በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ ጨፌ ቀበሌ የሚኖሩ ከ300 በላይ ነዋሪዎች ለልማት ተብሎ ቦታቸው ከተወሰደ ሦስት ዓመት ቢቆጠርም ካሳ እንዳልተከፈላቸው ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።
የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከ2011 ከመጀመሪዎቹ ወራት ጀምሮ ለሞጆ – ሐዋሳ የፈጣን መንገድ ግንባታ ተብሎ በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ ጨፌ ቀበሌ ከ300 በላይ ሰዎች የእርሻ መሬትና ቦታ በፌዴራል መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በኩል የመሬት ግምት ቢገመትም፣ የመሬቱ ግምት ክፍያው ሳይሰጣቸው ወደ አራተኛ ዓመት እየተሸጋገረ መሆኑን ተናግረዋል።
እያንዳንዱ ሰው 200 ሺሕ ብር እና ከዚያ በላይ የመሬት ግምት በባለሥልጣኑ በኩል እንደተገመተ የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፣ ለሐዋሳ ከተማ አስተዳደርና ለሲዳማ ክልል መንግሥት በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል። ሆኖም በጀት አለመለቀቁን ተከትሎ እንደተጎተተ እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በጀት በሚመድብበት ወቅት እንደሚሰጥ ቢነገራቸውም መረጃው እስከተጠናከረበት ግንቦት 11/2014 ድረስ እንዳልተሰጣቸው ጠቁመዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች አክለውም፣ የተወሰደባቸው መሬት እስከ አሁን ባለው የመንገድ ግንባታ ያልተገነባባቸው ቦታዎች እንዳሉ እና ለመሠረተ ልማት ካልዋለ መሬቱ እንዲመለስላቸው ቢጠይቁም፣ ቀስ በቀስ ለግንባታ እንደሚውል እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ለሞጆ ሐዋሳ የፈጣን መንገድ ግንባታ እንዲሆን ብሎ የገመተውን መሬት ሙሉ ለሙሉ ለግንባታ ካላዋለው እንዲመልስላቸው ወይም በግምት ያሰፈረውን ጥሬ ገንዘብ እንዲከፍላቸው ቅሬታ አቅራቢዎች ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሳምሶን ወንድሙ በበኩላቸው፣ በመንገድ ግንባታ ምክንያት የሚነሳ የቦታም ሆነ የመሬት ግምት ቅሬታዎችን ወረዳዎች አዘጋጅተው መረጃ ለባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት በሚልኩበት ወቅት ክፍያው የሚከፈል ሲሆን፣ ቅሬታ ያቀረቡትን ግለሰቦች ጉዳይ ግን እስከተጠየቁበት ጊዜ ድረስ የሚያውቁት መረጃ አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
አክለውም፣ ባለሥልጣኑ ቅሬታውን አጽዕኖት ሰጥቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ የቀረበው ቅሬታ እውነት ከሆነ ከባለ መሬቶቹ ጋር ተነጋግሮ ክፍያው የሚፈጸምበት ሂደት ይመቻቻል ብለዋል።
ኃላፊው በተጨማሪ፣ ባለሥልጣኑ በበጀት እጥረት ሳቢያ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመሬት ግምት ክፍያ ሳይከፈላቸው የሚጓተትባቸው ግለሰቦች እንዳሉ ሁሉ፣ አንዳንድ የመሬት ወይም የቦታ ግምት ክፍያ የማይገባቸው አካላትም ጥያቄ እና ቅሬታ የሚያቀርቡ እንዳሉም ጠቁመዋል።
የሞጆ ሐዋሳ የመንገድ ፕሮጀክት አካል የሆነው የሞጆ – ባቱ (ዝዋይ) የክፍያ ፍጥነት መንገድ የተሟላ የክፍያ ማከናወኛ ስርዓት ተሟልቶለት መስከረም 10/2014 ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ይታወቃል።
መንገዱ 92 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ አምስት ደረጃቸውን የጠበቁ የክፍያ ጣቢያዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል። የክፍያ ጣቢያዎች ሞጆ፣ ቆቃ፣ ቦቴ፣ መቂ እና ባቱ መውጫ ጣቢያዎች ናቸው ተብሏል።
ከተከናወኑት ሥራዎች መካከል የአምስት ክፍያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽን ሥራ ማከናወኛ ሕንፃዎች እና የሠራተኞች ማደሪያ ዶርሚተሪዎች፣ ጋራዦች፣ የተሽከርካሪዎች ደኅንነት ማስጠበቂያ ቴክኖሎጂዎች፣ የክፍያ ማከናወኛ ካኖፒ ተጠናቀው ወደ ሥራ መገባቱ ይታወቃል።
ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014



