እንደተቸገሩ ነው። አክሎም የበርካታ አገራት ባለሥልጣናት የተሳሳተ ዘገባ ሲያስተላልፉ ጋዜጠኞች ግን ትክክለኛውን መረጃ በማቅረብ ይህን ሲያርሙ ነበር ይላል።
በ2021፣ 174ኛ ደረጃ ላይ ትገኝ የነበረው ኢራን የፕሬስ ነፃነትን የበለጠ በመጨቆን ሥሟ ተጠቅሷል። የፕሬዝዳንት አብዱልፋታህ አልሲሲ አገር ግብፅም በተለያዩ ምክንያቶችን የፕሬስ ነፃነትን በመግፈፍ 166ኛ ደረጃ ላይ ማስፈሩ አይዘነጋም።
ኖርዌይ ለፕሬስ የላቀ ነፃነት በመስጠት ለአምስተኛ ተከታታይ ዓመት የአንደኛ ደረጃን ተቆጣጥራ የነበረ ሲሆን፣ ፊንላንድ ኹለተኛ፣ ስዊድን ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ 44ኛ ላይ ስትገኝ ድርጅቱ ጨቋኝ ናት ሲል የፈረጃት ቻይና እንዲሁ 177ኛ ላይ ትገኛለች። የመጨረሻውን ሦስት ደረጃ የያዙት አገራት ደግሞ ተርከሜኒስታን 178ኛ፣ ሰሜን ኮሪያ 179ኛ እንዲሁም ኤርትራ 180ኛ ተቀምጠዋል።
ድርጅቱ በአፍሪካ ደግሞ ጥሩ መሻሻል አሳይተው ያላቸውና በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍ ብለው የተገኙት አገራት ቡሩንዲ፣ ሴራሊዮን እና ማሊ ናቸው።
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ተነፍጎት የነበረው የፕሬስ ነፃነትም ከሦስት ዓመት በፊት ወደ መንበር በመጣው አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በመጀመሪያው አንድ ዓመት ቀድሞ ከነበረው ስርአት አንፃር መሻሻል እንዳሳየ በርካቶች ነበሩ ሲናገሩ የተደመጡት።
በኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙኀን እንቅስቃሴ ዙሪያ ለውጦች መመዝገባቸው እና በታዩ ለውጦች ምክንያትም ዓለም ዐቀፍ አድናቆት ሲቸራት ተሰምቷል።
የኢትዮጵያ የኘሬስ ነፃነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ የሚዲያ ተቋማትን በማበረታታት፣ በመደገፍ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚወጣ ከማውራት ባሻገር የሚዲያ ፖሊሲ፣ የብዙኃን መገናኛ ሕግ በማውጣት አፅድቆ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አዲሱ መንግሥት የራሱን አሻራ ማሳረፉ አይካድም ሲሉ የሚሰሙት በርካቶች ናቸው።
ነገር ግን ቀስ በቀስ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያሰፈራቸውን ሕጎች በመሸፋፈን በኢትዮጵያ ያለውን የፕሬስ ነፃነት ወደ ቀድሞ አፈና እንደመለሰው እና አሁንም ከስጋት ነፃ እንዳልሆነ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበርም የሚስማማበት ጉዳይ እንደሆነ ይሰማል።
በየወቅቱ የጋዜጠኞች መደብደብ፣ መታፈን፣ መታሰር እና ከታሰሩ በኋላ ያሉበት ቦታ አለመታወቅ እና በነፃነት ዙሪያ የታዩትን መሻሻሎች ወደኋላ የመቀልበስ ስጋቱ አሁንም የሚዲያው ፈተናዎች ሆነው ይገኛሉ።
ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለ31ኛ ጊዜ የተከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን፣ የሙያ ሥነምግባርን ባከበረ መልኩ ጋዜጠኝነት እንዲተገበር፣ መንግሥት የፕሬስ ነፃነትና የገባውን ቃል እንዲያከብር በማስታወስና በማሳሰብ አልፏል።
በዚህም ነፃነታቸው ለታፈኑ ሚዲያዎች እና በጋዜጠኝነታቸው ብቻ ለሚታሰሩ ድምፅ ለመሆን እንዲሁም ለሙያቸው ብለው ሕይወታቸውን ላጡ ጋዜጠኞች መታሰቢያ ለማድረግም ነው።
በአፍሪካ በየጊዜው ጋዜጠኞች ከሚታሰሩባት አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች እና አሁንም በየወቅቱ ጋዜጠኞች እየታሰሩ መሆናቸው የሚታወቅ ነው።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር በበኩሉ በየጊዜው የሚታሰሩት የጋዜጠኞች ጉዳይ እያሳሰበው መሆኑን ይገልፃል። ማኅበሩ የተለያየ ግልፅ የሆነና የማያሻማ የሕግ ጥሰት ያለበት የቦርድ ሹመት፣ ሕጉ ሳይሸራርፍ መተግበር ያለመቻሉ ችግርን አጉልቶ እንደሚያሳይ በኢትዮጵያ ያለውን የሚዲያ እድገት በእጅጉ የሚጎዳ እንደሆነም ጠቅሷል። ሕዝብም በሕግ አውጭው ተቋም ላይ እምነት እንዳይኖረው የሚያደርግ እንደሆነ ይገነዘባል ነው ያለው።
ከዚህ በተጨማሪ ማኅበሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቃቸውን አዋጆችንና የድንጋጌዎችን ተፈፃሚነት በትኩረት መከታተል ስለመቻሉ ጥያቄ የሚያጭር ሆኖ አግኝቸዋለሁ ብሏል።
ማኅበሩ አክሎም የሕግ ጥሰት የተስተዋለበት እና የተንሰራፋበት የመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት ሹመት እና የሥራ ምደባ በአመዛኙ መስተካከል ያለበት መሆኑን በአፅንዖት እንደገለፀ እና የመገናኛ ብዙኀንን ቁልፍ አገራዊ ሚና ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መሆን እንዳለበት ይገልፃል።
በግልፅ እየታየ ያለውም ችግር እርምት የሚሻው እና ውስን የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ እና ድምፀ ተዓቅቦ ያቀረቡበት ሹመት ማኅበሩን እንደሚያሳስበው አሳውቋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን ዳግም የሚያጤንበትን አማራጭም እንዲመለከት በአፅንዖት መጠየቁ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው፣ ከሦስት ዓመት በፊት አዲሱ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ለአንድ ዓመት ያክል የፕሬስ ነፃነት ጥሩ መሻሻል አሳይቶ እንደነበር እና ጋዜጠኞችም ሥራቸውን በነፃነት የሚሠሩበት እንዲሁም ለእስር ያልተጋለጡበት ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በኢትዮጵያ እንዲከበር በመደረጉ ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት ወቅት ነበር።
ኘሬዝዳንቱ አክለውም በኢትዮጵያ የብዙኀን መገናኛ ሕግ ለብዙ ዓመታት አጠያያቂ የነበረ ቢሆንም፣ አዲሱ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ሕግ በባለሙያዎች ተረቅቆ በማፅደቅ እንዲተገበር የተደረገበት ወቅት ነው ብለዋል።
ይህ የብዙኀን መገናኛ ሕግ ጋዜጠኞች በወንጀል ከተከሰሱ በወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑበት ሂደት ቢኖር እንኳ እስከ 300 ሺሕ ብር ድረስ በሚያስቀጣ ወንጀል እንዲጠየቁ የሚደረግበት ሂደት ነው ያለው ይላሉ።
ፕሬዝዳንቱ አስከትለውም ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት የሚዲያ ፖሊሲ ያልነበራት መሆኑን ጠቅሰው፣ አዲሱ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ፖሊሲው ተፅፎ በፓርላማ በማፅደቅ ተግባራዊ ለማድረግ የተሠራበት ሂደት ጥሩ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪ መንግሥት ከሦሰት ዓመት በፊት ሚዲያዎችን እንደሚንከባከብ እና ሚዲያዎች የተለያዩ ቁሳቁሶችን ከሌሎች አገራት በሚያስገቡበት ወቅት የውጭ ምንዛሬ የሚያሳድርባቸውን ተፅእኖ ለማስቀረት ከመደገፍ ጎን ለጎን የታክስ ክፍያን በተመለከተም እገዛ እንደሚያደርግ ማውሳቱን ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ቀስ በቀስ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የወጡ ሕጎችን ወደ ጎን በመተው ጋዜጠኞች እየታሰሩ፣ እየተደበደቡ እና የት እንዳሉ የማይታወቁበት ሂደት እንዳለ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፣ የሚዲያ ተቋማትም አጥፍታችኋል ተብለው እቃዎቻቸው እንደሚወሰድ እና በወቅቱ አፋጣኝ ምላሽ ሳይሰጥ የሚቀርበት ጊዜ አለ ይላሉ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር፣ መንግሥት በፕሬስ ነፃነቱ እንዲሁም በጋዜጠኞች ላይ የሚደረጉ ተደጋጋሚ እስራቶችን እንዲያስተካክል እና የወጡ ሕጎችንም እንዲከተል በተደጋጋሚ መወትወቱን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ እንደሚሉት፣ በቀጣይ መንግሥት ጋዜጠኞች በአስቸጋሪ ሂደቶች ውስጥ ሆነው ሥራቸውን እየሠሩ መሆናቸውን በመገንዘብ፣ የፕሬስ ነፃነቱን በማረጋገጥ፣ እንዲሁም ያወጣቸውን ሕጎች በመተግበር በትኩረት ሊሠራ ይገባል።
በተጨማሪ፣ የሚዲያ ፖሊሲ እና የመገናኛ ብዙኀን ሕጉን ተግብሮ ከማሳየት ባሻገር የኘሬስ ነፃነቱ አሁን ከተጋረጠበት አዙሪት ማውጣት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014



