ጥሪ ይቁም!

0
1248

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ምስቅልቅል ውስጥ እንድትገባ ያደረጓት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ የምትማርባቸው ተመሳሳይ ወቅቶች ከዚህ ቀደምም ሆነ በሌላ አገራት ስለመከሰታቸው የሚቀርብ ማስረጃ የለም። ሕዝብ በቀጣይ ምን ይፈጠር ይሆን እያለ ከደቂቁ እስከ ሊቁ ነጋ ጠባ እየተጨነቀ ባለበት በዚህ ወቅት፣ አባባሽ ተግባራት ተሰሚነት ባላቸው ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በመንግሥትም ሲፈፀሙ ማየት እየተለመደ መጥቷል።

የተወጠረ እንዲረግብ ቋጠሮን ማላላትም ሆነ መፍታት በቅድሚያ የመንግሥት ኃላፊነት ሆኖ ሳለ፣ አባባሽ ተግባሮች መፈፀማቸው ሊቆም እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች። ሆድ ብሶት ለተቀመጠ ማጭድን አፈላልጎ ሳይጠይቅ መስጠቱ እንደማያዛልቅ ከቀደመው ሥርዓት መማሪያው ጊዜ አሁንም አልረፈደም። `ትምክህተኛ` እያለ በትምክህት ኅብረተሰቡን እንደፈለገ እያጎረ ሲገድልና ሲያሰቃይ እንደኖረው ሥርዓት፣ አሁንም ተፈሪነትን ፍለጋ የሚደረጉ የማናለብኝነት ተግባሮች መጨረሻቸው እንደማያምር ለማወቅ አራት ዐይና መሆንን አይጠይቅም።

የጦርነት ነጋሪት በአንድ በኩል ሲጎሰም የሚያስከትለውን እልቂት እያወሱ እንዲያቆሙ መንገርና ለማሳመን መሥራቱ ተገቢ ሆኖ ሳለ፣ ጦር የሚሰበቅበትን ወገን ለይቶ ጦርነት አያስፈልገም እያሉ እንደ ከዚህ ቀደሙ እንዲዘናጋና ለማይቀር ጦርነት እንዳይዘጋጅ ማድረጉ ከጨፍጫፊዎች የማይለይ ደባ መሆኑ ግልፅ ነው።

ጦርነት ለማንም እንደማይጠቅም ሁሉም የሚያውቀው ቢሆንም፣ ከጥንት እስከ ዛሬ የሚጠቀሙበት ጥቂቶች በመኖራቸው ብዙኀኑን ለመማገድ ሴራ ሲጎነጉኑም ሆነ ተንኮል ሲጠነስሱ ይኖራሉ። ሰላም ሲሰፍን ዐይናቸው የሚቀላ የውጭ ጠላቶች ብቻ ሳይሆኑ ደጋፊዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉ መንግሥት ሊገነዘብ ግድ ይለዋል።

በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት፣ ‹ጦርነቶችን ሁሉ የሚቋጭ ታላቅ ጦርነት› እየተባለ በተለይ በምዕራባውያኑ የተቀሰቀሰውን የሰላማዊ ጦርነት ጥሪ ተከትለው፣ መንግሥታቸውን አምነው ወደውም ሆነ ተገደው የገቡት ሚሊዮኖች ከኹለቱም ወገን አልቀዋል። ከዚያኛውም ሆነ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ያልተማርነው እኛ፣ አሁንም ተመሳሳይ ድለቃ ውስጥ እንገኛለን።

የማስታወስ ብቃታችን ለአጭር ጊዜ ነው የሚባለው የእኛ የግለሰቦች ብቻ ሳይሆን የሕዝብ አካል ነኝ የሚለው የመንግሥትም መሆኑን ካለፈው አንድ ዓመት ስህተቱ አለመማሩን ማስረጃ እያጣቀሱ ማሳየት ይቻላል። በጭንቁ ጊዜ የረዱትን ባለማመን በየወንዙ መማማሉ ያላረካው አካል፣ ‹ሰውን ማመን ቀብሮ ነው› እንዳለችው ቀበሮ፣ ያለምንም ምክንያታዊ መነሻ ‹ለሰላም አስፈላጊ ነው› ያለውን ዘመቻ በአንድ ክልል ብቻ በድብቅ ከፍቷል። በዚህ የምንጠራ ተግባሩ ቀናት ሳይቆጠሩ መንግሥት ያጣው የሕዝብ ተቀባነት እንዳለ ሆኖ፣ በተወሰኑ ከተማዎች የተቃውሞ አመፅም ገጥሞታል።

መንግሥት ዘመቻውን ሲያቅድ ሰላማዊ ተቃውሞ ቢገጥመኝ ነው ብሎ የገመተ ቢመስልም፣ ጦርነትና ዘመቻ እንደታቀደው እንደማይሆን፣ አሁንም ደግሞ የሚመለከት ይመስላል። በጦርነቱ ወቅት በተለያዩ የውጊያ አውዶች ላይ ባሳዩት ተሳትፎ የሕዝብ ተቀባይነት ያላቸውን የፋኖ አባላትን ትጥቅ ለማስፈታትና ለመያዝ በሚል የዳቦ ሥም እየሰጡ አፈና ወደተባለ ድርጊት በሰፊው ገብተዋል። ከዚህ ቀደም ከሕዝብ ለመነጠል በተደጋጋሚ የተሸረበ ድርጊት ውጤታማ ካለመሆኑ ባሻገር፣ ከቀደመው ስህተቱ መማር ይገባ እንደነበር አዲስ ማለዳ ታስታውሳለች።
በቀዳሚው ኢሕአዴግ ዘመን ሊይዙት የመጡት አፋኞች ላይ እርምጃ በመውሰዱ ጀግና የተባለው የኮለኔል ደመቀ ዓይነት የአልሞት ባይ ተጋዳይነት እርምጃ ባህል ሆኖ እንዳይቀር የአፋኞችን ተግባር እስከመጨረሻው የሚያስቆም ፍትሓዊ ተግባር ሊታሰብበት ይገባል።

የቀረውን እንጥፍጣፊ ተቀባይነት ለማሳደግ በሕዝብ ጠላት ላይ መነሳት አልያም፣ የሕዝብን ፍላጎት ማሟላት ይገባው የነበረው መንግሥት፣ ይባስ ብሎ አንቅሮ ሊያስተፋው በሚችል መንገድ መጓዙ ዙሪያውን አሰፍስፈው ውድቀቱን የሚጠብቁትን የሥልጣን ተቀናቃኞቹንም ሆነ የውጭ ጠላቶቹን ተልዕኮ ራሱ እያስፈጸመ ይመስላል።

የትግራይ አስተዳዳሪዎች ከሆኑት የቀድሞ ገዢዎች ጋር ድርድር እንደጀመረ ሲነገር ቆይቶ ይፍረስ ይስማሙ ምንም ሳይታወቅ፣ ከጎኑ ሆነው ሲፋለሙ የነበሩ አደረጃጀቶች ላይ መዝመት ከክህደት በላይ ነው። ለአገር ሕይወቱን የሰጠን አካል ጠላቴ ብሎ ለተዋጋው አካል ፍላጎት ሲባል በድርድር ሥም መስዋዕት ማድረጉ ከአገር ክህደት እንደማይለይ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ሰላምና እርቅ አስፈላጊና ጠቃሚ ቢሆንም፣ ማሪቱ ለገሠ እንዳቀነቀነችው ከሽንፈት ሠላም ጦርነት ሳይሻል አይቀርም የሚል የሕዝብ አመለካከት ያለበት አገር ውስጥ መኖራችን ሊዘነጋ አይገባም። ጠላትን መቀነስ የሁሉም ወገን የጦር ስልት ቢሆንም፣ መጨረሻው በማይታወቅ መቦዳደን ውስጥ ገብቶ ምንም የማያውቅ የዋህ ሕዝብን ማስጨረስ በስተመጨረሻ አፈሙዙን ወደ ላከው አካል እንዲያዞር ያደርገዋል።

ምንም የኢትዮጵያ ጠላት ቢሆንም፣ ከሙሶሎኒ የመጀመሪያና መጨረሻ ታሪክ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ባለሥልጣናቱ ሊማሩ ያስፈልጋል። በመናገር የመጣ ዝና በተግባር ካልተደገፈ እንደ አፍ ወለምታ በቅቤ ታሽቶ አለመዳኑ ብቻ ሳይሆን፣ የሚያስከትለው መዘዝ ማብቂያ አይኖረውም።

‹የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል› እንደሚባለውም ስጋው እያለለት መውጊያን የሚነክስ፣ ጥርሱን ማጣቱ ብቻ ሳይሆን ለወደፊት የሚበላበትን ስለሚያጣ ተርቦ መሞቱ አልያም በመሰሎቹ መበላቱ አይቀርም። ታጥቆ የተቀመጠን አካል በዘዴ ማስፈታት ያባት ሆኖ ሳለ፣ ሕዝብን እየጨፈጨፈ ያለ ጠላት ባለበት ሰዓት፣ ወርሰህ ታጠቅ እንዳልተባለ የግል ትጥቅን ለመንጠቅና ለማፈን መሞከር፣ ተጠቂው ቅድሚያ የሚሰጠውን አካል እንዲቀይር ሊያደርገው እንደሚችል ሊታሰብበት ግድ ይላል። ከረፈደ የማይመለስበት አዘቅት ውስጥ ገብቶ ከማንም ወገን በኩል ቢሆንም እልቂት ከመከሰቱ በፊት አርቆ አሳቢዎች መሰማት እንዳለባቸው አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

በሕግ ማስከበር ሥም ሕግ አስከባሪዎችን የሚከፋፍል ተግባር ላይ አውቀውም ሆነ ሳያውቁት መግባት ማንን እንደሚጠቅም በቅርቡ የምንመለከተው ይሆናል። መንግሥት ለሥልጣኑም ሆነ ለሕዝቡ በትንሹም ቢሆን ካሰበ፣ ማድረግ ያለበት ነገር ቢኖር ሁኔታዎች እንዲረጋጉ እንጂ እንዲወሳሰቡ መሆን የለበትም። በሕዝብ ዘንድ የሚነሳ ቁጣን ለማብረድ እንደከዚህ ቀደሙ የጋራ ጠላት ተነሳብን ከጎኔ ሁኑ ቢል፣ አብሮት የሚሰለፍ ሳይሆን ከጀርባው ሆኖ የሚጠልፈው እንደሚበዛ ለማሰብ ሊቅ መሆን አይጠይቅም።

አንጋፋ ጋዜጠኞችን እንደተራ ወንበዴ አፍኖ ይህን አድርጉ ማለት አልበቃ ብሎ የአገር ባለውለታ የሆኑ ታላላቅ የጦር ጀነራሎችንና ባለሥልጣናትን ከሕግ አግባብ ውጭ ማንገላታትና ደብዛቸውን ማጥፋት እንደአገር አድራጊውን ብቻ ሳይሆን ተደራጊውንም ሕዝብ በጋራ የሚያስንቅ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

አንድ የቀድሞ ንጉሠ ነገሥት ‹‹ወንዶች እጃቸው ለሰለሰ፣ ጀግና የሚለይበት ጦርነት ጠፋ›› ብለው እግዜርን ጦር አውርድ ብለው በለበቅ ምድሪቱን ገረፉ እንደሚባለው፣ የዘመናችን ሹሞችም ሆኑ አጫፋሪዎቻቸው ለአላስፈላጊ ጦርነት ሲሉ ሰበብ ከመፈለግ ቢቆጠቡ መልካም ነው።

ጦርነት በአንድ ወገን ጥረት ብቻ ሊቀር የሚችል ባለመሆኑ ኹሉም ወደፍልሚያ ሊገባ የሚችል የሚዛትበትም ሆነ የሚዝት አካል የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። እርቅ ተብሎ የተዘናጋን የንጉሥ ሚካኤልን ጦር ሰገሌ ላይ የጠበቀውን እልቂት የሚያውቅ የዘመናችን ሰው፣ ወይ ሰጥ ለጥ ብሎ ለገዢዎች ያድራል አልያም አምፆ ከከተማ ወጥቶ ይዋጋል። በባህላችንም ሆነ በታሪካችን አስታራቂዎች ጦርነት እንዳይካሄድ፣ ይህም ካልሆነ ብዙ እልቂት እንዳይፈፀም ለኹለቱም ወገን ያገለግላሉ። ይህ የማይሆንም ከሆነ ጥጋበኞች ይፈታተሹ ተብሎ ከተራው ሕዝብ ርቀው ሜዳና ብዛት ወስነው እንዲራኮቱ ይደረጋል።

ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ በበዛበት፣ ግጭት አባባሽና መሣሪያ አስታጣቂ ባሰፈሰፈበት በዚህ ወቅት፣ የማንም መጠቀሚያ ለመሆን ከመናናቅና ከመተላለቅ ይልቅ፣ እየተፈራሩ ተከባብሮ መቆየቱ የተሻለ ነው። ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት አስከፊ ሁኔታ እንድትወጣ ዋናው ኃላፊነት የመንግሥት ቢሆንም፣ አቅም ያላቸውም ራሳቸውን እንደምናባዊ መንግሥት ቆጥረው በኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ አዲስ ማለዳ ጥሪ ታቀርባለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 185 ግንቦት 13 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here