በቀድሞ የደርግ ባለሥልጣን ላይ የተወሰነው የእድሜ ልክ እስራት እንዲጸና ተበየነ

0
1337

የደች ዜግነትን ያገኙትና የቀድሞ የደርግ መንግሥት ባለሥልጣን የነበሩት መቶ አለቃ እሸቱ ዓለሙ ላይ የዓለም ዐቀፉ የጦር ወንጀለኞች በሚዳኙበት በሄጉ ፍርድ ቤት ተወስኖ የነበረው የእድሜ ልክ እስራት እንዲጸና የደች ፍርድ ቤት መወሰኑ ተዘግቧል።
የ67 ዓመቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ጉዳይን ሲመለከት የነበረው የሄጉ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ በጦር ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው የነበሩትን የቀድሞ የኢትዮጵያ ባለሥልጣን ይግባኝ ጥያቄ ባለፈው ረቡዕ ውድቅ አድርጓል።

የቀይ ሽብር ዘመቻ ተካሂዶበታል በሚባለው በ70ዎቹ መጀመሪያ በነበራቸው ተሳትፎ ከአምስት ዓመት በፊት ጥፋተኛ ተብለው የነበሩት ይግባኝ ባይ፣ ውሳኔው ውድቅ እንዲደረግላቸው አመልክተው ክሱን ግን በነበረባቸው ከፍተኛ ሕመም ምክንያት በአካል ተገኝተው መከታተል አለመቻላቸውን ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል።

የዓለም ዐቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አካል የሆነው የደቹ ፍርድ ቤት፤ ይግባኛቸውን ሲከታተል የቆየ ሲሆን፣ ሰሞኑን የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አፅንቶ የእድሜ ልክ እስራቱ ተፈጻሚ እንዲሆን ማዘዙ ተሰምቷል።

መቶ አለቃ እሸቱ ዓለሙ በ1970 እና 1971 የደርግ መንግሥት የጎጃም ግዛት ባለሥልጣን በነበሩበት ወቅት ፈጽመውታል በተባለ የጦር ወንጀል ተከሰው ነበር ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የተደረገው። በዓለም ዐቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ቀርበው ከተከራከሩ በኋላም፣ ጥፋተኛ ተብለው የእድሜ ልክ እስራት ነበር የተበየነባቸው።

ዓለም ዐቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔውን የሰጠው፣ ተከሳሹ የጦር ወንጀሉ በጎጃም ግዛት በተፈፀመበት ወቅት የሚደረገውን ያውቁ ነበር በሚል ነው። በድርጊቱም ተሳትፈዋል በሚል በሥልጣን ዘመናቸው ፈፅመውታል በተባለ የተለያየ የጦር ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ሲል ነበር የወሰነባቸው። ይህንንም ተከትሎ በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ በፈረንጆቹ 2017 የወሰነባቸው ሲሆን፣ ከዛም ጊዜ አንስቶ ውሳኔው እንዲቀለበስላቸው በጠበቃቸው አማካኝነት ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አቤት ብለው ውሳኔውን ሲቃወሙ ቆይተዋል።

ይግባኛቸውን ሲከታተል የነበረው የሄጉ ዓለም ዐቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አካል የሆነው የደቹ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ ሰሞኑን የመጨረሻ ውሳኔውን ይግባኝ ባዩ በአካል በሌሉበት አሰምቷል።

እንደፍርድ ቤቱ ገለጻ ከሆነ፣ መቶ አለቃ እሸቱ ዓለሙ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በጎጃም በርካታ ተማሪዎች፣ ወጣቶችና ምሁራንን ለእስር ዳርገዋል። ከተቃዋሚዎች ጋር መንግሥታቸው በሚዋጋበት በዛን ወቅት እስከሞት የሚደርስ አላስፈላጊ የሆነ እርምጃን በመንግሥት እጅ ላይ በነበሩት ላይ ፈፅመዋል በሚል ጥፋተኛ እንዳደረጋቸው ይፋ ባደረገው የውሳኔ መግለጫ አሳውቋል።

ይግባኝ ባዩ መቶ አለቃ እሸቱ ከ5 ዓመት በፊት የእድሜ ልክ እስራት የተወሰነባቸው በደርግ ዘመን የተሠራውን የጦር ወንጀል በማመናቸው ነበር። ስርዓቱ ወጣቶች ላይ የተለያዩ ግፎችን መፈፀሙን ያመኑት እኚህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ፣ በግላቸው ተነሳስተው ሳይሆን ከበላይ በመጣ ትዕዛዝ መሠረት የፈጸሙት ተግባር እንደሆነ ቢናገሩም ተቀባይነት አላገኙም። ዓለም ዐቀፍ የጦር ወንጀል የፈጸመ ሰው ታዝዤ ነው በማለት ራሱን ከተጠያቂነት ማዳን ስለማይቻለው፣ በሥልጣን ዘመናቸው ለተሠራው የጦር ወንጀል መጠየቅ አለባቸው በሚል ነበር ጥፋተኛ የተባሉት።

የደርግ መንግሥት ከሥልጣን እንዲለቅ ከተደረገ በኋላ ሸሽተው ወደ አውሮፓ የገቡት የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው እኚህ የቀድሞ ባለሥልጣን፣ ጥገኝነት ጠይቀው የገቡት ኔዘርላንድ ስለነበር ነው የደቹ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ሲከታተል የቆየው። በዘጠናዎቹ መጀመሪያ ባገኙት የደች ዜግነት አማካኝነት ፍርዳቸውን በዛው አገር እየተከታተሉ መቆየታቸውም ታውቋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 188 ሰኔ 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here