በባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የሥርቆት ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ ተገለፀ

0
977

ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኪሳራ እስካሁን ደርሷል

ሐሙስ ግንቦት 18 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ለአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የሥርቆት ወንጀል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ገለፀ።

ሥራ አስኪያጁ ቡልቱማ ቂጣታ እንዳሉት፤ ለባቡር በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የሥርቆት ወንጀል የአገርን ኢኮኖሚ ወደኋላ ከማስቀረቱም በተጨማሪ በከተማዋ ያለውን የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እያስተጓጎለ ነው፡፡

በ2013 በጀት ዓመት ብቻ በዚሁ የቀላል ባቡር መስመር ላይ በተዘረጋ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ በተፈፀመ የሥርቆት ወንጀል 1 ሚሊዮን 293 ሺህ 350 ብር የሚገመት ርዝመቱ 1 ሺህ 55 ሜትር የኤሌክትሪክ ኬብል ሥርቆት እንደተፈፀመ ቡልቱማ አስታውቀዋል።

በ2014 በጀት ዓመትም 24 ሚሊዮን 800 ሺህ 725 ብር በላይ የሚገመት ርዝመቱ 15 ሺህ 347 ሜትር የኤሌክትሪክ ኬብል ሥርቆት መፈፀሙን ጠቅሰዋል፡፡

በአጠቃላይ ከ2013 ጀምሮ እስካሁን ድረስ 16 ሺህ 402 ሜትር የሚረዝም የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብል ሥርቆት ተፈፅሞ 26 ሚሊዮን 94 ሺህ 75 ብር የሚገመት ኪሳራ በተቋሙ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

አብዛኛው የባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ሥርቆት እየተፈፀመ የሚገኘው በቂርቆስ፣ በንፋስ ስልክ፣ በየካ፣ በልደታ፣ በአቃቂ ቃሊቲና በለሚኩራ ክፍለ ከተሞች መሆኑንም ቡልቱማ ጨምረው ገልጸዋል።

በዚህ ሳምንት ብቻ መሪ ሎቄ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ፣ ልደታ እና ሳሪስ አቦ አካባቢ ከመሬት በታች በተዘረጉ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብሎች ላይ ሥርቆት እና ውድመት መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ እየተባባሰ የመጣውን የባቡር የኤሌክትሪክ ኬብል ሥርቆት ለመከላከል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ቢሆንም ድርጊቱን በሚፈፅሙ ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪ ባለመሆኑ ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ሥራ አስኪያጁ መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕግ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ታሪኩ ማዕረጉ በበኩላቸው፤ በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀምን የሥርቆት ድርጊት ለመከላከል የተለያዩ አዋጆች በሥራ ላይ ቢውሉም፤ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንደመጣና ከፍተኛ የአገር ሃብት እየተዘረፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

እንደ ታሪኩ ገለጻ፤ በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ሥርቆት ሲፈፅም የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ በአገሪቱ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 669 መሰረት በከባድ ሥርቆት ወንጀል ተከሶ ከ15 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል።

በ2014 በጀት ዓመት 11 ወራት በተደረገ ክትትልና የማጣራት ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ በቁጥር ከ37 በላይ ‘’የሥርቆትና ጉዳት ማድረስ’’ የወንጀል ተግባራት ተፈፅመው ለተለያዩ የክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች ክስ ተመስርቶ በምርመራና በፍርድ ሂደት ላይ መሆናቸው ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here