የዝንጀሮ ፈንጣጣና ስርጭቱ

0
1605

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወይም “ሞንኪ ፖክስ” እየተባለ የሚጠቀሰው የፈንጣጣ በሽታ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በወረርሽኝ መልክ ሊከሰት እንደሚችል ፍንጩ ከታየ ሰነባብቷል። ይህ ቆዳን በትንንሹ እያሳበጠ ለሕመምና እከክ የሚዳርገው በሽታ የሚመጣው በቫይረስ ምክንያት ነው።
በሽታው የዝንጀሮ ፈንጣጣ የተባለው በመጀመሪያ በሽታው ላቦራቶሪ ውስጥ ለሙከራነት ከተቀመጡ ጦጣዎች ላይ በመገኘቱ ነው። በማዕከላዊ አፍሪካ በስፋት ይገኝ የነበረው ይህ የቫይረስ ዝርያ አሁን በተለያዩ አገራት ተስፋፍቶ መገኘቱ ለብዙዎች ስጋት አሳድሯል።

‹ስሞል ፖክስ› ከሚባለው የተለመደው የፈንጣጣ ዝርያ ጋር ተቀራራቢ የሆነው ይህ በቫይረስ አማካኝነት የሚተላለፍ በሽታ እስከ አሁን ለከፋ ጉዳት ባይዳርግም፣ ተባብሶ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ጥናት እየተደረገበት ነው። ይህም በስፋት በአፍሪካ አገራት የተከሰተ ቢሆንም፣ ኮሮና ቫይረስ ያሳደረው ስጋት ገና ዓለማችንን ስላለቀቃት የምርምር ሥራው ላይ ብዙዎች እየተረባረቡ ነው።

አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝና አውስትራሊያን የመሳሰሉ አገራት ሳይንቲስቶቻቸው ስለበሽታው ስርጭትም ሆነ ባህሪ እንዲያጠኑና በቶሎ ግኝታቸውን እንዲያሳውቁ አዘዋል። እንግሊዝን የመሳሰሉ አገራት ደግሞ ቢከፋም ቢለማም ብለው ለፈንጣጣ በሽታ መከላከያ የሚሆነውን ክትባት ለጦጣ ፈንጣጣውም ሊሆን ይችላል በሚል ግምት ከወዲሁ ግዢያቸውን ማጠናከራቸውን ቢቢሲ አስነብቧል።

እስከ ቅርብ ቀን ድረስ በእንግሊዝ ብቻ 300 የሚሆኑ ሰዎች በጦጣ ፈንጣጣ በሽታ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ ዋናው የበሽታው መስፋፊያ እንደሆነ በሚነገርለት በመካከለኛውና ምዕራብ አፍሪካ ከ1 ሺሕ 200 በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ታውቋል። እስካሁን ኹለት ዓይነት የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ ዓይነቶች መኖራቸው የታወቀ ሲሆን፣ የምዕራብና የመካከለኛው አፍሪካ ዝርያዎች በመባል ይታወቃሉ።

በሽታው በዓለማችን ከተከሰተ 65 ዓመት አስቆጥሯል። ሆኖም እንደዘንድሮ ግን ከአፍሪካ ውጭ በርካቶችን አላዳረሰም ነበር። የስርጭት መጠኑ ያን ያህል አስጊ ነው ባይባልም፣ የጉዞ ታሪክ በሌላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይም መከሰቱ የስርጭቱ መንገድ መስፋቱን እንደሚያሳይ ተጠቁሟል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ የሚተላለፈው በቫይረስ አማካኝነት ነው ይባል እንጂ እንደ ኮሮና በአየር ስለመሰራጨቱም ሆነ በምን መንገድ ስለመዛመቱ ምንም የታወቀ ነገር የለም። ይህ ቢሆንም ግን እንግሊዝን የመሳሰሉ አገራት ዜጎቻቸው ግብረ ስጋ ግንኙነት ሲያደርጉ ኮንዶም በማድረግ እንዲጠነቀቁ መክረዋል። በጦጣ ፈንጣጣ ቫይረስ የተጠቃ ሰው ጋር ቢያንስ ነገሮች እስኪጣሩ ለ8 ሳምንታት ያህል ያለኮንዶም እንዳይጠቀሙ ተብሎም ለሕዝቡ አስቀድሞ ተነግሯቸዋል።

መተላለፊያውና ምልክቶቹ
የዝንጀሮ ፈንጣጣ የሚተላለፈው አንድ ቫይረሱ ያለበት ሰው ጋር ቅርብ ግንኙነት ሲፈጠር እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ቫይረሱ ወደ ሰውነት ሊገባባቸው ከሚችሉ መንገዶች መካከል ቆዳ ላይ በሚኖር ክፍተት፣ በመተንፈሻ አካል፣ በዐይን፣ አፍና በመሳሰሉ የሰውነት ቀዳዳዎች ሊገባ እንደሚችል የዘርፉ ተመራማሪዎች ሲናገሩ ይሰማል። ምንም ዓይነት ማስረጃ እስከ አሁን ባይገኝም፣ በግብረስጋ ግንኙነትም አማካኝነት ሊተላለፍ ይችላል ተብሎ ስለተገመተ ጥንቃቄ ማድረጉ አይከፋም ተብሏል።

በሽታው ከሰው ወደ ሰው ብቻ ሳይሆን የሚተላለፈው፣ ከእንስሳትም ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል ተብሎ ተገማች የቤት እንስሳት ተቀምጠዋል። ተጠንቀቋቸው ተብለው ከተጠረጠሩት መካከል አይጥ፣ ጦጣና ዝንጀሮ እንዲሁም ሽኮኮዎችን የመሳሰሉ እንስሳት ተጠቃሾች ናቸው። ከእንስሳቱም ሆነ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር በሚኖር ቀጥተኛ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፣ የነኩትን ጨርቅም ይሁን የተለያየ ቁሳቁስ በመንካትም ሊተላለፍ ይችላል ተብሏል።

ምልክቶቹን በተመለከተ በበሽታው የተያዘ ሰው በመጀመሪያ ሊያሳያቸው ከሚችሉ ምልክቶች መካከል ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ እብጠት፣ የጀርባ ሕመምና የጡንቻ ስቃይ የሚጠቀሱ ጠቋሚዎች ናቸው።

ትኩሳቱ ሲቀንስ የቆዳ መቆጣት ስለሚከተል ማሳከክ ይጀምራል። ማበጡ የሚጀምረው በመጀመሪያ የፊት ቆዳ ላይ ቢሆንም ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችም ይሸጋገራል። በይበልጥ የእጅ መዳፍንና የእግር መረገጫ ቆዳን የሚያጠቃ ሲሆን፣ በጣም ማሳከክም ይቀጥላል።
ፈንጣጣው የሚከሰትበት የተለያየ ደረጃ ያለው ሲሆን፣ በሂደት የተለያዩ ቦታዎችን እያጠቃ ይቆያል። በዚህ የቆይታ ጊዜው በጣም በማሳከክ ሕመሙና ስቃዩ የሚበረታ ሲሆን፣ በስተመጨረሻ አካባቢ እከኩ እንደመቁሰል ብሎ እባጩ ይደርቃል። ከዚህም በኋላ የሚረግፍ ሲሆን፣ በኋላ ላይም ቁስሉ ጠባሳ ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች አሳስበዋል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሰውነት ላይ በይፋ የሚታይባቸውን ሂደት ካለፈ በኋላ በአንድ ሰው ሰውነት ላይ በተከሰተ ከ14 ቀን እስከ 21 ቀን ውስጥ ባሉት ጊዜያት ሙሉ በሙሉ ምልክቶቹ ይወገዳሉ ተብሏል። ለበሽታው የተጋለጠ ሰው ከሚሰማው ስቃይና ሕመም በስተቀር በዘላቂነት ጉዳት የሚያስከትልበት ሁኔታ አይኖርም ቢባልም፣ በጥናት መረጋገጥ እንዳለበት ተጠቁሟል።

“ቺክን ፖክስ” እየተባለ ከሚታወቅ የበሽታ ዝርያ የተለየ ሕመም አይኖረውም የተባለም ሲሆን፣ ኅብረተሰቡ ሳይረበሽ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተመክሯል። በሌላ በኩል ግን በበሽታው ሳቢያ ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ ሰው መሞቱ የታወቀ ሲሆን፣ ይህም መዘናጋት እንዳይኖር የሚያሳይ ነው ሲሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

የበሽታው አመጣጥ
የዝንጀሮ ፈንጣጣ ዓለማችን ላይ መከሰቱ የታወቀው በፈረንጆቹ 1957 ላይ መሆኑን የCDC መረጃ ያመላክታል። በቤተ ሙከራ ውስጥ ለምርምር ተብለው በተቀመጡ ጦጣዎች ላይ የታየው ይህ በሽታ፣ ከምርምር ማዕከሉ ወጥቶ በኅብረተሰቡ ዘንድ ለመከሰት የፈጀበት አጭር ጊዜ ነበር። በ1970 በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ላይ ቫይረሱ የተገኘ ሲሆን፣ ከዛን ጊዜ ወዲህ መከላከያውንም ሆነ መድኃኒቱን ለማግኘትም ሆነ ጨርሶ ዝርያውን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ሳይንቲስቶች ርብርብ ላይ መሆናቸው ይነገራል።

አብዛኛው በበሽታው የሚያዝ ሰው የኮንጎ ዜጋ ቢሆንም፣ በካሜሩን፣ በሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ፣ በኮትዲቯር፣ በጋቦን፣ በላይቤሪያ፣ በናይጄሪያና ሴራሊዮን በስፋት መከሰቱ ይታወቃል። አብዛኞቹ አገራት በበሽታው የሚያዙትን ሰዎች ቁጥር ለይተው ስለማይመዘግቡ ይህን ያህል ሰው እስከ ዛሬ በጦጣ ፈንጣጣ ተይዟል ለማለት እንደማይቻል ተነግሯል።

ከአፍሪካ ውጭ መከሰት ከጀመረ ወዲህ በተሻለ መታወቅ የጀመረ ቢሆንም፣ እንደዘንድሮ ትኩረት አግኝቶ የአገራትን ርብርብ አለማግኘቱ ተጠቁሟል። ጦጣና መሰል ዝርያዎች መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ግምት ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ቆይቷል። እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ እስራኤልና ሲንጋፖርን በመሳሰሉ አገራት በስፋት ቢከሰትም፣ አሁንም ድረስ መነሻውና ተፈጥሮ መቀመጫው የሆነው እንስሳ ባለመለየቱ ኹሉንም አገራት ያዳርሳል የሚለው ስጋት አልቆመም።

ባለፉት 15 ቀናት ብቻ በ780 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መኖሩ በላቦራቶሪ ምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን፣ በሽታው የተገኘባቸውም ሰዎች ከአፍሪካ ውጭ ባሉ በ27 አገራት የሚኖሩ መሆናቸውን ሪሊፍ ዌብ አስነብቧል። ከአፍሪካ ውጭ ቫይረሱ “ኢንደሚክ” ባልሆነባቸው አገራት መከሰቱ በራሱ ወረርሺኝ ሊያስብለው ይችላልም ተብሏል። እንዲሁም የበረራ ታሪክ የሌላቸውና ከታማሚዎች ጋር ምንም ዓይነት ትስስር የሌላቸው ሰዎች ጭምር መያዛቸው ነገሩን ግራ አጋቢ እንዳደረገው ተጠቁሟል።

እንደዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ፣ አሁን ያለው የስርጭቱ መጠን በጣም አስጊ የሚባል ሳይሆን መካከለኛ ሊባል የሚችል ነው። እንደተቋሙ ሪፖርት እስከ አሁን ከአፍሪካ ውጭ በበሽታው ተይዘው የሞቱ ስለመኖራቸው ምንም የተመዘገበ አሃዝ የለም። በሽታው በተለምዶ በሚገኝባቸው የአፍሪካ አገሮች ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ ይነገራል። በዓለም ዐቀፍ ደረጃም መጀመሪያ ወረርሺኝ መከሰቱ ከተነገረ ወዲህ፣ ስርጭቱ እየሰፋ በርካቶች እየተጠቁ መሆናቸውን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ምዝገባ ታውቋል። ከኹለቱ ዝርያዎችም ከአፍሪካ ውጭ የተመዘገበው ምዕራብ አፍሪካ ነው ተብሏል።

ወረርሺኙን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥትም በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ መግለጫ አውጥቶ ነበር። በአገሪቱ 20 መግቢያና መውጫ መተላለፊያዎች ላይ መቆጣጠሪያዎችን በማቋቋም ስርጭቱን ለመግታት እየጣረ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ባለሥልጣናት አሳውቀው ነበር።

በሽታውን ለመለየት የሚያስችሉ 50 የላቦራቶሪ ማዕከላትም ተለይተዋል የተባለ ሲሆን፣ መመርመር የሚያስችል መሣሪያና ኬሚካል ለማዕከሎቹ ለማሟላት እየተሠራ እንደሆነ ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በተሰጠው መግለጫ ተጠቁሟል። መመርመሪያ ቁሳቁሶቹ በዓለም ላይ መመረት አቁመው ስለነበረ እጥረት በመኖሩ ግዢ ለመፈፀም እንቅስቃሴ መጀመሩም ተጠቅሷል።

እስከ አሁን በኢትዮጵያ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ስለመከሰቱ ባይታወቅም፣ ከተለመደው ቀጠናው ወጥቶ ሌሎች አገራት በመከሰቱ ኢትዮጵያም ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ባለሥልጣናቱ አሳውቀዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here