በሚል ስያሜ ኢሕአዴግ ውሕድ ፓርቲ ሊሆን ነው
ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) በትጥቅ ትግል ላይ እያሉ በትግራይ በረሃ በ1981 የመሰረቱት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የኢትዮጵያ የብልፅግና ፓርቲ (ኢብፓ)/ Ethiopian Prosperity Party (EPP) ሊባል እንደሆነ አዲስ ማለዳ ከታማኝ ምንጮች ሰማች።
በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ፍልስፍና ሲመራ የቆየው ኢሕአዴግ የአፋር፣ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የሶማሌና የሐረሪ ክልል ገዢ ፓርቲዎችን በማቀፍ አንድ ወጥ ፓርቲ ሆነው ለመውጣት የፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብና ለኢትዮጵያ ብልጽግናን ያመጣሉ ተብለው ተስፋ የሚጣልባቸውን የፓርቲውን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በወጣት ምሁራን በማስረቀቅ ሒደት ላይ መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ያረጋግጣሉ።
ከመስከረም 8 ጀምሮ ለአምስት ቀናት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ስብሰባ የተቀመጡ ሲሆን በጉባዔው አብዮታዊ ዴሞክራሲን በመተካት የአዲሱ ፓርቲ የፖለቲካ ፍልስፍና ይሆናል በተባለው የመደመር የፖለቲካ ቀመር ላይ ውይይት እየተደረገ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ማረጋገጥ ችላለች። የመደመር ፍልስፍና ላይ በባህር ዳር፣ በአዳማ እና ሐዋሳ ከተሞች ላይ የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ ወጣቶችንና ምሁራንን ያሳተፈ ዝግ ስብሳባ እየተደረገ ይገኛል።
ተዋህዶ ወጥ ፓርቲ ስለመሆን ማውራት ከጀመረ ከ17 ዓመት በላይ የሆነው ኢሕአዴግ በ1994 የቀድው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በዋሺንግተን ዲ.ሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባደረጉት ስብስባ ላይ በተሳታፊዎች ተጠይቀው ጉዳዩን አንስተውት እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጂ ሐሳቡን አንድ ዕርምጃ እንኳን ወደፊት ሳይንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ከተመረጡ ከመጋቢት 2010 ጀምሮ በተደጋጋሚ ጉዳይን ከመገናኛ ብዙኀንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሲወያዩበት ቆይቷል።
ውሕደቱ መቼ ይፈጸም የሚለው ጉዳይ ላይ ካልሆነ በቀር ውሕደቱን የሚቃወም የኢሕአዴግ አባል ድርጅት የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸውም ይታወሳል። ይሁን እንጂ በምስረታ ላይ ባለው ወጥ ፓርቲ የሕወሓት ተሳትፎ አጠያያቂ እንደሆነ ይነገራል።
የአዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሸገር ሬዲዮ ጣቢያ የጨዋታ እንግዳ ሆነው በቀረቡበት ወቅትም “ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የሚወስድ አንድ ፓርቲ ይመሰረታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ በጉዳዩ ላይ ዘርፈ ብዙ ውይይቶች እንደሚደረጉ መናግራቸው ይታወሳል።
“በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሕደቱን እንዴት ማከናወን ይቻላል የሚለው ላይ እየተወያየን ነው” ሲሉ ያከሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ዴሞክራሲን በውስጥ [በኢሕአዴግ ውስጥ] ካልተገበረነው በውጪ ልንፈጽመው ስለማንችል ብዙ ውይይት እናደርግበታልን። ስለዚህ ውይይታችንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቋጭተን በቅርቡ አንድ ዜና ይዘን እንመጣለን ብለን እናስባለን” ብለዋል።
ኢሕአዴግ የአራት ፓርቲዎች ግንባር ሲሆን አባላቱም ሕወሓት፣ አዴፓ፣ ኦዴፓና ደኢህዴን ናቸው።
ቅጽ 1 ቁጥር 46 መስከረም 10 2012



