በዳኞች ላይ የሚደርስ ጥቃት ይቁም!

0
512

ኢትዮጵያውያን ለዳኝነት ክብር፣ በፍትሕም እምነት እንዳላቸው የታሪክ መዛግብት እንዲሁም አንዳንድ ብሂሎች ይነግሩናል። “በፍትሕ ከሔደ በሬዬ፣ ያለፍትሕ የሔደች ጭብጦዬ” ሲሉም ርቱዕ በሆነች ፍትሕ የማይቀበሉት እንደማይኖር ይናገራሉ። በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ዘመናዊ የሕግ ስርዓትን ከመተዋወቋ በፊት በአገር ሽማግሎች ዳኝነት ብዙ መፍትሔዎች ተሰጥተዋል፤ ዳኝነቶች ተካሒደዋል። አጥፊውን ለማረምና ለሌላውም ትምህርት እንዲሆን በሚሰጠው በዋርካው ሥር ፍትሕ አሰጣጥ፤ የተፈረደለት “እልልል. . . ” ሲል የተፈረደበት ቅጣቱን ሲቀበል፤ ዳኛ ተብለው የተሰየሙ ሊቃውንትም ሲፈርዱ፤ ሁሉም ስለፍትሕ እውን መሆን ብቻ ነበር።
በስራ ላይ ያለው ሕገ መንግስት ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ በማለት የመንግስት አካላትን ለሶስት ከፍሎ የሚመለከት ሲሆን፤ እነዚህም እርስ በእርሳቸው ሳጣረሱ ተግባራቸውን በመከወን አገር በህግ እንዲመራ ሚናቸው የላቀ ነው። በመካከላቸውም የቁጥጥርና ምዘና ተግባር ስለሚኖራቸው ለሚፈጽሙት/ለሚያስፈጽሙት ተግባር ተጠያቂነት እንዲኖራቸው ያደርጋል። በተለይ ሕግ ተርጓሚ የሆነው የፍርድ ቤት አእምሮ የሆኑ ዳኞችን ዜጎች እንዲታዘዟቸው ይጠበቅባቸዋል፤ ውሳኔያቸውም ተፈጻሚ እንዲሆን የግድ ነው።

ይህም ከእነዚህ ሰዎች የተለየ ማንነት የመነጨ ሳይሆን ከዋርካው ሥር እንደሚቀመጡና እንደሚዳኙ ቀደምት አባቶች ሁሉ ፍትሕን ለመስጠት የተሰየሙ በመሆናቸው ነው። ከሕግ በላይ አለመሆን ከዚህ የሚጀምር ነው። እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት አካላት በተለይ የሕግ አስፈጻሚው በፍርድ ቤቶች ወይም በዳኞች የዕለት ተዕለት ሥራ ጣልቃ እንደማይገባ ይጠበቃል።

ይሁንና በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የእነዚህ ሦስት የመንግሥት አካላት የእርስ በርስ ጣልቃ ገብነት በተለይ በቅርብ ጊዜ የአገረ መንግሥት ታሪካችን ውስጥ ጎልቶ ይታያል። በተለይ ሕግ አስፈጻሚው አካል የዳኝነቱን ስርዓትም ላይ ሆነ ሕግ አውጪው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ብሎም ለራሱ የህልውና ጥቅም በግልጽ ጣልቃ እንደሚገባ ቀደም ብለው ሲወጡ የነበሩ ሕጎችን/አዋጆችን በምሳሌነት መዘርዘር ይቻላል፤ የተሰጡ ፍርደ ገምድል የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን መመርመርም ይቻላል። አዲስ ማለዳም በተለያየ ጊዜ ሕግ ተርጓሚ በሆኑ ዳኞች ላይ የተለያዩ ጫናዎች መደረጉ ላይ ዘገባ ያጠናቀረች ሲሆን ይህ ጉዳይ በጊዜ ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ ሊባል ይገባዋል በማለት አጽንዖት ትሰጣለች።

ለአብነትም በቅርቡ በተለይም በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በእነዚህ የፍትሕ አካላት የወሰኑት ውሳኔ ተፈጻሚ ሳይሆኑ መቅረት፣ በዳኞች ላይ ማስፈራሪያና ዛቻ ማድረግ፣ ጥይት በመተኮስ በፍርድ ውሳኔያቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደር እና ዳኞች በግፊት ሥራቸውን እንዲለቁ ወይም እንዲሰደዱ በማድረግ የፍትሕ ስርዓቱን ማስተጓጎል፣ ውሳኔ ላይ ጫና ማሰደር ብሎም ውሳኔ ማስቀልበስ የሚደርሱ ተጽዕኖዎች እንደደረሱ ከዳኞች አረጋግጣለች።

በተለይ የዳኞች የሕግ ከለላ ማጣት ህልውናውቸውን አደጋ ላይ ከመጣል ባሻገር የተሰጣቸውን ትልቅ ኀላፊነት በብቃትና በሙሉ ነፃነት መወጣት እንዳይችሉ ያደርጋል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ለፍርድ ቤት እና ለዳኞች ጥበቃ ይደረግ፤ ፍትሕንም በልበሙሉነት፣ ሕግና ሕሊናቸውን ተጠቅመው እንዲያስፈጽሙ ሊደረግ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ አጽንዖት ትሰጣለች። የፍትሕ በርታዊነት አለመፈጸም መዘዙ ብዙ ነው፤ ለሕገ አልቦነትም ለግለሰብ አምባገነንት በር ይከፍታልና።

በአንድ አገር ገለልተኛ የሆነ፣ በማንም ተጽእኖ ሥር የማይወድቅ ዳኛ መኖሩ ለሁል ጊዜም አስፈላጊ ነው። ይህ ያልሆነ እንደሆነ በመጀመሪያ ተጎጂ የሚሆኑት ዜጎች ናቸው። ፍትሕ ርዕት ተፈጻሚ ስለማይሆን ማለት ነው። የፍርድ ቤት አካላት የሆኑት ዳኞች ከመዛግብት ተማክረው፣ ግራ ቀኙን አይተው፣ የቀደሙ የውሳኔ ዶሴዎችን አገላብጠው እና ነፃ አእምሯቸውን ተጠቅመው ለመዳኘት እንዳይችሉ ይሆናል። በመሆኑም ዳኞች ከሰውነታቸው ባሻገርም የቆሙለት ፍትሕ-ርትዕ ሲባል ክብር ሊያሰጣቸው የሚገባ ነው።

በየትኛውም የሙያ መስክ ላይ ያለ ሰው በአገሩ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት እንዳለው ሁሉ ዳኞችም እንደባለሙያ አገልግሎት ለመስጠት በአገራቸው ከቦታ ቦታ ሊንቀሳቀሱ ይገባል። ሕግ ተርጓሚነታቸውና የሚሰጡት ውሳኔም ከተወለዱበት አካባቢ ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል። ፍርድ ቤት ፍትሕን ፍለጋ የሚቆሙ ሰዎችም ከሕጉና ከዳኝነት እንጂ ከዳኛው ማንነት የሚያገናኛቸው ጉዳይ ሊናራቸው አይገባም ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
በተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሕግ ትምህርትን የሚማሩና ወደ ፊትም ለዳኝነት ወንበር የሚጠበቁ ዜጎች ይህ ሥጋት ሊሆንባቸው አይገባም። ዳኛም ሆነ ዳኝነት በሕጉ መሠረት እውነተኛ የሆነችውን ፍትሕ መተግበር፣ የተጻፈውን ሕግ መተርጎም እንጂ ከጥላቻም ሆነ ከፍቅር ጋር ማበር አይደለም።

አዲስ ማለዳ ይህ በዳኞች ላይ የሚደርስ ጥቃት ሕግን እንዳለማክበር ይቆጠራል ብላ በጽኑ ታምናለች። በመሆኑም በዳኝትና በፍርድ ቤቶች ላይ የሚደርሰው ግልጽም ሆነ ስውር ተጽዕኖ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቆም ይገበዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ በፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ ያለውን መተማመን ከማሳጣት ባሻገር ወደለየለት ጥፋት አምርቶ የአገር ህልውናን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ስትል አዲስ ማለዳ አጽንዖት መስጠት ትፈልጋለች። የፍርድ ቤት አመራሮችም ከፖለቲካ ስራዎች በመውጣት የዳኞችን ደህንነት ለማስጠበቅ ቅድሚያ ይስጡ!

ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here