ከአንድ እስከ ሦስተኛ ለሚወጡ አሸናፊዎች በጠቅላላው የ20 ሺህ ዶላር ሽልማት መዘጋጀቱም ተገልጿል
ሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ሄይፈር ኢንተርናሽናል “አዩቴ ኢትዮጵያ ቻሌንጅ 2022”ን በይፋ በማስጀመር በኢትዮጵያ ግብርና ላይ ያተኮሩና ሊበለፅጉ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ሀሳቦችን የሚያቀርቡ ወጣቶችን አወዳድሮ ለመሸለም መዘጋጀቱን አስታወቀ።
የአዩቴ አፍሪካ ቻሌንጅ በአህጉሪቱ ካሉት ታላላቅ የግብርና ውድድሮች አንዱ ለመሆን ያለመ ሲሆን፤ በዚህም የአፍሪካ ወጣቶችን ኃይል ከተለያዩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማጣመር በመላ አፍሪካ የሚገኙ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው ገበሬዎች ንግዳቸውን እና ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ የማድረግ ራዕይ ይዞ መጀመሩን የሄይፈር ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ቴድሮስ የሺወርቅ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሄይፈር ከመላው አፍሪካ ለተውጣጡና እጅግ ተስፋ የሚጣልባቸው የግብርና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ባለሙያ ወጣቶች የገንዘብ ስጦታ የሚሰጠውን አዩቴ አፍሪካ ቻሌንጅ በ2021 በይፋ መጀመሩን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ውድድር ላይ ከምዕራብ እና ምስራቅ አፍሪካ የተገኙ ኹለት ኩባንያዎች አሸናፊዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።
”አዩቴ ኢትዮጵያ ቻሌንጅ“ የአህጉር አቀፉ የአዩቴ አፍሪካ ቻሌንጅ አገር አቀፍ መልክ ሲሆን፤ ዓላማውም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አነስተኛ አርሶ አደሮችን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ እና ምርትን፣ ምርታማነትን፣ ገቢን፣ የፋይናንስ አቅርቦትን እና የመቋቋም አቅም ያላቸውን የግብርና ቴhኖሎጂ ፈጠራ ሐሳቦችን መርጦ መሸለም ነው።
ውድድሩ በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ወጣት አመልካቾች እና በፈጠራ ሥራዎቻቸው ልቀው ለሚወጡ ወጣት የአግሪቴክ ፈጠራ ባለሙያዎች በሙሉ ክፍት መሆኑንም ቴድሮስ ጨምረው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
”ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ስንል አዲስ ፈጠራ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን፤ ባሉን ነገሮች ላይ እሴት መጨመርና በዚህም ምርታማነትን ማሳደግ ነው።” ያሉት ደግሞ በሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የአዳዲስ ሥራ ዕድሎችና ፕሮጀክቶች ዳይሬክተር የሆኑት አለምፀሀይ ደረሰልኝ ሲሆኑ፤ የአገራችንን ችግር በራሳችን ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ልንፈታ ይገባል ብለዋል።
አክለውም ውድድሩ ትኩረቱን ግብርና ላይ ብቻ ማድረጉ እራሱን የቻለ ሰፊ እድል ይዞ የመጣ መሆኑን ገልፀው፤ እንደመንግስት አስፈላጊው ድጋፍ ኹሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
አዩቴ ኢትዮጵያ ቻሌንጅ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ለሚወጡ አሸናፊዎች በጠቅላላው የ20 ሺህ ዶላር ሽልማት ይዞ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፤ 1ኛ ለሚወጡ 10 ሺህ ዶላር 2ኛ ለሚወጡ 6 ሺህ 500 ዶላር እንዲሁም 3ተኛ ለሚወጡ የ3 ሺህ 500 ዶላር ሽልማት መዘጋጀቱ ተገልጿል።
በውድድሩ ለመሳተፍ የማመልከቻ ጊዜው ከግንቦት 13 ቀን 2014 ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ ዕድሜያቸው ከ8-29 የሆነ እና በኢትዮጵያ ግብርናን ለማሻሻል የሚረዳ የፈጠራ ሐሳብ ያላቸው የኢትዮጵያ ዜጎች መሳተፍ እንደሚችሉ ተነግሯል።
ተወዳዳሪዎች ለውድድሩ ማመልከት የሚችሉት የኦንላይን የማመልከቻ ፎርሙን በመሙላት ብቻ ሲሆን፤ የማመልከቻ ፎርሙን ለማግኘትም የሚከተለውን ሊንክን በመጫን ማግኘት ይቻላል :- https://ayute-ethiopia.et/apply-here/
የውድድሩ ዳኞች ቡድን ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአዋሽ ባንh፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሌሎች የግል ኩባንያዎች የተውጣጡ 8 ታዋቂ ባለሙያዎችን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




