የጥራት ደረጃቸው አነስተኛ የሆነና ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን ብረታብረቶች የመረከብና የማጓጓዝ ሥራ እየተሰራ ነው

0
789

 

ዕረቡ ግንቦት 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተገዝተው የጥራት ደረጃቸው አነስተኛ የሆነና፤ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን ብረታ ብረቶችን የመረከብ እና የማጓጓዝ ሥራ እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ንብረት አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አበበ ጉዲሳ እንደገለፁት፤ ብረታብረቶቹ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በአሁኑ ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ በኩል ከውጭ አገር ተገዝተው የገቡ ናቸው፡፡

ኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ብረታ ብረቶቹን ለግድቡ ግንባታ በሚል ገዝቶ ወደ አገር ውስጥ ያስገባቸው ቢሆንም፤ የጥራት ደረጃቸው አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት በሞጆ፣ በቢሾፍቱ፣ በአቃቂና በመካኒሳ ቅርንጫፍ ጣቢያዎቹ አከማችቷቸው መቆየቱን አበበ ገልፀዋል፡፡

የተለያየ መጠን እና ዓይነት ያላቸውን ብረታ ብረቶች በመረከብ በ529 ተሽከርካሪዎች ወደ ቆቃ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የማጓጓዝ እና የመደርደር ሥራዎች መከናወኑን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡

ቢሮው ብረታ ብረቶቹን ከኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ቅርንጫፍ ጣያቢያዎች ወደ ቆቃ የኃይል ማመንጫ ላጓጓዘበት እስካሁን ከ12 ሚሊየን ብር ያላነሰ ወጪ እንዳወጣ የገለፀ ሲሆን፤ ቀሪ ብረታ ብረቶችን እያጓጓዘ በመሆኑ ወጪው ከዚህም ከፍ ሊል ይችላል ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለመልካ ሰዲ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ጥቅም ላይ ይውላሉ ተብለው ተገዝተው የነበሩ የአርማታ ብረታ ብረቶችን እና የመሬት ውስጥ ተቀባሪ የኤሌክትሪክ ገመዶችን የመረከብ ሥራ እየተሰራ እንደሆነም ሥራ አስኪያጁ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ንብረቶቹን ኮተቤ ወደሚገኘው የተቋሙ ዕቃ ግምጃ ቤት የማጓጓዝ ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

በቁጥር 14 ሺህ 319 የሚሆኑ የተለያየ ክብደት እና ዓይነት ያላቸው የአርማታ ብረቶች እና 35 ድራም የሚመዝኑ የተለያየ ሥፋት እና ርዝመት ያላቸው የመሬት ውስጥ ተቀባሪ የኤሌክትሪክ ገመዶች ርክክብ ተደርጎባቸዋል፡፡

ለተቋሙ አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉትን ብረታ ብረቶች በመለየት ቀሪውን ለሽያጭ በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ የሚገኝበት ምክረ ሃሳብ ለተቋሙ ሥራ አመራር እንደሚቀርብ አበበ መጠቆማቸውን ከተቋሙ ያገኘኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here