ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)”መደመር” በሚል ርዕስ ያዘጋጁት አዲስ መጽሐፍ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ በአማርኛ እና በኦሮምኛ ቋንቋዎች ለገበያ እንደሚውል አዲስ ማለዳ አረጋገጠች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ፍልስፍና ይዘው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ጽፈውታል የተባለው ይህ መጽሐፍ ህትመቱ የተጠናቀቀ ሲሆን ገቢው በገጠር ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ይውላል።
በሦስት መቶ ብር ወይም በ 30 የአሜሪካን ዶላር ለገበያ የሚውለው ይህ መጽሐፍ 365 ገፆች ሲኖሩት በ16 ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው። አዲስ ማለዳ እጅ የገባው የአፋን ኦሮሞ ቅጂ ጀርባ ከመጽሐፉ የተቀነጨቡ አንቀፆችም መጽሐፉ የመደመር ፍልስፍናን ከተለያየ አቅታጫ መመልከቱን ያሳያል።
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም የተራራቁ የአስተሳሳብ ጫፎች አሉ›› የሚለው መጽሐፉ እነዚህን አቻችሎ መሔድ ላይ ግን የታሪክ እርግማን ያለብን ይመስላል። በሌላ በኩል ደግሞ የታሪክ ትርክቶችን ተከተሎ መሔድ እንደ መልካም ልምድ የመውሰድ አዝማሚያ አለ›› ሲል ያትታል።
በተጨማሪም ልማት እና እድገትን ማምጣት የሚቻለው በመንግሥት ተቋማት፣ በግሉ ዘርፍ፣ በሲቪል ማህበራት በትምህርት ተቋማት መደመር እንጂ ብቻውን ጠንክሮ በመውጣት አይደለም የአገር ለውጥ የሚረጋገጠው የሚል መልዕክትም የመጽሐፉ ጀርባ ላይ ሰፍሯል።
ኢትዮጵያ በተጨባጭ ያለችበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባትም ወደ ዴሞክራሲ መሔድ አስፈላጊ ነው የሚለው መጽሐፉ፣ ይህንንም ለማድረግ ሌሎች ሃገራት እንዴት ተሳካላቸው የሚለውን ማየት እና የመጣንበትንም መንገድ መፈተሽ አስፈላጊ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እርካብ እና መንበር”ን ጨምሮ ሌሎች መንፈሳዊ መጽሐፍትን እንዳዘጋጁ ባሳለፍነው ሳምንት በሸገር ሬዲዮ የጨዋታ ፕሮግራም ላይ በነበራቸው ቃለ ምልልስ አረጋግጠዋል። ይህ የመደመር ፖለቲካዊ ፍልስፍናን የያዘው መጽሐፍ ከታተመ ከተወሰኑ ወራት በኋላ በድጋሚ ቀለል ባለ ቋንቋ ታትሞ ለንባብ አንደሚበቃ መናገራቸውም ይታወሳል።
መጽሐፉ እስኪወጣ የተለያዩ አገራት ዜጎች በተለይም አፍሪካዊያን ይህንን መጽሐፍ በጉጉት እየጠበቁ ነው ሲሉም መናገራቸው ይታወሳል። ብዙ የአፍሪካ ወጣቶች “መደመር” መጽሐፍ እስኪወጣ እየጠበቁ ነው ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከአስር የሚበልጡ የአፍሪካ ሃገራት ወጣቶች ወደ ሥልጣን ለመምጣት ወደ እርሳቸው መጥተው እንዳነጋገሯቸው እና የመደመር ፍልስፍናም ከኢትዮጵያ ተሻግሮ በአፍሪካ ሃገራት ላይም ውጤት ያመጣል ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ባልደረቦቻቸውን እና የትግል አጋሮቻቸውን አመስግነዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012



