ከአንድ ቤት ውስጥ ሦስት የቤተሰብ አባላት ተገድለዋል
ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በታጣቂዎች ጥቃት የተፈናቀሉ 600 የሚሆኑ ሰዎች ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻሉ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ በጎሮ ወረዳ የሲናሞ ቀበሌ ነዋሪ፣ የወረዳው የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉና እርዳታ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸው፤ ጥቃቱ በመቀጠሉ ምክንያትም የተፈናቃዮች ቁጥር ከ600 በላይ መድረሱንም አብራርተዋል።
የአካባቢው ታጣቂ ቡድን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ልዩ ልዩ ወረዳዎች ጥቃቱን እያስፋፋ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፤ ሰሞኑን ባደረገው ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነዋሪዎቹ ቤት ንብረታቸውን አስረክበው ቢፈናቀሉም ድጋፍ ባለመኖሩ “እንደ ወለጋ ነዋሪዎች ገፈቱን ለመቅመስ ተገደናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላኛው የአዲስ ማለዳ ምንጭ፣ አብዛኛው ተፈናቃይ ሰላም ወዳለበት ስፍራ በመጓዝ በዘመድ ቤት መጠጋቱን አንስተው፤ ቤት ንብረታቸው እንደወደመና እንደተዘረፈ ተናግረዋል። በቦታውም ጥቃቱን ሊመክት የሚችል የመንግሥት አካል (ታጣቂ) የለም ያሉት ተፈናቃዩ፤ ሕጻናት፣ እናቶችና አዛውንትን ጨምሮ የምግብ፤ የመጠለያና የአልባሳት ችግር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ለወራት ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻሉና ታጣቂ ቡድኑ ጥቃቱን እንዳላቆመ የጠቆሙት የአዲስ ማለዳ ምንጭ፤ ከኹለት ሳምንት በፊት አንድ ቤት ውስጥ ሦስት ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ተናግረዋል። ‹‹የሟቾቹን ሥም በትክክል አላውቅም እናት፤ አባትና ሚስት እንደሆኑ እርግጠኛ ነኝ።›› ሲሉ መስክረዋል ።
በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ውስጥ ጫንዶ ቀበሌ ታህሳስ 22/2014 ላይ 20 የአማራ ተወላጆች፤ በዳኖ ወረዳ አድላ ዳሌ ቀበሌ ጥር 23/2014 ደግሞ 13 የኦሮሞ ተወላጆች በታጣቂ ቡድኑ መገደላቸውም ተመላክቷል።
በሌላ በኩል፣ ጥቃቱ በሚሰነዘርባቸው ቦታዎች ያሉና ለማምለጥ ያልቻሉ ሰዎችን “ታጣቂ ቡድኑ ቤት ለቤት እየገባ መሣሪያ አምጡ እያለ እያስፈራራቸውና ንብረታቸውን እየዘረፈ ነው” ተብሏል።
ጥቃቱ እንዲቆም በመንግሥትና በሚመለከተው አካል በኩል ስር ነቀል እርምጃ ባለመወሰዱ አሁንም ግድያውና መፈናቀሉ ተባብሷል ያሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ሕይወት ስለሚበልጥ ንብረታችንን አስረክበን ሸሽተናል። ነገር ግን ልጆቻችንን ምን እናብላቸው? እንደዚህ የሚሆነውስ እስከ መቼ ነው? ብለዋል።
በወለጋ አካባቢ ላለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ንጹሀን ዜጎችን ገድሏል፣ ለቀላልና ከባድ አካል ጉዳት ዳርጓል፤ አፈናቅሏል፤ እንስሳትንና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ዘርፏል፤ ቤት ንብረት አውድሟል፤ ማሳዎች ጾም እንዲያድሩ አድርጓል የተባለለት ሽብርተኛ የተባለው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን፣ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃቱን ከወለጋ የተለያዩ ዞኖች ወደ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ማስፋፋቱን ከአስተማማኝ ምንጮች በተገኘ መረጃ ማወቅ ተችሏል።
ሸኔ በሚሰነዝረው ጥቃት ብቻ በኦሮሚያ ክልል ከአምስት ሺሕ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን በክልሉ የኮምዩኒኬሽን ቢሮ በኩል በቅርቡ የተሰጠው መግለጫ አመላክቷል።
አዲስ ማለዳ የተፈናቃዮችን ጥያቄ ይዛ ምላሽ ለማግኘት የኦሮሚያ ክልል የኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛን ብትጠይቅም፣ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ሙከራው ያልተሳካው ስልክ ዘግተው መልዕክት እንዲጻፍ ከጠየቁ በኋላና በጠየቁት መሠረት መልዕክቱ ቢላክም በድጋሚ ሲደወል ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014


