96.7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 750 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

0
983

120 ዳያስፖራዎች በሪል ስቴት ዘርፍ ሊሳተፉ ነው

በ2014 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 96.7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 750 ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 750 የዳያስፖራ አባላት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በቱሪዝም እንዲሳተፉ የተለያዩ ድጋፎችን ለመስጠት ታቅዶ፣ 97.6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሳተፍ ፍላጎት ላላቸው አንድ ሺሕ 489 ዳያስፖራ አባላት የተለያዩ ድጋፎች መስጠቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው የ2014 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸሙ ላይ እንደገለጸው፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥ በማኅበር ተደራጅተው ሪል ስቴት ለመገንባት ሰባት ሚሊዮን ዶላር የቆጠቡ 120 የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት የግንባታ ቦታ ተረክበዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት 120 ዳያስፖራዎች የግንባታ ቦታ መረከባቸውን ይግለጽ እንጂ፣ የት እንደተረከቡና ስለሚገነቡት ሪል ስቴት የጠቀሰው መረጃ የለም። እንዲሁም የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው ቀሪዎቹ 630 ዳያስፖራዎች የተሰማሩበት ዘርፍ አልተብራራም።

በሌላ በኩል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳያስፖራው 150 ሚሊዮን ብር ከቦንድ ሽያጭ፣ ከስጦታና ልዩ ልዩ ፕሮግራም ለመሰብሰብ ታቅዶ 32 ሚሊዮን 664 ሺሕ 330 ብር የቦንድ ሽያጭ፣ 89 ሚሊዮን 320 ሺሕ 866 ብር ስጦታ፣ 833 ሺሕ 760 ልዩ ልዩ ገቢ በድምሩ ብር 122 ሚሊዮን 818 ሺሕ 957 በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በማሰባሰብ ከታቀደው 82 በመቶ ማሳካት ተችሏል ተብሏል።

እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍና የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም 300 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍና የተጎዱ መሠረተ-ልማቶች መልሶ ለመገንባት 1.14 ቢሊዮን ብር በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት አብራርቷል።

ለመከላከያ ኃይል እና “ለሕልውና ዘመቻ” 109 ሚሊዮን 813 ሺሕ 817 ብር ማሰባሰብ ተችሏልም ተብሏል። 6 ሚሊዮን 149 ሺሕ 940 ዶላር በ‹አይዞን ኢትዮጵያ› የገንዘብ ማስተላለፊያ መተግበሪያ እንደተሰበሰበ በሪፖርቱ ተካቷል።

የውጭ ምንዛሬ ፍሰት እንዲጨምር ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ገንዘቡን ወደ አገር ቤት ሬሚታንስ እንዲልክ ድጋፍና ክትትል በማድረግ በዘጠኝ ወር ሦስት ቢሊዮን ዶላር ለማስገባት ታቅዶ፣ 3.8 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት መላኩን ከብሔራዊ ባንክ መረጃ ማግኘቱን ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት ጠቅሷል። ከሐምሌ 1/2013 እስከ መጋቢት 30/2014 አምስት ሺሕ 250 የዳያስፖራ አባላት በአገር ውስጥ ባሉ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ አካውንት እንዲከፍቱ በማስቻል 6.3 ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ እንዲያደርጉ ታቅዶ አምስት ሺሕ 965 የዳያስፖራ አባላት የውጭ ምንዛሬ አካውንት ከፍተው አምስት ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ አድርገዋል ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here